Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኩሪፍቱ የባህል ማዕከልና የውኃ ፓርክ ሥራ ጀመረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ውስጥ የሪዞርት ኢንቨስትመንትን በማስተዋወቅ ኩሪፍቱ ሪዞርት ስፖ በቀዳሚነት የሚቀመጥ ኩባንያ ነው፡፡ በደብረ ዘይት ኩሪፍቱ ሐይቅ ዳርቻ በከተማ ከሚታወቀው ዘመናዊ ሆቴሎች በተለየ የውጭ ቱሪስቶችንም ሆነ ሌሎች እንግዶችን በተለየ ድባብ ለማስተናገድ የሚያስችሉ 15 ማረፊያዎችና ሌሎች አገልግሎት የሚሰጡ ግንባታዎችን በማካሄድ ወደ ሥራ የገባ ሪዞርት ነው፡፡

የኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፖ ገና ከመነሻው የግንባታ ይዘቶቹ አገራዊ አሻራ ኖሯቸው በአገር በቀል የግንባታ ግብዓቶች የሚታነፁና አሁንም ድረስ ይኼው የግንባታ ሥልቱ በሁሉም ሪዞርቶቹ ላይ የሚታይ ነው፡፡ ለእንግዶች ማረፊያ የሚሆኑት የመኝታ ክፍሎች እንዲሁም ለሌሎች አገልግሎት የሚውሉት ግንባታዎች፣ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ አገራዊ ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡ የመመገቢያ ጠረጴዛዎች፣ አልጋዎች፣ ቁም ሳጥኖች፣ የየክፍሎቹ መዝጊያና ኮርኒስ በሙሉ በአገር ውስጥ በሚገኙ እንጨቶች፣ ጠፈሮችና ሌሎች ግብዓቶች የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በሰፊው የኩሪፍቱ ኢንቨስትመንትም እነዚህን ምርቶች የሚያመርት ወርክሾፕ አለው፡፡ ከእንጨት የተሠሩ መገልገያ ዕቃዎች በማሽን ሳይሆን በእጅ ተልገውና ተፈልፍለው የተሠሩ መሆናቸውም ኩሪፍቱና ዕደ ጥበብን አዋድዷል፡፡ እንዲህ ባለው የአገነባብ ሥልት በቢሾፍቱ የተጀመረው ኢንቨስትመንት በአዳማ፣ በባህር ዳር፣ በትግራይ፣ በጂቡቲና በሌሎች ሪዞርቶቹም ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡

ከ15 ዓመታት በፊት የተጀመረው የኩሪፍቱ ጉዞ አሁንም የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ ለቱሪስት ያስፈልጋሉ የተባሉ አገልግሎቶችና ግንባታዎችን በማስፋፋት እየሠራ ያለው ሥራ አሁንም እንደሚቀጥል የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ አንድ ብሎ በጀመረበት ኩሪፍቱ ሪዞርት ዙሪያ፣ እንዲሁም ከኩሪፍቱ ውጪ ባሉ ይዞታዎች ሁሉ አዳዲስ ግንባታዎችን መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ሁሌም አዲስ ገጽታ ካለው ግንባታ ጋር አዲስ ፈጠራ የታየበት አገልግሎት ለመጀመር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ያደርጋል፡፡ ከኩሪፍቱ ሪዞርቶች ውስጥ በተለይ የደብረ ዘይት ሪዞርት አገልግሎት ከሚሰጡት ነባር ግንባታዎች ጎን ለጎን የማስፋፊያ ሥራ ወይም የአዲስ አገልግሎት ግንባታ አይጠፋም፡፡  ለኩሪፍቱ ሪዞርቶች ውስጣዊና ውጫዊ የግንባታ ግብዓቶች የሚሆኑ ምርቶችን የሚያመርተው ወርክሾፑም ሁሌም ሥራ ላይ ነው፡፡ ለአዲስ አገልግሎት የሚሆኑ ዲዛይኖችን በመቀበል ያመርታሉ፡፡ አንዱ ፕሮጀክት ተመርቆ ሥራ ሲጀመር ወዲያው በአዲስ ሐሳብ፣ ሌላ አዲስ ነገር የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በወርክሾፑ ሁሌም ድንጋይ ይጠረባል፡፡ እንጭት ይፈለፈላል፡፡ ጠፈር ይወጠራል፡፡ ለመጋረጃና ለመሳሰሉ አገልግሎት የሚውሉ ጨርቃ ጨርቆች ይቀደዳሉ፣ ይሰፋሉ፡፡ ከቀርከሃ የሚሠሩ መገልገያዎች ሳይቀሩ ይሠራሉ፡፡ የመኝታ ቤት መብራቶቹም በአገር በቀል ግብዓቶች የሚሠሩ ናቸው፡፡ በኩሪፍቱ የግንባታ ሥራ ቆሞ አያውቅም የሚለውን የሚያጠናክረው ደግሞ ከሰሞኑ ለአገልግሎት ያበቃውና በቀጣይ የሚሠሩ ሥራዎችን ማሳወቁ ነው፡፡   

ይህም ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በደብረ ዘይት የኢትዮጵያ ካልቸራል ሴንተርና የዋተር ፓርክ ፕሮጀክትን አስመርቋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በውስጡ ኢትዮጵያ ባህላዊ እሴቶችን፣ የእጅ ጥበብ ውጤቶችንና ባህላዊ መደብሮችን የያዘው  በኢትዮጵያ ካልቸራል ሴንተሩ 123 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊ ሱቆችን ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል፡፡ ‹‹ሁሉም የኢትዮጵያዊ መልክ ያላቸውና ኢትዮጵያውያን የሠሩዋቸው ሻምፒዮን የኢትዮጵያ ምርቶች ያሉባቸው ሱቆችና ሦስት ባንኮች ያሉበት ነው፤›› ያሉት የኩሪፍቱ ሪዞርት ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታዲዮስ ጌታቸው ናቸው፡፡ በቅዳሜው የምረቃ ፕሮግራም ወቅት የብዙዎችን ዓይን የያዘው ደግሞ በባህላዊ መደብሮች መሀል ላይ የተገነባውና ለአገልግሎት የበቃው ‹ዋተር ፓርክ› ነው፡፡ የአገሪቱን ቱሪስቶችን ለመሳብ ብሎም የአገር ውስጥ ነዋሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በአዲስ አገልግሎት እንዲስተናገዱ የሚያስችል የውኃ መዝናኛ ነው፡፡ የውኃ ማዕከሉ ለአዋቂና ለሕፃናት መዝናኛ የሚሆን ሲሆን፣ በ72 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ አርፏል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ካልቸራል ሴንተርና የዋተር ፓርኩ ፕሮጀክት በአንድ ጊዜ 1,980 እንግዶች ማስተናገድ የሚስችል ሲሆን፣ በማዕከሉ ውስጥ ባህላዊ መጠጥና ምግብ የሚዘጋጁበት ሥፍራዎች አሉት፡፡ የመዝናኛ ሥፍራውም ከውኃ ላይ ጨዋታዎች ባሻገር እንደ ሰርከስ ያሉ ትርዒቶች የሚታዩበት ቦታ አለው፡፡ አንድ ሺሕ ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡  

እንዲህ ያለው የቱሪዝም መዳረሻ ቦታ የአገር ገጽታ በመቀየር በኩል የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው የሚሉት አቶ ታዲዮስ፣ ‹‹የአገር ገጽታ የሚቀየርና የኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከአፍሪካ ዳያስፖራ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመሆን የአገራችንን ቱሪዝም ዘርፍ እናሳድጋለን፤›› በማለት አክለዋል፡፡  

እንደ አቶ ታዲዎስ ገለጻ፣ በዚህ ማዕከል ቀጣይ ምዕራፍ ያለው ግንባታዎች ይካሄዳሉ፡፡ ዋተር ፓርኩ ተጨማሪ ግንባታዎች እንደሚኖሩት ገልጸዋል፡፡ በኩሪፍቱ ቀጣይ የግንባታ ሥራዎች መኖሩን የሚያመላክተው ደግሞ በምርቃቱ ሥርዓት ላይ መሠረት የተቀመጠለት አዲስ ፕሮጀክት ነው፡፡

ይህንንም ገላጭ የሚደርገው በዕለቱ የካልቸራል ማዕከሉና ዋተር ፓርኩን በክብር እንግድነት በመገኘት የመረቁት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አዱኛ ለአገልግሎት የበቃውን ማዕከል ሪቫን ብቻ በመቁረጥ አልተወሰኑም፡፡ ኩሪፍቱ አዲስ ግንባታ አለኝ በማለቱ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ለዚህ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ እንዲጥሉ ተደርጓል፡፡ የመሠረተ ድንጋይ የተጣለለት አዲሱ ፕሮጀክት በዕለቱ ከተመረቀው ማዕከል ጎን በኩሪፍቱ ሪዞርት አስፈላጊ ነው የተባለውን የስብሰባ አዳራሽና 200 የመኝታ ክፍሎችን ያጠቃለለ ግንባታ ለማካሄድ የታለመለት ነው፡፡

እንደ አቶ ታዲዎስ ገለጻ በቢሾፍቱ ሪዞርት የሚገነባው አዳራሽ ከ2,000 በላይ ሰዎችን በአንዴ የሚያስተናግድ ሲሆን፣ በኩሪፍቱ ደረጃ የሚገነቡት 200 የመኝታ ክፍሎች ደግሞ እየጨመረ ይሄዳል ተብሎ ለሚታሰበው ቱሪስት በበቂ ዝግጅት ለማስተናገድ ታስቦ ነው፡፡ በቅዳሜው ፕሮግራም ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፖ ሌላም የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት ፕሮግራም ነበረው፡፡ ይህም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ነዋሪዎች መማሪያ የሚሆንና ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ክፍል የሚያስተምር ትምህርት ቤት ለመገንባት የሚያስችለው ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች