Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በችኩንጉኒያ ከ20,000 በላይ በኮሌራ ደግሞ 64 ሰዎች ተይዘዋል

በድሬዳዋ ከተማ በተከሰተው ችኩንጉኒያ ወረርሽኝ ከ20,000 በላይ እንዲሁም በተለያዩ ሦስት ክልሎች በሚገኙ ልዩ ልዩ ሥፍራዎች አልፎ አልፎ በሚታየው የኮሌራ ወረርሽን 64 ሰዎች ተይዘዋል፡፡ ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ በተከሰተው የችኩንጉኒያ ወረርሽኝ የተመዘገበ ሞት እንደሌለ፣ በኮሌራ ወረርሽኝ ለተያዙ ሰዎችም ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በየነ ሞገስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የችኩንጉኒያ ወረርሽን ‹‹ኤደስ›› በምትባል ትንኝ ንክሻ ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን፣ ለዚህ ዓይነት ወረርሽኝ የሚሰጠው ድጋፋዊ ሕክምና ነው፡፡ ይህ ማለት ምልክቶቹን ማከም ወይም እንዲሻላቸው የሚያደርግ ማስታገሻ መስጠት ነው፡፡ ቫይረሱን የሚገድል ወይም ሙሉ ለሙሉ ሊያጠፋ የሚችል መድኃኒት የለውም፡፡ ድሬዳዋ ውስጥ ቤት ለቤት በተካሄደው አሰሳ 86 በመቶ የሚሆኑት ቤቶች ወረርሽኙን የሚያስተላልፉት ትንኞች እጭ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ይህም ሊፈጠር የቻለው ነዋሪዎቹ ለንጽህና መስጫና ለልብስ ማጠቢያ ሲሉ የዝናብ ውኃ በማጠራቀማቸውና የተጠራቀመውም ውኃ ክፍቱን ሲውል እጮች በመፈጠራቸው ነው፡፡ እነዚህ በየቤቱ ብዙ ሰዎችን ማጥቃት ችለዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችል ምላሽ በመስጠት ላይ ሲሆን፣  የባለሙያ፣ የኬሚካሎች፣ የመድኃኒትና የሕክምና ድጋፍ ከማድረጉም ባሻገር ለሥራ ማስኬጃ የሚውል 1.2 ሚሊዮን ብር አበርክቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው የኮሌራ ወረርሽን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር የተቻለ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል በሻሸመኔና ፈዲስ ወረዳዎች 35፣ በሐረሪ ክልል ስድስት ወረዳዎች 15፣ በሐዋሳ ከተማ 14 በድምሩ 64 ሰዎች ተይዘዋል፡፡ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በየነ ሞገስ (ዶ/ር) በሁለቱም ወረርሽኞች ዙሪያ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን መልስ ታደሰ ገብረማርያም እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡

ጥያቄ፡- ችኩንጉኒያ ወረርሽኝ በአፋር እንደተከሰተ ቀላል ግምት ተሰጥቶት ነበር፡፡ አሁን ግን በ20,000 የሚቆጠሩ ሰዎችን ለበሽታ ዳርጓል፡፡ ይህን ያህል የተስፋፋው የመከላከሉ ተግባር ተዘንግቶ ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት አለው?

ዶ/ር በየነ፡-ችኩንጉኒያ ወረርሽኝ በዚህ ዓመት ድሬዳዋን ጨምሮ በአራት ክልሎች በሚገኙ ልዩ ልዩ ሥፍራዎች ተከስቷል፡፡ በዚህም መሠረት መጀመርያ በአፋር፣ ቀጥሎ በሶማሌ ክልል ቀብሪደሃር ከተማ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ዳውሮ ወረዳ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ለአራተኛ ጊዜ ድሬዳዋ ላይ ተከስቷል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ግን በሶማሌ ክልል መከሰቱ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓመት የተከሰተውን ወረርሽኝን ብቻ በምሳሌነት ብንመለከት ወረርሽኙ ከወባ ጋር የተያያዘ ይመስል ነበር፡፡ ከሌሎችም ትኩሳት ከሚያመጡ በሽታዎች ጋር ይያያዛል፡፡ በዚህም መካከል ሰዎች በበሽታው የመጠቃት ችግር ደርሶባቸዋል፡፡ የጉልበት መገጣጠሚያ ላይ የቁርጥማት ስሜት አለው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ ባለሙያዎችን የማሳሳትና የማዘናጋት ባህሪ አላቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ እየበዛና ቁጥሩ እየጨመረ ሲመጣ፣ ተመሳሳይ የበሽታ ምልክቶች አንድ ዓይነት ቦታ ላይ መታየት ሲጀምሩ የጤና ባለሙያዎችና የኅብረተሰብ ጤና ሠራተኞች በችግሩ ዙሪያ የመጠራጠር ሁኔታ ፈጠሩ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ከታዩ በኋላ ነው የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ወረርሽኙን ማረጋገጥ ወይም ለወረርሽኙ ምላሽ መስጠት የቻለው፡፡

ጥያቄ፡- ለወረርሽኙ ፈውስ የሚሆን መድኃኒት የለውም ተብሏል፡፡ ከዚህ አንፃር በበሽታው የተያዙ ሰዎች ዕጣ ፋንታቸው ምን ይሆን?

ዶ/ር በየነ፡- በሽታውን ወይም ቫይረሱን የሚገድል ወይም የሚያድን መድኃኒት አይኑር እንጂ በበሽታው የተያዙ ሰዎች መታከም ይችላሉ፡፡ እየታከሙም፣ እየዳኑም ያሉ ሰዎች አሉ፡፡ በሽታው ያለበት ወይም ቁርጥማት ያለበት ሰው በሚሰጡት መድኃኒቶች ከሕመሙ ሊፈወስ ይችላል፡፡ በሽታው ራሱን በራሱ የሚያጠፋ ነው፡፡ በሁሉም የጤና ተቋማት ሕክምናው ይሰጣል፡፡ ቅድመ ዝግጅት ሥራ አለመኖር፣ የመድኃኒት እጥረት ክፍተት ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ክፍተቶች ግን ተቀርፈዋል፡፡

ጥያቄ፡– የድሬዳዋ ነዋሪዎች የዝናብ ውኃ የሚያጠራቅሙት ለመጠጥ የሚውል ውኃ ከማጣት አንፃር ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት አለው?

ዶ/ር በየነ፡- ድሬዳዋ ላይ ሰዎች የዝናብ ውኃ የሚያጠራቅሙት በውኃ ዕጥረት ሳቢያ አይደለም፡፡ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በአብዛኛው የውኃ ዕጥረት የለም፡፡ ነገር ግን ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር ለልብስ ማጠቢያነትና ለሌሎች ንጽሕና መስጫዎች የመገልገል ልምድ አላቸው፡፡ ስለዚህ በበርሜሎችና ቁርጥራጭ ባልዲዎች ወይም ባገኙት የወዳደቁ ቁሳቁስ የማጠራቀም ልምድ አላቸው፡፡ የዝናብ ውኃ ማጠራቀም በራሱ ችግር የለውም፡፡ የተጠራቀመው ውኃ በትክክል ተከድኖ ከተቀመጠ ምንም ዓይነት ተግዳሮት አያመጣም፡፡ ችግር እየሆነ ያለው በበርሜል ወይም በተሰበሩ ዕቃዎች አጠራቅሞ ክፍት መተው ነው፡፡ ክፍተቱንም በመጠቀም ነፍሳቶች እንቁላላቸውን ይጥላሉ፡፡ ከዛ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ ይራባሉ፡፡ በበሽታ የተያዘ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ካሉ በንክሻ ደማቸውን በመውሰድ ወደ ሌሎች ሰዎች የማስተላለፍ መንገድ ይኖራል፡፡

ጥያቄ፡- የችኩንጉኒያ ወረርሽኝ አስመልክቶ ለኅብረተሰቡ የተሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት አልነበረም? ኅብረተሰቡ ትምህርቱን ለመቀበል የነበረው ፍላጎት እንዴት ይታያል?

ዶ/ር በየነ፡- ቤት ለቤት በተካሄደው የአሰሳ ዘመቻ ላይ ለማስተማር ሲሞከር ከኅብረተሰቡ በኩል ትምህርቱን ያለመቀበል ሁኔታ ይታይ ነበር፡፡ ተጠራቅሞ ክፍት የከረመውን የዝናብ ውኃ ድፉ ሲባል አለመድፋት ተስተውሏል፡፡ ይህም እንደተጠበቀ ሆኖ ለልብስ ማጠቢያ ማስቀመጫ የሚጠቀሙበትን የመኪና ጎማዎች እንዲሁም ሌሎች አላስፈላጊ  የውኃ መያዣ ዕቃዎች እንዲጥሉ ሲመከሩ ምክሩን ያለመቀበል አዝማሚያ ታይቶባቸዋል፡፡ ባለሙያዎች ለቁጥጥር ብቅ ባሉ ጊዜ የተጠራቀመውን የዝናብ ውኃ የመድፋት፣ ባለሙያው ዞር ሲል ደግሞ እንደገና የማጠራቀም ሁኔታ ተስተውሏል፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ ለበሽታው መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ትልቁና ዋናው ሥራ ትንኞች ላይ የሚከናወን ተግባር ነው፡፡ ከዚህም ግንዛቤ በመውሰድ ትንኞቹ የሚራቡበትን ቦታዎች የመለየት ሥራ ወዲያውኑ ተደርጓል፡፡

ጥያቄ፡- ኅብረተሰቡን የማንቃት ሥራ ተቋረጠ? ወይስ ቀጥሏል? በዚህ ዙሪያ የተወሰደው ዕርምጃ ምን እንደሚመስል ቢገልጹልን?

ዶ/ር በየነ፡- ኅብረተሰቡን የማንቃት ሥራና የፅዳት ዘመቻ በተጠናከረ መልኩ ተከናውኗል፡፡ ትንኞቹንም በማሳየት በሽታ አምጪ መሆናቸውን ኅብረተሰቡ እንዲረዳ ተደርጓል፡፡ ይህም የተከናወነው በኤፒዲዮሞሎጂ ባለሙያዎች ነው፡፡ በነገራችን ላይ ‹‹ኤፒዲዮሞሎጂ›› የነፍሳት ባህርያትን፣ አኗኗርና አረባብን የሚያጠና ሳይንስ ነው፡፡ ባለሙያዎቹ ይህንን ሥራ ያከናወኑት ሥፍራው ድረስ በመሄድ ትንኞቹ የተራቡበትን አካባቢ በመለየትና በሚያስከትሉት የጤና ጉዳቶች ዙሪያ ጥልቀት ያለው ምርምር ካካሄዱ በኋላ ነው፡፡

ጥያቄ፡- በቺኩንጉኒያ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ትክክል መሆን አለመሆኑ የሚጣራበት ሁኔታ አለ፡፡

ዶ/ር በየነ፡- በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ ትክክለኛነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ ምክንያቱም በሽታው በጥቂት ቀናት ውስጥ አይድንም፡፡ ስለሆነም ሰዎች ዛሬ ታክመውና የታዘዘላቸውን መድኃኒት ይዘው ወደ ቤታቸው ከሄዱ በኋላ እንደገና ወደ ጤና ተቋማት የመመለስ ሁኔታ ይታይባቸዋል፡፡ በግል ሕክምና ተቋም የታዩ ታካሚዎች እንደገና ወደ መንግሥት የሕክምና ተቋም የመሄድ፣ ከዚህም ሌላ በአንድ የጤና ተቋም ብቻ ከሁለትና ሦስት ቀናት በኋላ ተመልሶ የመምጣት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ በዚህም የተነሳ በተደጋጋሚ የመመዝገብና ሪፖርት የመደረግ አዝማሚያዎች ታይተዋል፡፡ ሆኖም በጥንቃቄ ሪፖርት እንዲደረግ ጥረት ተደርጓል፡፡

ጥያቄ፡- ድሬዳዋ ውስጥ በወረርሽኝ ሳቢያ አንዳንድ ድርጅቶች የሚሰጡትን አገልግሎት አቋርጠዋል ይባላል፡፡ ይህንን ጉዳይ እንዴት እያያችሁት ነው?

ዶ/ር በየነ፡- አገልግሎት ማቋረጣቸው ትክክል ነው፡፡ በሽታው የተፈጥሮ መገጣጠሚያዎችን የሚያውክና እንቅስቃሴን የሚገድብ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በዚህ በሽታ የተያዙ ሰዎች መንቀሳቀስ ስለሚያዳግታቸው የሚሰጡት አገልግሎት በዚያው ልክ ይቆማል ወይም ይቋረጣል፡፡ ሰዎቹ መገጣጠሚያ አካላቸውን ያማቸዋል ወይም ያብጥባቸዋል፡፡ ሲንቀሳቀሱ የተለየ የሰውነት ቅርጽ ይታይባቸዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ለትንኝ ንክሻ ከሚያጋልጡ ሁኔታዎች ራሱን መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ በማንኛውም ጊዜ ሙሉ ሰውነትን የሚሸፍን ልብስ መልበስ፣ የትንኝ መከላከያ ቅባት በቆዳ ላይ መቀባትና በሚተኛበት ጊዜ ሁሉ የአልጋ አጎበር በመጠቀም ራስን ከትንኝ ንክሻ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ሌላ ማንኛውንም ለትንኝ መራቢያ አመቺ የሆኑ ትቦዎች፣ የወዳደቁ ውኃ የሚቋጥሩ ጎማዎችና ሎሎች ዕቃዎችን ማስወገድ፣ በየቤቱ የሚገኝ የተጠራቀመ የዝናብ ውኃ በማፍሰስና ቤትንና አካባቢን በትንኝ መከላከያ ኬሚካል በባለሙያ በማሥረጨት ራስን መከላከል ግድ ይላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...

ከጎዳና ከማንሳት ራስን እስከማስቻል የሚዘልቀው ድጋፍ

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን...