በኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለውና ከሕገወጥ ንግድ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ተመለከተ፡፡ ይህ የተገለጸው የንግድና ኢንዱትስሪ ሚኒስቴር ከዋጋ ንረትና ቁጥጥር ሥራ ጋር በተያያዘ ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ከንግድ ኅብረተሰቡና ጉዳዩ ይመለከታችኋል ከተባሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በተዘጋጀ መድረክ ላይ ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ በተደረገው የምክክር መድረክ ላይ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር መንግሥት ቁጥጥሩን ያጥብቅ የሚለው አመለካከት የጎላው፣ በዕለቱ በዋጋ ንረት ላይ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍን ተከትሎ በተሰጠው አስተያየት ነው፡፡
ይህንኑ የውይይት መድረክ አስመልክቶ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንደገለጸው፣ ኅብረተሰቡ በስፋት የሚጠቀምባቸው የፍጆታ ሸቀጦች በተለይም በምግብ ሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ እየተስተዋለ ባለው የዋጋ ንረት ምክንያት ባለ አንድ አኃዝ የነበረው የዋጋ ግሽበት ወደ ሁለት አኃዝ ከፍ ብሏል፡፡
የዋጋ ጭማሪው ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለውም የሚለው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መረጃ፣ የዋጋ ንረቱ ግን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ስለመጉዳቱ ጠቅሷል፡፡ በተለይ ግን ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍሉን የበለጠ እየጎዳ መሆኑ ገልጿል፡፡
አሁን ላለው የዋጋ ንረት ምክንያት ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥም በአንዳንድ ነጋዴዎች ይፈጸማል የተባለው ያላግባብ ምርት የማከማቸት ተግባር ነው፡፡ የምርት እጥረት ሳይኖር ምርቱን በማከማቸት በገበያ ውስጥ ሰው ሠራሽ እጥረት በመፍጠር የሚፈጸመው ተግባር፣ የኑሮ ውድነቱን ከማባባሱም በላይ ሸማቹን ስለማማረሩ ይጠቅሳል፡፡ የመግዣ ዋጋና የመሸጫ ዋጋዎችን አለመለጠፍም ለችግሩ መባባስ እንደ ምክንያት ተጠቅሰዋል፡፡
ንግድ ሚኒስቴር ባደረገው ጥናትና በዕለቱ በቀረበው ጥናት ለኑሮ ውድነት መባባስ ምክንያት አድርጎ የጠቀሳቸው የደላሎች አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ይጠቀሳል፡፡
የኮንትሮባንድ ንግድም ሌላው ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ምክንያት እንደሆነ እንዲሁም ንግድ ፈቃድ ሳይኖር በተለያዩ ተሽከርካሪዎች የሚፈጸሙ የንግድ ሥራዎች የየራሳቸው አስተዋጽኦ ነበራቸው ተብሏል፡፡
የዋጋ ንረትን ለመቀነስና ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ መሠረታዊ ፍጆታዎችን እንዲያገኝ ያስችላሉ የተባሉት የሸማቾች ማኅበራትና ዩኒየኖች በአግባቡ አለመሠራታቸው ለኑሮ ንረቱ የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዳላቸውም የተመለከተበት መድረክ ነበር፡፡
ያለደረሰኝ የሚደረግ ግብይትም ሌላው ምክንያት እንደሆነ በቀረበው ጽሑፍ ተጠቅሶ፣ እንደ ዱቄት ፋብሪካ ያሉ ተቋማት ደግሞ ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ በማድረግ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ አድርገዋል ተብሏል፡፡ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ተደርጓል ተብሏል፡፡
ይህንን ጥናት ለማዘጋጀት አዲስ አበባ ውስጥ በ162 በሚሆኑ ዳቦ ቤቶች ላይ በተወሰደው መረጃ በተገኘው ውጤት መሠረት፣ አራት ዳቦ ቤቶች ብቻ በትክክል ግራም የሚሠሩ መሆኑን ተገልጿል፡፡
የዱቄት አምራቾችም በመንግሥት ድጎማ እስከ 550 ብር የሚቀርብላቸውን ስንዴ ከ2,000 ብር በላይ በመሸጥ ያልተገባ ጥቅም እንደሚያገኙም ተጠቅሷል፡፡
በሲሚንቶ፣ በብረታ ብረትና በሌሎች መሠረታዊ ዕቃዎች ላይ የታዩት የዋጋ ለውጦችም በተመሳሳይ ሰው ሠራሽ ስለመሆናቸው የሚጠቁም ነው፡፡ በዚሁ መነሻነት ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዕርምጃዎችን እየወሰደ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡ ኅብረተሰቡም ተባባሪ መሆን አለበት የተባለ ሲሆን፣ አሁን ያለውን የዋጋ ንረት ለመከላከል ቁጥጥሩ መጥበቅ እንዳለበት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር፣ የዋጋ ንረቱ በተለይ በትልልቅ ከተሞች ላይ የሚስተዋል መሆኑ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውም ይህንን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሥርዓት አልበኛ ነጋዴዎችንም ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት ጠበቅ ያለ የቁጥጥር ሥርዓት እየተዘረጋ ስለመሆኑ፣ የምክክር መድረኩን የተመለከተው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መረጃ አትቷል፡፡