Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱሪዝም ዒላማው ያደረገው ግዙፉ የቱርክ ሆስፒታል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቱርክ ከሚገኙ የሕክምና ተቋማት በቀዳሚነቱ የሚጠቀሰውና በአውሮፓም ሆነ በተቀረው ዓለም ከሚገኙ የሕክምና አገልግሎት መስጫዎች አንዱ የሆነው አጂባደም ሆስፒታል ግሩፕ፣ በአፍሪካ ተደራሽ የሚሆንበትን አሠራር በመዘርጋት በሜዲካል ቱሪዝም ቅድሚያ ከሚሰጣቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነችና በመጪው ዓመትም ወኪል ጽሕፈት ቤቱን በአዲስ አበባ እንደሚከፍት ይፋ አድርጓል፡፡

ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በመጋበዝ በቱርክ የንግድ ከተማ በሆነችው ኢስታንቡል የሚገኙ ተቋማቱን ያስጎበኘው አጂባደም ግሩፕ፣ በየዓመቱ ከ5.5 ሚሊዮን ያላነሱ ሕሙማንን በማስተናገድ ላይ የሚገኝ ግዙፍ የሕክምና ተቋም ለመሆን ስለቻለባቸውና ስለአገልግሎቶቹ አስዋውቋል፡፡ በአብዛኛው ሁሉንም ዓይነት የሕክምና አገልግሎቶችና ክብካቤዎች የሚሰጠው ይህ የግል ሆስፒታል፣ ከቱርካውያን ባሻገር ከ96 አገሮች የተውጣጡ 40 ሺሕ የውጭ ታካሚዎችን በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝ የሆስፒታሉ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ሙስጠፋ ካራዲድ ገልጸዋል፡፡ በተለይም የባልካን አገሮች፣ የመካከለኛው ምሥራቅ፣ እንዲሁም በመጠኑም የአፍሪካ፣ የላቲንና የሰሜን አሜሪካ በተለይም የአሜሪካ ታካሚዎች በሆስፒታሉ ሕክምናቸውን እንደሚከታተሉ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ብቻ 5.5 ሚሊዮን ሕሙማንን በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ባደረገበት ወቅት 139 ሺሕ የቀዶ ጥገና ሕክምና፣ 408 የኩላሊት ንቅለ ተከላ፣ 189 የጉበት ንቅለ ተከላ፣ እንዲሁም 380 የአጥንት መቅኒ ንቅለ ተከላ ሕክምናዎችን መስጠቱ ተብራርቷል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም የሕክምና አገለግሎቶቹ የተነሳም ከ800 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገቢ ማስገኘቱ ተገልጿል፡፡ ግዙፉና ዘመናዊው አጂባደም ሆስፒታል፣ እንደ ‹‹ጋማ›› ወይም ‹‹ሳይበር ናይፍ››፣ ዳቪንቺ ኤችኤስ የተባሉ የሕክምና መስጫ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የካንሰር ሕሙማንን በተለይም የጭንቅላት ዕጢዎችን፣ የጡትና የማህፀን ካንሰርን ጨምሮ በርካታ ቀዶ ጥገና የሚጠይቁ ሕክምናዎችን ያለ ቀዶ ጥገና ለማከም የሚያስችሉ ስለመሆናቸው፣ ሚስተር ካራዲድን ጨምሮ የሆስፒታሉ ሐኪሞች አስረድቷል፡፡

ከ23 ሺሕ በላይ ሠራተኞችን ያቀፈው አጂባደም በፀጉር ንቅለ ተከላ ሕክምናውም በአውሮፓ ሁለተኛው ግዙፍ ተቋም ለመሆን እንደበቃ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሕክምናውን ያገኙና በአብዛኛው ራሰ በረሃ የነበሩ ሰዎች ጉብኝት በተደረገው አልቱኒዛደና ማስላክ በተሰኙ የአጂባደም ሆስፒታሎች አካባቢ በብዛት ይታያሉ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሆስፒታሎች በአጂባደም ሥር ከሚገኙ 21 ሆስፒታሎች ትልልቆቹ ሲሆኑ፣ እያንዳንዳቸው ከ250 በላይ አልጋዎች ያሏቸው ስለመሆናቸውም ተብራርቷል፡፡ ተኝተው ለሚታከሙ ሕሙማን የሚሰጡት አገልግሎቶችም በሆቴል ደረጃ ከሚሰጡ አገልግሎቶች ጋር ተመሳሳይ ሲሆኑ፣ እንደ ታካሚው አቅምና ማንነት ማለትም ታዋቂ ሰው፣ ባለሥልጣን፣ ወዘተ. አገልግሎት የሚሰጥባቸው ኪንግ ስዊትስ፣ ቪአይፒ ስዊትስ፣ ቢ ሌቨል ስዊትስና መበደኛ የአልጋ ክፍሎችን ያካትታል፡፡

በሩቅ ምሥራቁ ኢይኤችኤች ሄልዝቻር ቤራንድ ከተሰኘው ግዙፍ ኩባንያ ጋር ከተጣመረበት እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ፣ በተለይ በቴክኖሎጂ ረገድ በርካታ ለውጦችን እያካሄደ እንደመጣም የሆስፒታሉ ተጠሪዎች ይገልጻሉ፡፡ አይማን ዩጂ በሆስፒታሉ የዓለም አቀፍ ሽያጭ ክፍል የኮሚዩኒኬሽንስ ስፔሺያሊስት ናቸው፡፡ ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ከሚጠቀምባቸው ሶፍትዌሮች መካከል የመድኃኒት አገልግሎትና የመድኃኒት አሰጣጥን በዲጂታል ዘዴ የሚቆጣጠረው ‹‹ኤስቶር›› የተሰኘውንና ጠቅላላ የተቋሙን እንቅስቃሴ የሚመራውን ‹‹ሰርብራል ፕላስ›› የተሰኘ ሶፍትዌር በራሱ ባለሙያዎች በመፍጠር፣ ከራሱ አልፎ ለውጭ ተቋማትም እየሸጠ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ‹‹ኤስቶር›› የተሰኘው የዲጂታል መድኃኒት አስተዳደር ሥርዓት፣ ሐኪም ያዘዘው መድኃኒት ታካሚውን በሚንከባከቡ ነርሶች በኩል ብቻ በጣት አሸራቸው የሚከፈት ማስቀማጫ ያለው ሲሆን፣ የተሳሳተ መድኃኒት እንዳይሰጡ የሚከላከልና ከሚያስፈልገው መድኃኒት ዓይነትና ብዛት በቀር ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖራቸው የሚያስችል የቁጥጥርና የአስተዳደር ሥርዓት የተገነባበት ነው፡፡

ሆስፒታሉ በቅርቡ ከኮትዲቯ ጤና ሚኒስቴር ጋር ባደረገው ስምምት መሠረት ‹‹ሰረብራል ፕላስ›› የተሰኘውን ሶፍትዌር፣ ለዚሁ ሥራ በመንግሥት ሆስፒታሎች የሚያገለግሉ ባለሙያዎችን በማሠልጠን ሶፍተዌሩን ከሙሉ አገለግሎቶቹ ጋር ለማቅረብ መስማማቱን ሚስ ዩጂ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በምትኩም አራት የኮትዲቯር ተማሪዎችን ሙሉ የትምህርት ወጪ በመሸፈን በአጂባደም የሕክምና ዩኒቨርሲቲ ተቀብሎ ለማስተማር መስማማቱን አክለዋል፡፡ እንዲህ ያሉትን አገልግሎቶች በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም የማስፋፋት ፍላጎት እንዳለው ገልጸው፣ መንግሥታት ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ ግንኙነት ከሆስፒታሉ ጋር መመሥረት ቢችሉ ለማገዝ፣ የዕውቀትና የቴክሎጂ ልውውጥና ሽግግር ለማድረግ ፍላጎት እንዳለም አብራርተዋል፡፡ በሕክምና ባለሙያዎች መካከልም የመረጃና የልምድ ልውውጥ፣ የፌሎሺፕና በሕክምና አሰጣጥ ሒደት ወቅት በምልከታ ልምድ የሚቀስሙበትን ዕድል እንደሚያመቻችም የሆስፒታሉ ሐኪሞች ገልጸዋል፡፡

መጠሪያውን ከኢስታንቡል መንደሮች አንዱ ከሆነውና አጂባደም ከተሰኘው የከተማዋ ክፍል የተዋሰው አጂባደም ሆስፒታል ግሩፕ በመላው ቱርክ ካሉት ባሻገር በኔዘርላንድስ፣ በቡልጋሪያ፣ በቤልጂየም፣ በሜቄዶንያ በጠቅላላው 21 ሆስፒታሎችን ያስተዳድራል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም 16 የተመላላሽ ሕክምና መስጫ ማዕከላትና 16 የጤና ክብካቤ ማዕከላት ሲኖሩት፣ የሕፃናትና የአዋቂዎች የልብ ሕክምናና ቀዶ ጥገና ሕክምና ይሰጥባቸዋል፡፡ 13 የመካንነት ሕክምና መስጫ ማዕከላት፣ የቀዶ ጥገና፣ የራዲዮና የኬሞቴራፒ ሕክምና የሚሰጥባቸው 11 የካንሰር ማዕከላት፣ የጉበት፣ የኩላሉትና የመቅኒ ንቅለ ተከላ ሕክምና የሚሰጥባቸው አሥር የሰውነት ክፍሎችና የኅብረ ህዋሳት ንቅለ ተከላ ሕክምና ማዕከላትን ያካተተው ይህ ሆስፒታል፣ በተጨማሪም ዘጠኝ የኅብለ ሰረሰርና የጭንቅላት ውስጥ ወይም የኒውሮ ሰርጀሪ ቀዶ ጥገና ሕክምና ማዕከላት፣ ስድስት በሮቦት ታጋዝው ሕክምና የሚሰጡ የቀዶ ጥገና ማዕከላት፣ እንዲሁም አንድ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ ተቋም (ፊፋ) ዕውቅና ያገኘ የስፖርት ሕክምና ማዕከል በማስተዳደር ይዞታዎቹንና የአገልግሎት ሥርጭቶቹን እያስፋፋ ይገኛል፡፡ ውድና ምናልባልትም ከ30 ሚሊዮን እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር እንደሚጠይቅ የሚነገርለትን ‹‹ፕሮቶን›› የተሰኘ የሕክምና መስጫ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ ወደ ሕክምና መስጫዎቹ ለማምጣት ማቀዱም ታውቋል፡፡

በእንዲህ ያለ ደረጃ እየተስፋፋ የሚገኘው ይህ የቱርክ ሆስፒታል፣ በአፍሪካ ትኩረቱን ማድረግ እንደሚፈልግና በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከጥቂት አገሮች በተለይም ከኬንያ፣ ከጂቡቲ፣ ከሊቢያ፣ ከአልጄሪያና ከሌሎችም አገሮች ሕሙማንን እየተቀበለ ማስተናገድ መጀመሩን በማስመልከት፣ ይበልጥ ተደራሽ የሚሆንባቸውን መንገዶች ለመፍጠር እንቅስቃሴዎች እያካሄደ ነው ሲሉ ሚስተር ሙስጠፋ ገልጸዋል፡፡ እስካሁንም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ስምምነት መፈጸሙን፣ ከመንግሥትና ከግል ሆስፒታሎች ጋርም ንግግር መጀመሩን፣ ሕሙማንን መቀበል ብቻም ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ የሕክምና አሰጣጥ ሒደት በተለይም በቴሪሼሪ ሕክምና መስክ ድጋፍ ማድረግ እንደሚፈልግ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሕክምና መስክ ብቻ ያተኮሩ የትምህርት ዘርፎችን በመምረጥ፣ ቱርካውያንና የሌሎች አገሮች ተማሪዎችን በማካተት 4,000 ተማሪዎችን የሚያስተናግደው አጂባደም ዩኒቨርሲቲም በሕክምናው መስክ መሠልጠን ለሚፈልጉ ወጣቶች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች እንዳስታወቁት፣ እ.ኤ.አ. በ2007 በአጂባደም ፋውንዴሽን አማካይነት ሲመሠረት ዋና ዓላማው ለሕክምናው መስክ ተተኪዎችን ማፍራትና አቅም ያላቸውን ብቁ ባለሙያዎችን ቁጥር ማብዛት ነው፡፡ በመሆኑም ከሁለተኛው ዓመት ጀምሮ ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት ይከታተላሉ፡፡ ሁሉንም የሕክምና ማሽኖችና ቴክሎጂዎች እየተጠቀሙ በገሃዱ ዓለም እንደሚካሄደው የሕክምና አሰጣጥ ሥርዓት መሠረት ትምህርት ይከታተላሉ፡፡ በአውሮፓ ዕውቅና በተሰጠው የሲሙሌሽን ማስተማር ሥልት የታገዙ የቀዶ ጥገናና ሌሎችም ውስብስብ የሕክምና ሒደቶችን የሚጠይቁ፣ የራሳቸውን ምርምር የሚያከናውኑባቸውና ልምዶችን የሚቀስሙባቸው ማዕከላትም በዩኒቨርሲቲው ይገኛሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከ60 በላይ የምርምር ሥራዎችን እየካሄደ እንደሚገኝ ሲያስታውቅ፣ በተለይም በሕክምና ሥራ ፈጠራ መስክ አዳዲስ ሐሳብ አፍላቂ ጀማሪዎችን የሚደግፍበት፣ ማንኛውም የኢስታንቡል ወጣት መሳተፍ የሚችልበት ማዕከልም አለው፡፡

በዚህ ማዕከል 118 የፈጠራ ሐሳቦች ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ በተለይም ማንኮራፋትን የሚከላከል አነስተኛ መሣሪያ የፈለሰፉ፣ በአልጋ የተኙ ሕሙማን በሰውነታቸው ላይ የሚወጣውን ቁስለት ቀድሞ ምልክቶቹን በመጠቆም ሕሙማኑ ጉዳት ሳይደርስባቸው በፊት ሕክምና እንዲያገኙ የሚያስችሉና ሌሎችም ከሕክምናው መስክ ጋር ተያያዥ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎች የሚደገፉበት ማዕከል የዩኒቨርሲቲው መገለጫዎች ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1991 የተመሠረተው አጂባደም ሆስፒታል ግሩፕ ዛሬ በአውሮፓ ከመንገሡ በፊት፣ በአንዲት አነስተኛ ክሊኒክ ውስጥ ለቤተሰብ አባላት ዝቅተኛ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ በመሥራቹና በአሁኑ ወቅት በቦርድ ሊቀመንበርነት በሚመሩት በመህመት ዓሊ አይዲንላር የተቋቋመ ነው፡፡

ቆየት ያሉ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ የውጭ ምንዛሪ ለውጭ ሕክምና ወጪ ታደርጋለች፡፡ የውጭ ሕክምና መዳረሻ ከሆኑት መካከል ህንድና ታይላንድ ሰፊውን ድርሻ ይዘዋል፡፡ ቱርክም እነዚህን አገሮች ለመቀላቀል ወይም አብዛኛውን ድርሻ ወደ ቱርክ እንዲያዘነብል ለማድረግ ፈልጋለች፡፡ በአገሪቱ ከአሥር ዓመታት በፊት ከነበረው ሁኔታ አኳያ አብዛኛው የቱርክ ባለሥልጣናትና ከበርቴዎች ለሕክምና ወደ ውጭ በተለይም ወደ አሜሪካ ያቀኑ ነበር፡፡ አሁን ይህ ተለውጦ አብዛኛውን ሕክምና የሚከታተሉት በአገራቸው ውስጥ ነው፡፡ ይህም ማለት አብዛኛው በሽታና ሕመም በአገራቸው ማከም የሚችሉባቸውን ልምዶች፣ ቴክኖሎጂዎችና ብቃቶች በማዳበራቸውና ይህም በተጠቃሚዎቹ ዘንድ በመረጋገጡ ወደ ውጭ ሄዶ መታከም እየቀረ መጥቷል፡፡

በኢትዮጵያም የቴርሸሪ ሕክምና የሚሰጡ ማዕከላትን ለማቋቋም አንዴ በመንግሥት ሌላ ጊዜም በግለሰቦች ስብስብና በኩባንያዎች እየተሞረከ እስካሁን ይህ ነው የሚባል ውጤት አልታየበትም፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል የማድረግ ፍላጎትም ዝግጅትም እንዳለ በመንግሥት ተደጋግሞ ሲነገር ይደመጣል፡፡

በብርሃኑ ፈቃደ፣ ኢስታንቡል ቱርክ

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች