መንግሥት ወደ ግል እንዲዞሩ ከለያቸው 13 የስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ የበለጠ አዋጭ ይሆናል የተባለውን የስኳር ፋብሪካ ለመግዛት ቀድሞ አክሲዮን በመሸጥ ላይ የሚገኘው ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር፣ የሚፈለገውን ካፒታል ለማሟላት የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም እየሠራ መሆኑን ገለጸ፡፡
ይህንን አዋጭ ይሆናል የተባለውን የስኳር ፋብሪካ ግዥ ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ እስካሁን ባለው መረጃ በቀጥታ አክሲዮኖች ግዥ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን መሸጡንና ቃል ማስገባቱን አስታውቋል፡፡ በስኳር ኢንዱስትሪው ውስጥ ዕውቀት ያላቸው በስኳር ፋብሪካዎች ዙሪያ ያሉ 40 ሸሕ የሚገመቱ ዜጎችም ወደ 1.6 ቢሊዮን ብር የሚገመት ብድር እንዲያገኙና አክሲዮን እንዲገዙ ለማስቻል፣ ከአራት የተለያዩ ባንኮች ጋር ድርድር መደረጉን ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. የአክሲዮን ማኅበሩ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡
የአክሲዮን ማኅበሩ አመራሮች ስለአክሲዮን ኩባንያው ወቅታዊ እንቅስቃሴ በሰጡት ጋዜዜጣዊ መግለጫ፣ መንግሥት ለሽያጭ ያቀረባቸው የስኳር ፋብሪካዎችን ለመግዛት ያለውን ሰፊ ዕድል እንደሚጠቀሙ አስታውቀዋል፡፡
ከተለያዩ አራት የአገር ውስጥ ባንኮች ጋር በተደረገ ድርድር ብድር የሚገኝበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ቢተው ዓለሙ አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ ቢተው ገለጻ አክሲዮን ለሚገዙና በመተሐራና ወንጂ ፋብሪካ ዙሪያ ላሉ የፋብሪካ ዕውቀት ኖሯቸው አቅም ለሌላቸው ሰዎች ብድር ተሰጥቶ ባለአክሲዮን የሚሆኑበት ዕድል እንዲመቻች፣ 40 ሺሕ ለሚሆኑ ግለሰቦች ለእያንዳንዳቸው ሃያ ሺሕ ብር ብድር ለመፍቀድ ከባንኮቹ ጋር በተደረገ ድርድር ስምምነት ላይ በመደረሱ፣ ከዚህ የብድር ምንጭ ብቻ ከሁለት ባንኮች ወደ 1.6 ቢሊዮን ብር ሊገኝ እንደሚችል ታሳቢ ተደርጓል፡፡
አዋጭ ይሆናሉ የተባሉትን የስኳር ፋብሪካዎችን ለመግዛትም በቅድሚያ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ስኳር ፋብሪካ በመገንባት ከሚታወቀው የሆላንዱ ኤችቪኤ ኩባንያ ጋር ስምምነት መደረጉም ተጠቁሟል፡፡ በአገር ውስጥ ከሚሰበሰበው ካፒታል በተጨማሪ፣ ከዚህ ኩባንያ ጋር በመጣመር የስኳር ፋብሪካ ለመግዛት የሚያስችል ካፒታል ይሰበሰባል የሚል እምነት እንዳላቸው ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ያለው የአክሲዮን ሽያጭ አበረታች ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በአሁኑ ወቅት እየታየ ላለው የአክሲዮን ኩባንያዎች የአክሲዮን ሽያጭ መነቃቃት ኢትዮ ስኳር አስተዋጽኦ ማበርከቱን አመልክተዋል፡፡ የስኳር ፋብሪካ አዋጭነት ምንም ጥርጥር የሌለውና የተሻለ የሚተረፍበት በመሆኑ፣ ‹‹መንግሥት ፋብሪካዎቹን ለመሸጥ በሰጠው አጭር ጊዜ ውስጥ ካፒታሉን ለማሟላት አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን ዕድል መጠቀም አለብን፤›› ብለዋል፡፡
ሊገዙ ያሰቡትን የስኳር ፋብሪካ በጨረታ ተወዳድረው ባያሸንፉ ወይም ሌሎች የውጭ ኩባንያዎች ፋብሪካውን ለመግዛት ዕድል ቢያገኙ፣ የኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የሚፈልጉትን ፋብሪካ ለመገንባት ዕድል ያላቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ግዥው ባይሳካ እንኳን ሌላ አማራጭ ስለሚኖር በዚያ መሠረት የሚንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ በአማራጭነት የተያዘ ሲሆን፣ ይህም ባይሆን ሌላ የስኳር ፋብሪካ ለመገንባት ዕድል እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ በዋናነት በወንጂና በመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች ላይ ዓይኑን የጣለ መሆኑን፣ ፋብሪካዎቹን ለመግዛትና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት የሚያስችል ቁመና እንደሚኖር አመልክተዋል፡፡
የአክሲዮን ማኅበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ ጉርሙ (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ አክሲዮን ማኅበሩ ያሰባሰባቸው ባለሙያዎች ሥራውን በተገቢው መንገድ ለመሥራት ልምድ ያላቸውና ተጨማሪ ዕገዛ ለማግኘትም የውጭ ኩባንያ ይዘው መንቀሳቀሳቸው ግባቸውን ለማሳካት እንደሚረዳቸው አስታውቀዋል፡፡
የስኳር ኢንቨስትመንት አዋጭ ከመሆኑ አንፃር ብዙ ገዥዎች እየቀረቡ መሆናቸውን የጠቆሙት የአክሲዮን ማኅበሩ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከየትኛውም ዘርፍ የተሻለ ትርፍ የሚገኝበት በመሆኑ ባለው አጭር ጊዜ የሚፈለገውን አክሲዮን እናሟላለን ብለዋል፡፡ አሁን ባለው የመንግሥት ዕቅድ መሠረት እነዚህ ፋብሪካዎች በስድስት ወራት ውስጥ መሸጥ መሆኑንም አቶ ለማ ጠቁመዋል፡፡
እስካሁን የስኳር ፋብሪካዎቹን ለመግዛት ፍላጎት ያላቸው አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ኩባንያዎች መሆናቸው ሲታወቅ፣ ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር ለመሸጥ ያሰባቸው አክሲዮኖች ዋጋ ሦስት ቢሊዮን ብር ነው ተብሏል፡፡