በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የተለዩ የሚባሉ ክስተቶችን ያስተናገደ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ማሳያ ተብለው ከሚጠቀሱት ክስተቶች መካከል፣ ከስምንት ከዓመታት በኋላ ስምንት ያህል አዳዲስ ባንኮች ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል ዝግጅት ያደረጉበት መሆኑ ነው፡፡
በምሥረታ ሒደት ላይ ከሚገኙት ባንኮች መካከል አንዱ ደግሞ እስካሁን በኢንዱትሪው ውስጥ በግል ኩባንያ ደረጃ ያልተሞከረ፣ ግን መሠረታዊ የሚባለውን የአገሪቱን ችግር በመገንዘብ በቤቶች ግንባታና ተያያዥ ኢንቨስትመንቶች ላይ ስፔሻላይዝድ ያደረገ ባንክ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡
‹‹ጎህ የቤቶች ባንክ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ በምሥረታ ላይ የሚገኘው ይህ ባንክ፣ በሌላ የተለየ ገጽታ ባለው አደረጃጀት ብቅ ማለት ችሏል፡፡ ባንኩን ለማቋቋም በመሥራችነት ከተካተቱ አሥር አባላት ውስጥ አምስቱ፣ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የግልና የመንግሥት ባንኮችን በፕሬዚዳንት በማገልገል የሚታወቁ መሆናቸው ነው፡፡
የዚህን ፕሮጀክት ሐሳብ በማፍለቅ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት የቀድሞ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ፣ ከዚያም በኋላ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ጌታሁን ናና ናቸው፡፡
ሐሳቡን በመቀበል ባንኩን ለማቋቋም በአደራጅነት የተቀላቀሉት በኢንዱስትሪው ውስጥ ረዥም ልምድ ያላቸው አራቱ የባንክ ባለሙያዎች ደግሞ የቀድሞ የንብ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አመርጋ ካሳ፣ የቀድሞ የወጋገን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አርዓያ ገብረ እግዚአብሔር፣ የቀድሞ የቡና ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፋንታዬና የቀድሞ የእናት ባንክ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ፋሲካ ከበደ ናቸው፡፡ ባንኩ ከቤት ግንባታ ጋር በተያያዘ የፋይናንስ አቅርቦት የሚሰጥ በመሆኑ ቀሪዎቹ አምስቱም መሥራቾች፣ ከዚሁ ሥራ ጋር የተገናኘ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ናቸው ተብሏል፡፡
የባንኩን አደረጃጀት የሚመለከተው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ የጊፍት ሪል ስቴት መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብረ ኢየሱስ ኢጋታ ከመሥራቾቹ አንዱ ናቸው፡፡ በተለያዩ ባንኮች በሕግ ባለሙያነት ያገለገሉት አቶ ከፈኒ ጉርሙ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና አማካሪ ውብሸት ዥቅአለ (ዶ/ር) እና የፋይናንስና የኢንሹራንስ ባለሙያው አቶ ዮሴፍ አሰፋ ከአሥሩ አደራጆች ውስጥ ስማቸው ተካቷል፡፡
እንዲህ ያለውን ስብጥር ይዞ ለመነሳት የተፈለገው የቤት ጉዳይ መሠረታዊ የሚባል በመሆኑ፣ በኃላፊነት ለመሥራት ታስቦ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡ እንደ አቶ ጌታሁን ገለጻ፣ በሙያው ረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸው ሰዎች ለአገርና ለወገን አንድ አስተዋጽኦ ማበርከት አለብን በሚል መነሻነት በተለየ የባንክ አገልግሎት ዜጎችን ለማገልገል በማሰብ የተጀመረ ነው፡፡
ለቤቶች ግንባታና ተያያዥ የሆኑ የባንክ አገልግሎቶች የሚሰጥ ባንክ ለማቋቋም ሲነሱ ከመንግሥትም ሆነ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ከተባሉ አካላት ጋር ባገኙት ግብረ መልስ፣ ‹‹በዚህ ዘርፍ የሚከናወነው ሥራ አዋጭ መሆኑን ልንገነዘብ ችለናል፤›› ብለዋል፡፡ በተናጠል በተደረጉ ውይይቶች ብቻ ሳይሆን በተደረገውም ጥናት ቤቶችን የተመለከተው ባንክ ሰፊ ገበያ ያለው መሆኑን በመገንዘባቸው፣ ባንኩን ለማቋቋም ወደሚያስችል እንቅስቃሴ ተገብቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም አክሲዮን ለመሸጥ ፈቃድ ከሰጠ ወዲህ፣ የአክሲዮን ሽያጭ ውስጥ መግባታቸውን የጠቆሙት አቶ ጌታሁን፣ ባንኩ በተፈረመ አንድ ቢሊዮን ብር ካፒታልና በ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል፡፡
የቤቶች ባንክ መቋቋም አስፈላጊነትን በተመለከተም፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን ተከትሎ ለሚመጣው የቤት ፍላጎት እንዲህ ያሉ ባንኮች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ የአገሪቱ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከስድስት ሺሕ ብር ወደ ስምንት ሺሕ ብር ከፍ ስለማለቱ የሚጠቁመው የአደራጆቹ ጥናት፣ የደሃ ሰዎች ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2011 እና 2017 መካከል ከ39 ወደ 22 በመቶ ዝቅ ሲል፣ በከተሞች የሚኖረው ሕዝብ ብዛት ደግሞ ከ16 ወደ 20 በመቶ ከፍ ማለቱን ከላይ የተጠቀሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፖርት እንደሚያመለክትም ይጠቁማል፡፡ ይህ ዕድገት ቀጣይነት እንደሚኖረው የዓለም የገንዘብ ድርጅትም ሆነ በመንግሥት ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
በሌላ በኩል የአገሪቱ ሕዝብ ብዛት በየዓመቱ በ2.5 በመቶ እያደገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቤቶች ፍላጎት በከተሞች በፍጥነት እንዲያድግና ለቤቶች ግንባታ የተለየ ባንክ መኖሩ ለቀጣዩ ትውልድ ተስፋ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች የመኖሪያ ቤት ችግር እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳዩ መረጃዎች በመኖራቸው፣ ለወደፊቱም ይህ ፍላጎት እያደገ እንደሚመጣ ስለሚጠበቅ እንዲህ ያሉ ባንኮች ማቋቋም የግድ እንደሆነ አቶ ጌታሁን ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የተደረገው ግምት እንደሚያመለክተው፣ በሕዝብ ቁጥር መጨመርና ያረጁ ቤቶችን ለመተካት በዓመት እስከ አንድ መቶ ሺሕ ቤቶች መገንባት እንደሚኖርባቸው ነው፡፡ እንዲህ መሰል ባንክ በማቋቋም ለቤት ግንባታ መሠረት መጣል ግድ ነው ተብሏል፡፡
የመኖሪያ ቤት እጥረትና ችግር አሁን እየተደረገ ባለው የመንግሥትና የግል ተቋማት እንቅስቃሴ ብቻ የሚፈታ ያለመሆኑን የሚያትተው የአደራጆች ጥናት፣ ችግሩን ለማቃለል የቤቶችን ግንባታ ማስፋፋት የግድ ይላል፡፡ ነገር ግን ለዚህ የሚሆን ፋይናንስ በአገሪቱ በሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት በበቂ ሁኔታ እየቀረበ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ለኮንስትራክሽን ዘርፍ (የቤቶች ግንባታን ጨምሮ) በ2009 ዓ.ም. የተሰጠው የብድር መጠን ከጠቅላላው ብድር ውስጥ አሥር በመቶ ብቻ መሆኑን የጎህ ቤቶች ባንክ ጥናት ያመለክታል፡፡ ከዚህ ውስጥ የቤቶች ግንባታ ዘርፍ ድርሻ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱንም ያሳያል፡፡ ይህም የቤቶች ግንባታን በሚመለከት ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን፣ ክፍተቱን ለማጥበብም ፋይናንስ ላይ የሚያተኩር በአገሪቱ ልዩ የሆነ ባንክ ለማቋቋም እንዲህ ያሉት እውነታዎች እንዳበረታቷቸው ከአደራጆቹ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
ለቤቶች ግንባታ ዘርፍ የባንክ አስፈላጊነትን በተመለከተ በዝርዝር በቀረበው ተጨማሪ መረጃ፣ አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተደራሽነት እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑ አንፃር፣ ባንኩ መቋቋሙ ለኢንዱስትሪውም አጋዥ ነው ተብሏል፡፡ የሚመሠረተው ባንክ ካሉት ባንኮች በዓይነቱ የተለየና ከቤቶችና ቁጠባ ባንክ በኋላ የመጀመርያው ፋይናንስ ላይ የሚያተኩር የግል ባንክ መሆኑ አንዱ ሲሆን፣ ትርፋማ፣ አዋጭና አስተማማኝ እንደሆነ በጥናት መረጋገጡን ከአቶ ጌታሁን ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የባንኩን ዓላማ በዝርዝር የሚያመለክተው መረጃ ደግሞ ዋና ዓላማው በከተሞች የቤቶች ግንባታ፣ ዕደሳ፣ ማሻሻያና ግዥ ፋይናንስ ማድረግና ለባንኩ ባለቤቶች ላቅ ያለ ትርፍ ማስገኘት የሚለው በቀዳሚነት ተቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህንን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚያግዙ የመድንና የኮንስትራክሽን እህት ኩባንያዎችን የማቋቋም ራዕይ ያለው እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
ባንኩ በቤቶች ግንባታ ፋይናንስ ላይ ያተኩር እንጂ መደበኛ የባንክ አገልግሎቶችን ይሰጣል ተብሏል፡፡ ተቀማጭ ገንዘብ ከሕዝብና ከገበያ በተለያዩ መንገዶች ማሰባሰብ፣ የተሰበሰበውን ገንዘብ በዋናነት እንደ ሁኔታው በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ በሚከፈል ለቤቶች ግንባታ፣ ዕደሳ፣ ማሻሻያና ግዥ ብድር ማዋል፣ እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ የአጭር ጊዜ የሥራ ማስኬጃ ብድሮችን በተለያዩ መንገዶች የመስጠት ዓላማ አለው ተብሏል፡፡ ቤቶችን መሥራትና መሸጥ ወይም ማከራየት፣ ለመኖሪያ ቤት ገንቢዎች የቴክኒክ ዕገዛና ድጋፍ ማድረግ፣ የባንኩን ዓላማ ለማሳካት በአገር ውስጥ የቤቶች ግንባታን ማበረታታት እተገብራቸዋለሁ ካለው ዓላማ ውስጥ ተካተዋል፡፡
ከወለድ ነፃ የሆኑ የባንክ አገልግሎቶችን መስጠትና ለደንበኞች ወኪል በመሆን አክሲዮኖችን መሸጥና ገንዘብ ማስተዳደር፣ በሌሎች ድርጅቶች ኢንቨስት ማድረግና ሌሎች የተለመዱ የባንክ አገልግሎቶችን የመስጠት ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀስ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በቤት ግንባታና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለመሥራት የታሰቡት ሥራዎች ዘመናዊ ግንባታን ለማጎልበት የሚያግዙ ናቸው ተብሏል፡፡ ቤት ሠርተው ለማከራየት የሚፈልጉ ወገኖችን በመደገፍ ጭምር ለመሥራት የሚሻ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታሁን፣ አሠራሩ የቤት ግንባታ ወጪን ለመቀነስም ዕገዛ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት በአምስት ባንኮች አክሲዮኖችን እየሸጠ ሲሆን፣ በ2012 አጋማሽ ላይ ሥራ ለመጀመር አቅዷል፡፡