Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሲፈተሽ

የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሲፈተሽ

ቀን:

የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን፣ ግለሰቦች አስቀድመው በሚያዋጡት አነስተኛ ገንዘብ ከቤተሰብ አባል ወይም ማንም ሰው ቢታመም ምን እከፍላለሁ የሚል ስጋት ሳያድርበት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ሕክምና የሚያገኝበት ሥርዓት ነው፡፡

በ2008 ዓ.ም. ብቻ ሆኖም የጤና መድን ሥርዓት በአግባቡ ባለመተግበሩ ግለሰቦች ለሕክምና 16 ቢሊዮን ብር ከፍለዋል፡፡ በቅርቡ የተሠራና ይፋ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ጥናትም የገንዘቡ መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ አመላክቷል፡፡

የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ ነሐሴ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው የኅብረተሰብ ውይይት፣ የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ አማካሪ አቶ አብዱል ጀሊል ረሻድ እንደገለጹት፣ ለሕክምና ከዋለው ገንዘብ ውስጥ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር የከፈሉት አቅም ያላቸው ታካሚዎች ሲሆኑ፣ ስድስት ቢሊዮን ብር የከፈሉት ደግሞ አቅም የሌላቸው፣ ዕርዳታ ጠይቀውና በዘመድ አዝማድ የተደጎሙ ታካሚዎች ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን ብር የተከፈለው በገጠርና በከተማ የሚገኙ ታካሚዎች ንብረቶቻቸውንና ከብቶቻቸውን ሸጠውና ብድር ወይም አራጣ ገብተው ያጠረቃቀሙት ነው፡፡

- Advertisement -

ሰው በታመመ ጊዜ ምን ያህል እንደሚቸገር፣ ለልመና፣ ንብረትን ለመሸጥና ለብድር እንደሚጋለጥ፣ ይህን ለማስተካከል ሲባልም፣ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሥርዓት መዘርጋቱንና ዓላማውም አቅም የሌለው ወገን በሥርዓቱ ተጠቅሞ ሕክምናውን የሚያገኝበትን አካሄድ ለማስተካከል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሥርዓት ሦስት መሠረታዊ መርሆዎች አሉት፡፡ እነርሱም መደጋገፍ፣ ፍትሐዊነትና አሳታፊነት ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዋነኛው የመደጋገፍ መርሆ ሲሆን፣ ይህም ጤነኞች ታማሚዎችን እንዲሁም የተሻለ ገቢ ያላቸው አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የሚደግፉበት ሥርዓት ነው፡፡

የፍትሐዊነት መርሆ ደግሞ ሁሉም ሰዎች በሕመማቸው መጠን ማግኘት የሚገባቸውን የሕክምና አገልግሎት ሳይሸራረፍ ለማግኘት የሚያስችላቸው አካሄድ ሲሆን፣ አሳታፊነት በተቋሙ የሚፈጠሩ ሰው ሠራሽና ከአቅም በላይ የሚሆኑ ችግሮችን ተጠቃሚዎቹ ማኅበረሰቦች በተደራጀ መልክ ተንቀሳቅሰው ችግሮችን የሚፈቱበትና በምትኩ የተሻለና ጥራት ያለው አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል ስልት ነው፡፡

በሌሎች አገሮች የሚታየውና አሁን እየተከሰተ ያለው የበሽታ ተለዋዋጭነት በኢትዮጵያ እየሰፋ መምጣቱን፣ ከአሁን ቀደም በነበረው ተላላፊ በሽታ ችግር ላይ ተላላፊ ያልሆኑት መምጣታቸውን እነዚህን በሽታዎች መታከም ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ያስታወሱት አቶ አብዱል፣ የሕክምና አገልግሎትና የመድኃኒት ዋጋ በየጊዜው እየጨመረና እየናረ መሄዱን፣ ይህንንም ችግር መፍታት የሚቻለው በተደራጀ መንገድ በመረዳዳት መሆኑን አክለዋል፡፡

እንደ አቶ አብዱል ማብራሪያ፣ እስካለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ በ509 ወረዳዎች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ከእነዚህም ወረዳዎች ውስጥ አዲስ አበባ በሚገኙ 40፣ በኦሮሚያ በ201፣ በአማራ 149፣ በደቡብ 88፣ በትግራይ 29 እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ሁለት ወረዳዎች ሥርዓቱ ተስፋፍቶ ለአባሎቻቸው የሕክምና አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ፣ በአፋር በሶማሌና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በሚገኙ ወረዳዎች ሥርዓቱን ለመዘርጋት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን የጤና መድኑን ተግባራዊ ባደረጉ በእነዚሁ ወረዳዎች 4.5 ሚሊዮን አባዎራዎችና አማካሪዎች በአባልነት ታቅፈው የሕክምና አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ እንደተመቻቸ፣ በአጠቃላይ ወደ 20 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሽፋን እንደተሰጠ ገልጸዋል፡፡

በተጠቀሱት ወረዳዎች ላይ እየተገበረ ያለውን የጤና መድህን ሥርዓት ወደ አገር አቀፍ ደረጃ ከፍ ከማለቱ በፊት በወረዳዎች በታሰበው መልኩ ውጤት አስገኝቷል ወይ? በሚለው ዙሪያ ጥናት ተደርጎ የተገኘው ውጤት፣ ሥርዓቱ በዋነኛነት እናቶችን ለማብቃት እንደቻለ፣ የጤና አገልግሎት አጠቃቀሙን በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀየርና ማኅበረሰቡም ከጤና ተቋማቱ በቅርበት እየተጓጓዘ ችግሮችን በመፍታት የመረዳዳትን ባህል አጠናክሮ እንደቀጠለ ተናግረዋል፡፡

ሥርዓቱ በተጠቀሱት ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ እስካሁን የተተገበረው በመመርያ ቢሆንም፣ ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር አገራዊ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል፡፡ እንደ አቶ አብዱል፣ አዲስ አበባ ውስጥ ማኅበረሰቡ በመጀመርያ ደረጃ፣ በጠቅላላና ሪፈራል ሆስፒታሎች አማካይነት የሥርዓቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ከጤና ተቋማት ጋር ተዋውለዋል፡፡ ወረዳው በአብኛው ውል ያሰረው ከጤና ጣቢያዎች ጋር ሲሆን፣ ከዚህ አንፃር በወረዳ ደረጃ የሚገኙ አባላት ወደ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ሆስፒታሎች ሄደው ለመታከም ችግሮች እንደነበሩ፣ በረቂቅ አዋጁ ግን ማንኛውም የሥርዓቱ አባል ከወረዳው ወይም ከክልሉ ውጭ በሚገኙ በየትኞቹም ሆስፒታሎች ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻሉም ተነግሯል፡፡

በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ለመታቀፍ ዓመታዊ መዋጮ መከፈል እንደሚጠበቅ፣ በዚህም መሠረት በገጠር ዓመታዊ መዋጮ 240 ብር ሲሆን፣ አዲስ አበባን በመሳሰሉ ትልልቅ ከተሞች ላይ ግን 500 ብር ነው፡፡ መክፈል የማይችሉ ብሎ ወረዳው ለሚለያቸው ወገኖች ደግሞ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ የሚሸፍንላቸው ይሆናል፡፡

አባል ከሆነ በኋላ በጤና ጣቢያ፣ በመጀመርያ፣ በሁለተኛና ሦስተኛ ደረጀ ሆስፒታሎች በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት የሚሸፈኑ ሁሉም ዓይነት የሕክምና አገልግሎቶች እንደሚሰጥ፣ ከእነዚህም መካከል የምርምራ፣ የላቦራቶሪ፣ የዲያጉኒስቲክ፣ የአልትራሳውንድ፣ የኤምአርአይ፣ የሲቲ ስካንና የመድኃኒት አገልግሎቶች ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ፣ በጤና መድኅን የማይሰጡ ተብለው የተለዩና በጣም ጥቂት የሆኑ የጤና አገልግቶች እንዳሉ፣ ከእነዚህም መካከል አንደኛው የጥርስ ማስተከል ሲሆን፣ የዓይን መነጽርና የትራንስፖርት አገልግሎቶችም በጤና መድኅን ከማይሸፈኑት ተጠቃሽ እንደሆኑ ነው አማካሪው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...