Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የዋጋ ቅናሽ ብርቅ የሆነበት ገበያ

ወደ ገበያ ሄደው የሚፈልጉትን ዕቃ ለመሸመት እየከበደ ነው፡፡ ዋጋ ጨመረ እንጂ ቀነሰ የሚል ወሬ መስማት ብርቅ እየሆነ መጥቷል፡፡ አንዱን ዕቃ ከአንድ ወር በፊት በገዙበት ዋጋ አሁን እገዛለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡

መሠረታዊ የሚባሉ ዕቃዎች ዋጋ አልቀመስ እያሉ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር ዋጋ መቆለል የተለመደ ሆኗል፡፡ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ልዩነት ሲፈጠር ዋጋ መጨመሩ አይቀሬ ቢሆንም፣ በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ግን በተለየ ሁኔታ እጥረት የማይታይባቸው ምርቶች ሳይቀሩ ዋጋ እየተቆለለባቸው ሸማቹን እያማረሩት ነው፡፡

ችግሩ እየባሰ ከመሄዱም በላይ፣ የችግሩን መንስዔ በማጣራት ዕርምት ወይም ዕርምጃ ያለ መወሰዱ ሁኔታውን አሳሳቢ እያደረገው ይገኛል፡፡

የዋጋ ግሽበት በዚህ ወቅት አገራዊ ችግር ስለመሆኑ በሁሉም ዘንድ ግንዛቤ የተወሰደ ከመሆኑ አንፃር፣ ለመፍትሔው ከልብ እየተደከመ ነው ለማለት እየከበደ ነው፡፡ ገበያው እየነገረን ያለው የዋጋ ግሽበቱን በመቆጣጠር ሸማቹን ለመታደግ አለመቻሉ ነው፡፡ በተለይ የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ለማሻሻል እየተከናወነ ያለው ሪፎርም መዘግየቱ፣ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በፓርላማ ተገኝተው የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል ያቋቋሙት አንድ ኮሚቴ፣ ችግሩን በማጥናት መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ቢያሳውቁም፣ ከዚያ በኋላ ኮሚቴው ምን እየሠራ እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ኮሚቴውም ተወደደ ማለት ነው?

በእርግጥ ከአገራችን የግብይት ሥርዓት አንፃር ገበያው ባልተገባ ዋጋ እንዲጋጋል በማድረጉ ረገድ ለራስ ብቻ ያደሩ፣ ለአገር ደንታ የሌላቸውና የሸማቹን ምሬት ከቁብ የማይቆጥሩ አንዳንድ ነጋዴዎችና ደላሎች የሚፈጸም መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የግብይት ሥርዓታችን ጤንነት ይጎድለዋል፡፡

አሁንም እንቆቅልሽ እየሆነ የመጣው የዋጋ ግሽበት በምግብ ሸቀጦች፣ በአላቂ ዕቃዎች፣ ከዚያም አልፎ በተለያዩ የመገልገያ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ላይ ሳይቀር የሚታይ ሆኗል፡፡ ስለዚህ የዋጋ ግሽበቱ በየትኛውም ምርት ላይ እየታየ መምጣቱ ጉዳዩን በልዩ ትኩረት ማየት እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ አሁን በሚታየው የዋጋ ግሽበት የቱንም ያህል ስግብግብ በምንላቸው ነጋዴዎች ላይ ጣታችንን ብንቀስርም፣ የመንግሥትም አስተዋጽኦ ቀላል ነው ሊባል አይችልም፡፡

እንደ ምሳሌ ከሰሞኑ የሰማነውን አንድ ዜና ማስታወስ ይቻላል፡፡ በስንት መከራ በተገኘ ዶላር የተገዛ ስንዴ ለወራት የሚያነሳው ጠፍቶ ተከማችቷል መባሉ፣ የኑሮ ውድነት ለወጠረው ሸማች መልካም ዜና አይሆንም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለው ክስተትም የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በአግባቡ ኃላፊነትን ባለመወጣት የሚፈጠረውን መዘዝ እንዲህ ባለው ድርጊትም መመዘን የሚያስችል ነው፡፡

ሌላው ጉዳይ የዋጋ ግሽበቱ አገሪቱ ካላት የውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገኘ በሚባልበት በዚህ ወቅት የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ስላልተቻለ፣ ኅብረተሰቡ በቅርብ ሊያገኝ የሚገባውን ምርት እያገኘ አለመሆኑን እንረዳለን፡፡ ወቅታዊውን አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከተመለከትንም ከወር ወር እየጨመረ መሄድ ማቆሚያው የት ላይ ሊሆን ነው? የሚለው ጥያቄ እያስነሳ በመሆኑ መንግሥት እየሰፋ የሄደውን የዋጋ ዕድገት፣ ከዚህም በላይ እንዳይሄድ የመቆጣጠር ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡

ሌላው ቢቀር መሠረታዊ የሚባሉ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋን ሊቆጣጠር የሚችልበትን አሠራር በመዘርጋት የሕዝቡን ምሬት መቀነስ ግድ ይለዋል፡፡ በተለይ ታች ያለው ሸማች ከዚህም በላይ እንዳይጎዳ የሚያደርግ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በወቅቱ የበዓል ዋዜማ ነውና ለበዓል የሚፈለጉ መሠረታዊ ምርቶች በአግባቡ እንዲቀርቡለት በማድረግ ሊታደገው ይገባል፡፡ በጥቅሉ ግን በተለይ በዚህ ዓመት የታየው የዋጋ ግሽበት ከተለመደው በተለየ እየሆነ ከመምጣቱ አንፃር፣ ጉዳዩ በልዩ ሁኔታ መታየት እንዳለበት የሚያመለክት ነው፡፡

ስለዚህ ከጊዜያዊ መፍትሔዎቹ ባሻገር ለዘለቄታውስ ምን ብናደርግ ይሻላል ብሎ ማሰብ ተገቢ ይሆናል፡፡ በተለይ የዋጋ ግሽበትን ያረጋጋል ተብሎ እየተሠራ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም፣ እየተሠራ ነው ከሚል መልዕክት ባሻገር ሥራው በቶሎ አልቆ መተግበር ይኖርበታል፡፡ የዋጋ ግሽበት መንስዔዎችን ካነሳን ዘንዳ ራሱ ሸማቹም የራሱ ኃላፊነት እንዳለበት መታወቅ ይገባል፡፡ ባለው አቅም ለሸማቹ የሚደርሱ አንዳንድ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን በአግባቡ መጠቀም ሲገባ፣ አትርፎ ለነጋዴዎች በመሸጥ የሚፈጸመው ድርጊት በብዙ የሸማች ማኅበራት መደብሮች ደጃፍ እየተመለከትን ነው፡፡ ይህ ድርጊት ከነጋዴው ወደ ሸማቹ ሲመጣ ዋጋው ተቆልሎ በመሆኑ የዋጋ ግሽበቱን ሊያባብስ የሚችል በመሆኑ፣ ጨዋ ሸማች መሆንም ችግሩን ለማቃለል ሌላ መፍትሔ መሆኑን መግለጽ ያስፈልጋል፡፡

የገበያ ሥርዓቱም በአግባቡ እንዲመራ ቁጥጥርና ክትትል ማድረጉም ችግሩን ሊያረግብ ስለሚችል፣ በአዲሱ ዓመት በብርቱ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ተደርጎ ሸማቹን በሚታደጉ አሠራሮች ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት