Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ጀኔሬተሮች ውስጥ አምስቱ ግድቡ ተጠናቆ ውኃ ከተሞላ በኋላ...

ከህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ጀኔሬተሮች ውስጥ አምስቱ ግድቡ ተጠናቆ ውኃ ከተሞላ በኋላ እንዲተከሉ ተወሰነ

ቀን:

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አካል ከሚሆኑት 16 የኃይል ማመንጫ ጀኔሬተሮች መካከል አምስቱ ጀኔሬተሮች፣ የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ የሚፈለገው ውኃ ከተሞላ በኋላ እንዲገጠሙ ተወሰነ፡፡

ከፍተኛ ሀብት የሚወጣባቸው እነዚህ ውስን ጀኔሬተሮች ግድቡ ሙሉ በሙሉ በውኃ ሳይሞላ ኃይል ማመንጨት እንደማይችሉ እየታወቀ እንዲደረደሩ ማድረግ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የሌለው፣ ይልቁንም ለእነዚህ ጀኔሬተሮች የሚወጣውን ሀብት ለሌላ ፍላጎት በማዋል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማስገኘት የውሳኔው ምክንያትነት እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሪፖርተር ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሆሮ (ኢንጂነር) ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የኃይል ማመንጫ ግድቡ ቀሪ ግንባታ በሦስት ምዕራፎች ተከፍሎ እንዲከናወን የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መንግሥት ተቀብሎ እንዳፀደቀውና ግንባታውም በዚሁ በተከለሰ የግንባታ መርሐ ግብር መሠረት መከናወን ተጀምሯል፡፡

- Advertisement -

በተከለሰው የግንባታ መርሐ ግብር መሠረት የመጀመሪያ ምዕራፍ ትኩረት የሚያደርገው፣ በታችኛው የግድቡ አካል የሚገጠሙትን ሁለት የኃይል ማመንጫ ጀኔሬተሮችን እስከ 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ኃይል ወደ ማመንጨት ተግባራቸው እንደሚገቡ ማድረግ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

 በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ዘጠኝ የኃይል ማመንጫ ጀኔሬተሮች እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ወደ ኃይል ማመንጨት ተግባር እንደሚገቡ የሚደረግ መሆኑን፣ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አስረድተዋል፡፡

ቀሪዎቹ አምስት ጀኔሬተሮች ተከላ ደግሞ በቀጣዩ ምዕራፍ ማለትም ሁለተኛው ምዕራፍ ትግበራ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ የግድቡ የሲቪል ሥራዎች ግንባታ አልቆ በውኃ ከተሞላ በኋላ እንደሚፈጸም ገልጸዋል፡፡ “እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስነው ከፍተኛ ሀብት የሚወጣባቸውን 16 ጀኔሬተሮች ደርድሮ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችለው ውኃ በግድቡ እስኪሞላ ድረስ የተወሰኑት ጀኔሬተሮች ኃይል ሳያመነጩ እንዲጠብቁ ማድረግ ይሻላል? ወይስ ግድቡ ሙሉ በሙሉ በውኃ እስኪሞላ ድረስ በሚኖረው ዓመታዊ የውኃ መጠን በዓመት ማመንጨት የሚቻለውን የኃይል መጠን ሊያመነጩ የሚችሉትን ብቻ ተክሎ ወደ ሥራ በማስገባት መካከል፣ የተሻለ ፋይዳ የሚኖረውን መዝኖ በማጤን ነው፤” ሲሉ የውሳኔውን አመክንዮ አስረድተዋል፡፡

 አንድ የኃይል ማመንጫን አቅም ያመነጫል በተባለው አጠቃላይ ሜጋ ዋት ኃይል የመለካት የተሳሳተ ግንዛቤ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደተዛመተ የሚገልጹት ኢንጂነሩ፣ ሜጋ ዋት ማለት የተመረተውን ኃይል እንዴት እንጠቀምበት (Rate of Energy Power Usage) ማለት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የአንድ በውኃ የሚሠራ ኃይል ማመንጫ አቅም የሚለካው በሁለት ነገሮች መሆኑን፣ ከእነዚህም አንዱ ኃይል ለማመንጨት ጥቅም ላይ በሚውለው የውኃ መጠን (Water Discharge) ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ውኃው ከምን ከፍታ ተውርውሮ ተርባይኖቹን ይመታል በሚለው የውኃው ጉልበት መጠን እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑም የህዳሴው ግድብ ውስጥ የሚገባው ዓመታዊ የውኃ መጠን፣ እንዲሁም ውኃው ተርባይኑን የሚመታበት ከፍታ የተወሰነ ከሆነ ቋሚ የኢነርጂ ማመንጨት አቅሙ የታቀደው አማካይ ብቻ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

 “ይህንን ኢነርጂ እንዴት አድርጌ ኃይል አመነጭበታለሁ ሲባል ነው የጀኔሬተር ቁጥር የሚመጣው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ በህዳሴ ግድቡ 16 ጀኔሬተሮችን መደርደር ኢኮኖሚያዊ ትርጉም የለውም፡፡ ምክንያቱም ከታችኛው የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ጋር ተደራድሮ በሚወሰነው መሠረት ግድቡን ውኃ ለመሙላት ረጅም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ፣ ጀኔሬተሮቹን ደርድሮ አምስት ዓመት ወይም ሰባት ዓመት መጠበቅ ለሌላ የልማት ሥራ ውሎ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ማስገኘት የሚችልን ሀብት ያለ ጥቅም ማበከን ነው የሚሆነው፤’’ ብለዋል፡፡ በመሆኑም 11 ጀኔሬተሮችን ወደ ሥራ አስገብቶ የተቀሩትን ግድቡ ሙሉ በሙሉ ውኃ ከተሞላ በኋላ አስፈላጊነቱ እየታየ እንዲተከሉ መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህደሴ ግድብ ግንባታን ለማስጀመር ሳሊኒ ከተባለው የጣሊያን ኩባንያ ጋር ውል የተገባው በታኅሳስ ወር 2003 ዓ.ም. ሲሆን፣ ግንባታውን ለማስጀመር የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠው በዚያው ዓመት መጋቢት ወር ነበር፡፡

 የኃይል ማመንጫ ግድቡን ገንብቶ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ከኮንትራክተሩ ሳሊኒ ኩባንያ ጋር የተገባው የውል መጠን 3.3 ቢሊዮን ዩሮ ሲሆን፣ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት የነበረው ዕቅድ 15 ኃይል ማመንጫዎችን (ተርባይን/ጀኔረተሮችን) በመጠቀም 5,250 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የኃይል ማመንጫ መገንባት እንደነበር ሪፖርተር ያገኘነው የሰነድ ማስረጃ ያመለክታል፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥት በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ አገራዊ የኢንጂነሪንግ አቅምን አብሮ መገንባት እንደሚያስፈልግ በማመን የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የኃይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር ሥራዎችን ማለትም የተርባይን፣ የጀኔረተር፣ የ500 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ፣ የውኃ ማስተላለፊያ የብረታ ብረት ሥራዎች በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) እንዲከናወኑ ወስኗል፡፡

 በዚህም መሠረት የመጀመሪያው የግንባታ ውል በጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም. እንዲሻሻል ተደርጎ ውሉ ለሁለት መከፈሉን፣ በተደረገው የውል ማሻሻያም ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የግድቡን የሲቪል ሥራዎች ሙሉ በሙሉ በ2.32 ቢሊዮን ዩሮ እንዲያከናውን፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የኃይድሮሊክ ሰቲል ስትራክቸር ሥራዎችን ደግሞ ሜቴክ በ1.007 ቢሊዮን ዩሮ እንዲያከናውን መደረጉን መረጃው ያመለክታል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጀመር ታሳቢ የተድረገው ግንባታው በአራት ዓመት ውስጥ 60 ሜትር ከፍታ ላይ እያለ ቀድመው የሚተከሉትን የታኞቹን ሁለት ተርባይኖች በመጠቀም፣ 750 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት ነበር፡፡ ነገር ግንባታው ከተጀመረ በኋላ የውል ማሻሻያ መደረጉና በግንባታ ወቅትም ጥልቅ የሆነ ልል የድንጋይ ሸለቆ በማጋጠሙ፣ ግባታው በሦስት ዓመት እንዲጓተት ማድረጉን መረጃው ያስረዳል፡፡

በዚህም ምክንያት ሁለቱን ተርባይኖች ወደ ኃይል ማመንጨት ሥራ ለማስገባት የነበረው ዕቅድ ወደ 2009 ዓ.ም. መጨረሻ እንዲገፋ ቢደረግም፣ በሜቴክ የሚከናወኑ ሥራዎች በመዘግየታቸው አለመቻሉን ይገልጻል፡፡

ሜቴክ ባለበት የፕሮጀክት አስተዳደርና የቴክኒክ ሥራዎች ልምድ ውስንነት የፕሮጀክቱን ጥልቀትና ውስብስብነትን በትክክል አለመረዳት፣ እንዲሁም ለመማር ዝግጁ ካለመሆን ጋር በተያያዘ የተሰጡትን ተግባራት መፈጸም ባለመቻሉ፣ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ከፍተኛ የጥራት ጉድለት በማጋጠሙ ውሉ በዚህ ዓመት እንዲቋረጥ መደረጉን መረጃው ያመለክታል፡፡

ሜቴክ በሥራ ላይ በነበረበት ወቅት ካከናወናቸው ተግባራት መካከል የግድቡን የማመንጨት አቅም ለማሻሻል ግድቡ የሚያርፍበትን ተራራ 40 ሜትር በመግፋት፣ አንድ ተጨማሪ ተርባይን ማስገባት የሚያስችልና በጀኔረተሮች ላይም ማሻሻያ በማድረግ አጠቃላይ የማመንጨት አቅሙ ከ5250 ሜጋ ዋት ወደ 6450 ሜጋ ዋት ከፍ እንዲል ማድረጉ ነው፡፡

የሜቴክ ውል ከተቋረጠ በኋላ ከሜቴክ ጋር ሲሠሩ ከነበሩ አምስት የውጭ  ኩባንያዎች ጋር የተናጠል ውል በመፈጸም፣ ሥራው በድጋሚ እንዲያንሰራራ መደረጉን  መረጃው ያመለክታል፡፡

 የህዳሴው ግድብ በተገባው የመጀመሪያ ኮንትራት መሠረት ሥራዎቹ መከናወን ቢችሉ ኖሮ በ85 ቢሊዮን ብር እንደሚጠናቀቅ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም፣ ዘንድሮ እስከደረሰበት ግንባታ ደረጃ 98 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን በዚህ ዓመት ለፓርላማ የቀረበ ሪፖርት ያስረዳል፡፡

የግድቡ የሲቪል ሥራዎች ግንባታ 82 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች 25 በመቶ፣ የብረታ ብረት ሥራዎች ድግሞ 13 በመቶ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 68.17 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ ቀሪ ሥራዎችን በመፈጸም የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ በአጠቃላይ ከ130 ቢሊዮን ብር በላይ ይወጣል ተብሎ ከወዲሁ ተገምቷል፡፡

 ይህ በእንዲህ እንዳለ ካለፈው አንድ ዓመት ገደማ ተቋርጦ የበረው የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቅ፣ እንዲሁም የአካባቢና ማኅበራዊ ጉዳት ተፅዕኖ የተመለከተ ድርድር በቅርቡ እንዲጀመር ጥያቄ መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...