ፌዴሬሽኑ ከጸረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በትብብር እሠራለሁ እያለ ነው
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና በክለቦች ይሁንታ አግኝቶ ሕግ ሆኖ ሥራ ላይ እንደሚውል ሲነገርለት የሰነበተው የተጨዋቾች የደመወዝ ጣሪያ መመርያና ስምምነት፣ በራሳቸው በክለቦቹ እየተጣሰ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ለጉዳዩ መድረኮችን በማመቻቸት ክለቦችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲመክሩበትና አቅጣጫ እንዲያስቀምጡ በማድረጉ ረገድ ትልቅ ድርሻ የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ፣ ድርጊቱን በተጨባጭ ፈጽሞ የተገኘ ክለብም ሆነ ተጫዋች በወንጀል ተጠያቂ የሚሆንበት አሠራር መዘጋጀቱን ይገልጻል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች የተጀመረው 50,000 ብር የደመወዝ ጣሪያ ወደ ከፍተኛውና ብሔራዊ ሊጉም በመውረድ የተጫዋቾችን የደመወዝ ጣሪያ ገደብ እንዲቀመጥለት ውሳኔ ላይ መደረሱ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ በውሳኔው መሠረት የክፍያው ጣሪያ ለከፍተኛ ሊግ 20,000 ብር፣ ለብሔራዊ ሊግ ደግሞ 5000 ብር መሆኑ ይፋ ሆኗል፡፡
በፕሪሚየር ሊግም ሆነ ከፍተኛና ብሔራዊ ሊግ የሚጫወቱ ተጨዋቾች ከ2012 የውድድር ዓመት ጀምሮ ክለቦች በተቀመጠው የክፍያ መጠን ከተጫዋቾች ጋር ውል እንዲገቡ፣ ይህንኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን እንዲያስፈጽም ከስምምነት መደረሱ የሚታወስ ነው፡፡
የተጨዋቾች የደመወዝ ጣሪያን በሚመለከት ውሳኔው በተጠቀሰው አግባብ እንዲሆን በተዘጋጁት ሁሉም መድረኮች የክለብ አስተዳዳሪዎችና አመራሮች የነበራቸው አቋምና ከሰሞኑ ከተጨዋቾች ዝውውር ጋር ተያይዞ ክለቦች እየሄዱበት ያለው እውነታ የተለየ መሆኑ መመሪያውን የ‹‹ይስሙላ›› እንዲሆን አድርጎታል የሚል ቅሬታ አስነስቷል፡፡
በዝውውር ገበያው የተጠመዱ ሁሉም ክለቦች የደመወዝ ጣሪያ መመርያውን በመጣስ ተጫዋቾችን የሚያዘዋውሩት በቀድሞ ዓይነት ሆኖ፣ ለፌዴሬሽኑ የሚያስገቡት የስምምነት ውል ግን በመመሪያው መሠረት እንደሆነና ይህም መንግሥት ከዘርፉ የሚያገኘውን የገቢ ግብር ታክስ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ስለመሆኑ ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ፣ የተጫዋቾችን የደመወዝ ጣሪያ በሚመለከት ሐሳቡ የመጣው ከራሳቸው ከክለቦቹ በመሆኑ መመርያውን ተግባራዊ ማድረግ የሚስችል የአሠራር ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ይገልጻል፡፡ በመሆኑም ከተደነገገው የደመወዝ ጣሪያ በላይ የሚከፍሉ ክለቦች ካሉ ከድርጊታቸው ተቆጥበው ውሳኔያቸውን እንዲያከብሩ፣ መንግሥትም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ግብር እንዲያገኝና ለዚህ ተብሎ ከተቋቋመው የገቢዎች ሚኒስቴርና ከፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በትብብር መሥራት ይችል ዘንድ ሥርዓት መዘርጋቱን ጭምር ያስረዳል፡፡
በደንቡና በመመሪያ ከተደነገገው የደመወዝ ጣሪያ ውጪ የሚከፍሉ ክለቦች ካሉና በዚህ ጉዳይ ተሳትፈው በተጨባጭ የሚደረስባቸው ክለቦች በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆኑ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሰጡዋቸው መግለጫዎች ማብራሪያ መስጠታቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
እንደ መግለጫዎቹ ይዘት ከሆነ፣ ‹‹የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ከተከፈተበት ጀምሮ እስከ አሁን ለፌዴሬሽኑ የደረሱት የስምምነት ውሎች በሙሉ መመሪያውን የተከተሉ ናቸው፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴርም ይህንኑ የክለቦችን የፋይናንስ የአሠራር ሥርዓት የሚፈትሽ ይሆናል፣ ለዚህ ተፈጻሚነት ሲባል በወንጀል የሚያስጠይቅ የሕግ ማዕቀፍ ተዘርግቷል፤›› ማለታቸውም ታውቋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች ችግሩ በእያንዳንዱ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ በቂ ዕውቀት ኖሯቸው ሥራውን ሊከውኑ የሚችሉበት ሥርዓት ባለመዘርጋቱ በየጊዜው መልክና ይዘታቸውን በሚቀያይሩ አለመግባባቶች እየተከሰቱ የሚባክኑ ወቅቶች መበርከታቸው ለስፖርቱ ወድቀት ዓይነተኛ መንስዔ ከሆነ ውሎ ማደሩን ያስረዳሉ፡፡
የሕግ ባለሙያዎቹ ምክንያቱን አስመልክቶ ሲያብራሩ፣ ሲጀመር የተጨዋቾች የደመወዝ ጣሪያ ምንም እንኳን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ባይኖርበትም ውሳኔው መሆንና መደረግ የነበረበት፣ ‹‹98 በመቶ የመንግሥት ቋት በሚጠይቀው የክለቦች በጀት ላይ የሚመለከተው ራሱ መንግሥት እንደመሆኑ የክለቡን በጀት መወሰን እየቻለ፣ ለተጨዋቾች የደመወዝ ጣሪያ መጨመር ዋና ተዋንያን ለሆኑት አመራሮች ውሳኔ እንዲያሳልፉ ማድረግ አግባብነቱ ግልጽነት እንዲጎድለው ያደርጋል፣ ውሳኔው የይስሙላ እንዲሆን የሆነውም ለዚህ ነው፤›› ይላሉ፡፡