Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየጤናውን ዘርፍ ጫና የሚያጠና ፕሮጀክት

የጤናውን ዘርፍ ጫና የሚያጠና ፕሮጀክት

ቀን:

በኢትዮጵያ በማኅበረሰብ ጤና፣ በድንገተኛ የጤና ችግሮችና ባዮሜዲካል በሆኑ ጉዳዮች የጥናትና ምርምር መረጃዎችን በአግባቡ መሰብሰብ፣ ማደራጀትና ሳይንሱ የደረሰበትን ጥበብ በመጠቀም መተንተንና የትንትና ውጤቱ የሕዝቡን ጤና ለማሻሻል እንዲውል የማድረጉ ሥራ ይህንንም ያህል የተቀናጀ አይደለም፡፡

በጤናው ዘርፍ በርካታ የጥናትና ምርምር መረጃዎች ለዓመታት በአገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ ሲሰበሰቡ የቆዩ ቢሆንም፣ ጥናቶቹ በተለያዩ ተቋማትና ተመራማሪዎች እጅ ተበታትነው ይገኛሉ፡፡

የአገሪቱን የኅብረተሰብ ጤና ጥናትና ምርምር እንዲመራ በአዋጅ ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስትር ጋር በመተባበር ከሁለት ዓመት በፊት ብሔራዊ የጤና ጥናትና ምርምር ማደራጃና ትንተና ማዕከል አቋቁሟል፡፡

- Advertisement -

ማዕከሉ የበሽታዎች ሥርጭትና አጋላጭ መንስዔዎቻቸው የሚያስከትሉትን የተለያዩ የጤና እክሎችን የሚያጠና ፕሮጀክት ቀርፆ ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ላይ በይፋ አብስሯል፡፡ 12 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለትና ለአራት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆነውን ይህንኑ ፕሮጀክት ያበሰሩትም የጤና ሚኒስትር አሚር አማን (ዶ/ር) ናቸው፡፡

የፕሮጀክቱ አጋርና የገንዘብ ምንጭ ቢል ኤንድ ሚሊንዳጌትስ ፋውንዴሽንና በዓለም አቀፍ ደረጃ 350 የሚርሱ በሽታዎችና አደጋዎች እንዲሁም አጋላጭ መንስዔዎቻቸውን በማጥናት ከፍተኛ ዕውቅና ያለውና ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው ኢንስቲትዩት ፎር ሔልዝ ሜትሪክስ ኤንድ ኢቫሉዌሽን (አይኤችኤምኤ) ናቸው፡፡

ከእነዚህም መካከል አይኤችኤምኤ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር ጥናቱን ከማካሄድ ባሻገር የብሔራዊ ማዕከሉን አቅም ይገነባል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ኢንስቲትዩቱና አይኤችኤምኤ የካቲት 2010 ዓ.ም. አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ ማከናወኛ የሚውለውን በጀት የሸፈነውም ፋውንዴሽኑ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ሦስት ዓላማዎች እንዳሉት፣ ከእነዚህም ማዕከሉን በሚፈለገው የሠለጠነ የሰው ኃይል እንዲሁም በቴክኖሎጂና በሌሎች ቁሳቁሶች መገንባት ይገኙበታል፡፡ በአገርና በክልል ደረጃ ጤናና ጤና ነክ የጥናት መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ የመረጃ ቋት ማዘጋጀትና ማደራጀት፣ ዘመኑ የደረሰበትን የሳይንስ ጥበብ መጠቀምና መተንተን፣ የዳታ ቅብብሎሽን ማሳለጥ፣ ቀዳሚ የሆኑ የጤና ችግሮችን መሠረት ያደረጉ የጥናት መረጃ ማሰባሰብ፣ ከአይኤችኤምኤ ጋር በመተባበር በየዓመቱ በርካታ በሽታዎችንና አደጋዎችን እንዲሁም አጋላጭ መንስዔዎችን ማጥናትም የፕሮጀክቱ ዓላማዎች ናቸው፡፡  

በጤናው ዘርፍ የሳይንሳዊ ጥናት ፍላጎትና አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የአቀራረብ ሥልትን ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ መተግበር፣ የበሽታዎች ሥርጭትና የጤና ጫና ላይ የተሠሩ የጥናት ውጤቶች አዎንታዊ ተፅዕኖ መከተታተልና ማጠናከር ከፕሮጀክቱ ዓላማዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶ/ር)፣ ፕሮጀክቱ በጤናው ዘርፍ ያለውንና ሊኖር የሚገባውን መረጃ በማበልፀግ ላይ ብቻ ሳያተኩር በአካዳሚክ ኢንስቲትዩሽን፣ በአጠቃላይ በአገር ደረጃ መረጃን ከማዳረስ አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው፣ በጋራ የመሥራት ባህልን ማዳበር ታሳቢ አድርጎ እንደተቃኘ ተናግረዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር በሔልዝ ሴክተርና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ላይ ካስቀመጣቸው ፕሮግራሞች መካከል አንዱ የመረጃ አብዮት (ኢንፎርሜሽን ሪቮሊሽን) ነው፡፡ ይህ ዓይነቱም አካሄድ የጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የግብርናውና ሌሎችም ዘርፎች በመረጃ ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ቢያደርጉ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ፕሮጀክቱ በሴክተር ደረጃ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ባሻገር በአኅጉር ደረጃም ተመሳሳይ ጥቅሞችን ለመስጠት እንዲያስችል ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ከእነዚህም ሥራዎች መካከል አንዱና ዋነኛው የአፍሪካን አጠቃላይ የጤና ጉድለቶች የሚከታተለው የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከል ማዕከል የአቅም ግንባታ ለመስጠት መንቀሳቀሱ እንደሚገኝበት ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡

የቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር ሰለሞን ዘውዱ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክት በአብዛኛው የሚሠሩት በውጭ ሰዎች ነበር፡፡ ፋውንዴሽኑ የአገር ልጆች እንዲያከናውኑት የማድረግ አቅጣጫ መከተሉን፣ ለዚህም በአቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረገ ድጋፍ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ ፋውንዴሽኑ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ሦስት ዓይነት ኢንቨስትመንቶችን አብሮ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ከኢንቨስትመንቶቹም መካከል ማዕከሉን መርዳት፣ በምርምር የሚገኙትን መረጃዎች ማጠናከርና የአቅም ግንባታ ሥራ ማከናወን ተጠቃሾች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር አሚር አማን (ዶ/ር)፣ በኢትየጵያ በየዓመቱ 700,000 ሰዎች እንደሚሞቱ፣ 86 ሚሊዮን የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ በተለያዩ የጤና ተቋማት የጤና አገልግሎት እንደሚያገኙ ገልጸው፣ ሰዎች የጤና እክል የሚጋጥማቸውና የሚሞቱባቸው ምክንያቶች ምንድናቸው? የሚለውን በዝርዝር ለማወቅና ተገቢውንም መፍትሔ ለመስጠት መረጃ ወሳኝ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ፍትሐዊና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የበሽታዎችን ምክንያቶች ማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶች በሽታን በትክክል ለመፈወስና ለመከላከል እንዲሁም ጤናን ለማበልፀግ የሚያስችሉ መሆኑን በእርግጠኝት ማወቅና ይህንንም በማስረጃ ማስደገፍ ግድ መሆኑን አክለዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ አገሮች በመረጃ ላይ ያለው ዕይታ ብዙ መስተካከል አለበት፡፡ በተለይ ቁጥር ሲጠራ ሃይ ባይና ተጠያቂነት የለም፡፡ የዛሬ ሳምንት የተነገረው ቁጥር በሚቀጥለው ሳምንት በተመሳሳይ አጀንዳ ላይ ሌላ ቁጥር ሆኖ ይጠራል፡፡ ይህ ዓይነቱ ተጨባጭነት የሌለው የመረጃ አያያዝ የተሳሳተ ስለሆነ መቀየር ይኖርበታል፡፡

ለዚህም ዕውን መሆን በመረጃ ላይ ተመሠረተ ውሳኔ የሚሰጥ አመራርና የጤና ባለሙያ ማፍራት እንደሚያስፈልግና አጠቃላይ ቴክኖሎጂውን ዲጂታላይዝድ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ጊዜ ከ97 በመቶ በላይ የሚሆኑ ጤና ተቋማት ጤና ጣቢያ፣ ሆስፒታል፣ የወረዳና የዞን ጤና ትሕፈት ቤቶች የክልል ጤና ቢሮዎችና ሚኒስቴሩን በ4ጂ ዳታ ለማገናኘት እየተመሞከረና በዚህም የተወሰኑ ውጤቶች መታየት እንደጀመሩ ገልጸዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...