በአፍሪካ በእግር ኳስ ደረጃቸው በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች ብሔራዊ ቡድኖች የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ አድርገው በደርሶ መልሱ ውጤት የሚቀናቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ 14 ቡድኖች ለዋናው ከተመደቡት 26 ቡድኖች ጋር እንዲጫወቱ ይደረጋል፡፡ እነዚህ ደግሞ እንደገና በአሥር ምድብ ውስጥ በሚካተተው የምድብ ድልድል ለመግባት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዚህ ታሪክ የሚያበቃውን ውጤት ለማስመዝገብ ረቡዕ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. የሌሶቶ አቻውን በባህር ዳር ስታዲየም ያስተናግዳል፡፡
በባህር ዳር የመጀመርያውን ጨዋታ የሚያደርጉት ኢትዮጵያና ሌሶቶ ሁለቱም በየአገሮቻቸው የውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች በሚሳተፉበት የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) በቅድመ ማጣሪያው ተጋጣሚዎቻቸውን ባሸነፉ ማግሥት የተገናኙ እንደመሆናቸው ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለቻን ዋንጫ የጅቡቲ አቻውን በጠባብ ውጤት አሸንፎ ለቀጣዩ ዙር የበቃው የኢትዮጵያ ቡድን ጨዋታውን በሜዳውና በደጋፊው ፊት ማድረጉ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ቅድመ ግምት አግኝቷል፡፡ ይሁንና ቡድኑ ጎሎችን ማስቆጠር ካልሆነ ጎል እንዳይቆጠርበት ጥንቃቄ አድርጎ ሊጫወት እንደሚገባውም ተመልክቷል፡፡
ዝግጅቱን ቀደም ብሎ በባህር ዳር የጀመረው የኢትዮጵያ ቡድን በግብጽ ሊግ የሚጫወቱትን ሽመልስ በቀለ፣ ኡመድ ኡኩሪና ጋቶች ፓኖም እንዲሁም በስዊዲን ሁለተኛ ሊግ የሚጫወተው ቢኒያም በላይን በቡድኑ ማካተቱ ታውቋል፡፡
‹‹አዞዎቹ›› በሚል ቅጽል ስያሜ የሚታወቁት ሌሶቶዎች በቅድመ ማጣሪያው የደቡብ አፍሪካ አቻቸውን አሸንፈው የመጡ ናቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካዊ ቴቦ ሴኖንግ የአዞዎቹ ዋና አሠልጣኝ ሆነው የተቀጠሩት ባለፈው ሳምንት ቢሆንም ካላቸው ልምድ በመነሳት ለዋሊያዎቹ ፈተና እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡