Saturday, April 20, 2024

የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ምን ይዞ መጣ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑን ጨርሶ ለዕረፍት የተዘጋው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ፓርላማ ካሉት 547 ወንበሮች ውስጥ መቶ በመቶ በኢሕአዴግ አባላት (አጋር ፓርቲዎችን ጨምሮ) መያዙ፣ የገዥው ፓርቲን ዴሞክራሲያዊነት ያሳጣና ለትችት የዳረገው እውነታ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይህ ትችት በእርግጥ ቀደም ብሎም ቢሆን የነበረ ቢሆንም በርካታ ዜጎች፣ የፓርቲ አባሎችን፣ አቀንቃኞችንና የውጭ አገሮች መንግሥታትን ጭምር በኢትዮጵያ መድበለ ፓርቲ ግንባታና የዴሞክራሲ ዕድገት ተስፋ ያስቆረጠ መሆኑ ይነገራል፡፡

አሁን በሥራ ላይ ያለው ፓርላማም ሆነ በሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት፣ በግንቦት 2007 ዓ.ም. የተካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ ያለ ምንም ተቀናቃኝ የተቃዋሚ ፓርቲ አባልም ሆነ የግል ተወዳዳሪ ብቻውን ‹ተመርጦ› ነበር የመጣው፡፡

ይህ የገዥው ፓርቲ አሸናፊነት በእርግጥ ከምርጫው ዕለት በፊት የተገመተና እንደሚሆንም የተጠበቀ ቢሆንም፣ በምርጫው ማግሥት በየምርጫ ጣቢያዎቹ የድምፅ ቆጠራ ውጤት ይፋ መሆን በጀመረበት ቅጽበት ነበር በምርጫው ተዓማኒነት ላይ ጥያቄ መነሳት የጀመረው፡፡

ለአብነት ያህል በማሳያነት የሚጠቀሱ የየምርጫ ጣቢያዎችን የወቅቱ ውጤት ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በትውልድ አካባቢያቸው በተወዳደሩበት የበሎሶ ሶሬ የምርጫ ጣቢያዎች ከቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲና ኢዴፓ (የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) ወኪል ተመራጮች ጋር ተወዳድረው፣ አቶ ኃይለ ማርያም በሰፊ ድምፅ ያሸነፉበት ውጤት አንዱ ነው፡፡

የሁለቱ የአቶ ኃይለ ማርያም ተፎካካሪዎች በድምፅ ቆጠራ ያገኙት ውጤት ሁለት እና አንድ ድምፅ ሲሆን፣ ቀሪውን የመራጮች ድምፅ አቶ ኃይለ ማርያም ማግኘታቸው ነበር ይፋ የተደረገው፡፡

ምንም እንኳ አቶ ኃይለ ማርያም የማሸነፋቸው ነገር ቀደም ብሎ የተገመተ ቢሆንም፣ የሁለቱ ተፎካካሪዎች ውጤት ፍፁም ያነሰ መሆኑ ጥያቄ አስነስቶ ነበር፡፡ ሁለቱ ተመራጮች ለራሳቸው ከሰጡት ድምፅ በስተቀር በአካባቢው ዘመድ እንኳ የላቸውም አስብሏል፡፡

የወከሏቸው ፓርቲዎችም ቢሆኑ (ሰማያዊና ኢዴፓ) በምርጫው ክልል ጽሕፈት ቤት ከፍተው ሲንቀሳቀሱ፣ እንዴት ሊመርጣቸው የሚችል አባል ወይም አባል ያልሆነ ደጋፊ የኅብረተሰብ ክፍል ጠፋ የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ምንም እንኳ ሁለቱ የኃይለ ማርያም ተፎካካሪዎች ብዙም የማይታወቁ ግለሰቦች ስለሆኑ ተደረጎ ቢቆጠርም፣ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የተወዳደሩ ስመጥር ፖለቲከኞችም ቢሆኑ በተወዳደሩባቸው የምርጫ ጣቢያዎች በገዥው ፓርቲ ተወካይ ተመራጮች በሰፊ ልዩነት መሸነፋቸው በምርጫ አስፈጻሚዎች የተገለጸ ሀቅ ነው፡፡

ለአብነትም በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተቃዋሚውን ጎራ ወክለው ከሚታወቁት ውስጥ የኦፌኮ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) እና የመድረክ አመራር የነበሩት በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ይጠቀሳሉ፡፡

ዶ/ር መራራ ጠንካራ መሠረት አላቸው በሚባልበት አምቦ ከተማ አካባቢ በሰፊ ልዩነት በኢሕአዴግ ተመራጭ ሲሸነፉ፣ በየነ (ፕሮፌሰር) የማይነቃነቅ ድጋፍ አላቸው በሚባልበት የሀዲያ አካባቢ የምርጫ ጣቢያ በተመሳሳይ መንገድ በገዥው ፓርቲ ተወካይ ተመራጭ ተዘርረው፣ ለዓመታት በአባልነት ከቆዩበት የፓርላማው ወኪልነት ተሰናብተዋል፡፡

በእነዚህ የምርጫ ወረዳዎችና ጣቢያዎች የተስተዋለው ውጤት፣ በመላው አገሪቱ ተመሳሳይ በሚባል ሁኔታ የኢሕአዴግ አሸናፊነት ታውጇል፡፡

ለአንዳንዶች ‹‹የመድበለ ፓርቲ መሞት›› የታወጀበት መስሎ ሲታያቸው ሌሎች ደግሞ የገዥው ፓርቲ አፋኝነትና አምባገነንነት መገለጫ ሆኖ ተወስዷል፡፡

የምርጫው ውጤት ተዓማኒነት ጥያቄ እንዲነሳበት ካደረጉ ጉዳዮች ትልቁን ቦታ በሚይዘው የምርጫ አካሄድ፣ ሕጉንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምዝገባ ሒደት የሚደነግገውን አዋጅ በአስቸጋሪ ጎኑ ይጠቅሳሉ፡፡

ለአብነት በ2007 ዓ.ም. ምርጫ በአንፃራዊነት የተሻለ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቁ ከነበሩት የተቃዋሚ ድርጅቶች አንዱ ሰማያዊ ፓርቲ ነበር፡፡ የወቅቱ ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) የነበሩ ሲሆን፣ መንግሥትን በግልጽ በመተቸትም ሆነ በመጋፈጥ ይታወሳሉ፡፡ ነገር ግን እሳቸው በአዲስ አበባ ከተማ መወዳደር እንዳይችሉ ተደርጎ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የወቅቱ የምርጫ ሕግ በዕጩነት ለሚቀርቡ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚደነግገው ኮታ ውስን በመሆኑ ነበር፡፡ በሕጉ መሠረት ኢንጂነሩ በዕጩነት መቅረብ እንደማይችሉ ከተገለጸ በኋላ፣ በምርጫ ሕጉ ላይ በርካታ ትችቶችና ጥያቄዎች ጎልተው እንዲወጡ አድርጓል፡፡

የድኅረ ምርጫ ራስ ምታት

አምስተኛውን ምርጫ መቶ በመቶ አሸንፎ ፓርላማውን የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ የኋላ ኋላ ነገሮች ሁሉ እንዳሰበው ተረጋግቶ ድሉን ማጣጣምም ሆነ አገር ለመምራት ተቸግሮ ነበር፡፡ ይልቁንም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተቃውሞና ግጭት ከአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ብቅ አሉ፡፡ ይህ ደግሞ ገዥው ፓርቲ የምርጫ ሕግን ጨምሮ በርካታ ሕጎችን እንዲከልስና የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት የሚያስችሉ ለውጦችን እንዲያመጣ አስገድዶታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ለውጥ የተባለው ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ፓርላማው ለሦስተኛ ጊዜ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ያፀደቀው፣ የኢትዮጵያ ምርጫና የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ይገኝበታል፡፡ የአዋጁ ረቂቅ ቀድሞ ብሎ ፓርላማው ለዕረፍት ከመዘጋቱ በፊት ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ነበር የቀረበው፡፡ ከዚያም ኋላ ረቂቅ አዋጁ የተመራለት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲመረምርና ከተለያየ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ከሦስት ጊዜያት በላይ ሲመክርበት መቆየቱም ይታወቃል፡፡

በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት በዕለቱ ቋሚ ኮሚቴው የረቂቅ አዋጁን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ ቀርቦ፣የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር ረቂቅ አዋጅበሚል ስያሜ  አዋጅ ቁጥር 1262/2011 ሆኖ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡ አዋጁ በአገሪቱ በየደረጃው የሚደረጉ ምርጫዎች ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሆኑ ያስችላል ሲሉ ለምክር ቤቱ ገለጹት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ የሺመቤት ነጋሽ ናቸው፡፡ አዋጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን የተለያየ ሐሳብና አመለካከት በሰላማዊናሕጋዊ መንገድ ለመራጩ ሕዝብ በተሻለ ደረጃ እንዲያሳውቁ ያስችላልለዋል።

መራጩ ሕዝብም በመረጃ ላይ በመመሥረት በነፃነት ወኪሎቹን የሚመርጥበት የምርጫ ሥርዓት ለመዘርጋት ታስቦ መቅረቡን፣ ተሳታፊ ፓርቲዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የሚኖራቸውን መብትና ግዴታ በግልጽ የሚያሳይ የምርጫ ሥነ ምግባር እንዲከተሉ የሚያደርግ እንደሆነም ነው የተብራራው። አዋጁ በዋናነት የምርጫ ሥርዓት፣ የምርጫ አፈጻጸም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሠራረትና አስተዳደር፣ የምርጫ ሥነ ምግባር፣ በምርጫ ሒደት የሚነሱ ክርክሮች የሚዳኙበትንና የሚፈቱበትን የአሠራር ሥርዓት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀናጁበትና እንደ አዲስ የሚዋሀዱበትን ዝርዝር የያዘ፣ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉበት መሆኑ ተብራርቷል። በተጨማሪም ከዚህ በፊት በስፋት ይስተዋሉ የነበሩ በርካታ ክፍተቶችን በመሙላት፣ በምርጫውደትና ውጤት ላይ የበለጠ ተዓማኒነትን ለመፍጠር የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል። ቋሚ ኮሚቴው አዋጁን ባቀረበበት ወቅት የአዋጁ ስያሜን ጨምሮ በአዋጁ 149 በሚሆኑ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምሥረታ ጀምሮ እስከ መሥራች አባላት ቁጥር ድረስ አዳዲስ አሠራሮችን እንዳካተተም ተገልጿል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞች ለምርጫ በዕጩነት ከተመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ፣ የምርጫደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሥራ ገበታቸው በጊዜያዊነት እንደሚለቁና ደመወዝና ጥቅማ ጥቅማቸውም እንደማይከበር የሚለው አንዱ ነው።

ረቂቁ የተመራለት ቋሚ ኮሚቴው በምርመራው ወቅት ያከናወናቸውን ውይይቶች፣ ምክክሮችና ከቃላት ጀምሮ የተለያዩ የሐሳብ ማሻሻያዎችን በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ያስረዳ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ አባላትም መሻሻል አለባቸው ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተው ውይይትና ክርክር አድረገው ነበር።

በተለይም በረቂቅ አዋጁ ሴትና ወንድ እኩል ድምፅ ቢያገኙ ሴቷ በምርጫ እንድታሸንፍ በሚደነግገው አንቀጽ ላይ፣ የምክር ቤቱ አባላት ከፍተኛ ክርክር አድርገውበታል። የዚህ ድንጋጌ አባላቱን ዘለግ ላለ ጊዜ በማከራከሩ በአፈ ጉባዔው ጥያቄ መሠረት በድንጋጌው ላይ ድምፅ እንዲሰጥ ተደርጎም ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ሴቶች በሥራና በትምህርት ከወንዶች ጋር ተወዳድረው እኩል ውጤት ቢያመጡ ቅድሚያ ለሴቶች የሚሰጠው ዕድል (Affirmative Action)፣ በምርጫ ሕግ ተግባራዊ መደረግ የሌለበትና ሕገ መንግሥቱንም የሚፃረር በመሆኑ ሊሻሻል ይገባዋል የሚለው ሐሳብ በድምፅ ብልጫማሸነፉ አንቀጹ ውድቅ ተደርጓል። ሌላው ድንጋጌ በአዋጁ የተቀመጠው አንድ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ አሥር ሺሕ አባላት ድጋፍ ማግኘት ሲኖርበት፣ የክልል ፓርቲዎች ደግሞ አራት ሺሕ አባላት ድጋፍ ይጠየቃሉ የሚለው በምክር ቤቱ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎበታል። በሌላ በኩል የመንግሥት ሠራተኛ በምርጫ ተወዳዳሪ ሆኖ ሲቀርብ የምርጫ ቅስቀሳ በሚካሄድበትና ምርጫ በሚከናወንበት ጊዜ ያለ ደመወዝ ፈቃድ እንዲሰጠው ይደረጋል። ከዚህ ባለፈም በሁሉም ደረጃ ለሚገኙ ምክር ቤቶች በምርጫ በሚሳተፍበት ጊዜ፣ በቀጣሪው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ንብረት መገልገል አይፈቀድለትም።

በአዋጁ የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙኃን አጠቃቀምን የሚመለከቱ የሥነ ምግባርና የአፈጻጸም መርሆዎች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው መመርያ መሠረት የሚወሰኑ እንደሆነም ተቀምጧል።

አዋጁ ከቀደሙት አዋጆች በተሻለ ሁኔታ መቅረቡን የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ጭምር የመሰከሩለት ቢሆንም አንዳንድ ድንጋጌዎች ግን ማከራከራቸው አልቀረም፡፡ ለአብነትም ያህል አዋጁ ከመፅደቁ ከአንድ ቀን በፊት ሪፖርተር የኢትዮጵያ ዜጎች ማኅበራዊ ፍትሕ (አዜማ) የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ናትናኤል ዘለቀን ጠይቆ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ሕጉ ፍፁም ነው ባንልም የተሻለና የሚያሠራ ነው›› ብለዋል፡፡

በአዲሱ አዋጁ በዋናነት መነጋገሪያና መወዛገቢያ ከሆኑት ድንጋጌዎች ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ በአገር አቀፍና በክልል ደረጃ ለመመዝገብ የሚያስፈልገው የአባላት ፊርማና የመንግሥት ሠራተኞች በምርጫ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ የተቀመጠላቸው መሥፈርት ይገኙበታል፡፡ አዋጁ በረቂቅ ደረጃ ሲቀርብ አስቀምጧቸው ከነበሩ ድንጋጌዎች ውስጥ ያከራከረው፣ የመንግሥት ተቀጣሪ ሠራተኞች ለምርጫ ዕጩ ሆነው ለመቅረብ ሲፈልጉ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ ሥራቸውን ያቆማሉ የሚለው ነበር፡፡

ነገር ግን ከፓርላማ አባላት በተደረገ ግፊት ይህ የረቂቁ ድንጋጌ እንዲስተካከል ተደርጎ ነው በቅዳሜው የአስቸኳይ ስብሰባ አዋጁ የፀደቀው፡፡ ሐሳቡ በግልም ሆነ በተቃዋሚና በገዥው ፓርቲ በኩል በዕጩነት የሚቀርቡ ተመራጮች የምርጫ ምዝገባ ተጀምሮ ምርጫው እስከሚካሄድበት ዕለት፣ ከመንግሥት ሥራቸው ተነስተው ያለ ደመወዝ እንዲቆዩ የሚያስገድድ ነበር፡፡

ነገር ግን ጉዳዩ የፓርላማ አባላቱንም ሆነ ሌሎች የመንግሥት ሹሞች እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ለምርጫው ሲባል ሥራቸውን ይለቃሉ የሚል መንፈስ ስለነበረው ነው በኋላ ማስተካከያ የተደረገለት፡፡ ረቂቅ ድንጋጌው የተካተተበት ዋና ዓላማም ዕጩዎች በመንግሥት ሀብት የምርጫ እንቅስቃሴያቸውን እንዳያስፈጽሙ የሚል ነበር፡፡ በእርግጥ የረቂቁ ድንጋጌ በቀጥታ ቢያልፍ ኖሮ የገዥው ፓርቲ ተወካይ ዕጩዎች ነበሩ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት የሚሉ አሉ፡፡ ምክንያቱም ደግሞ በመንግሥት ሥራ ውስጥ የገዥው ፓርቲ አባላት ብዛት አላቸው የሚሉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ይህ ድንጋጌ አሁን በፀደቀው አዋጅ መሠረት፣ ‹‹የመንግሥት ሠራተኛ›› የሚለውን ለአዲስ ትርጓሜ አስቀምጦታል፡፡

በአዲሱ ትርጓሜ መሠረት የመንግሥት ሠራተኛ ማለት በፌዴራል ወይም ለክልል መንግሥት በቋሚነት ተቀጥሮ የሚሠራ ሲሆን ሚኒስትሮችን፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችን፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ደረጃና ከዚያ በላይ የሆኑ ተሿሚዎችን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንና በየደረጃው ያሉ የክልል ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን ያካትታል፡፡

በቀዳሚው ረቂቅ ትርጓሜ፣ ‹‹የመንግሥት ሠራተኛ . . .›› ይለቃል የሚለውን ከፍተኛ ባለሥልጣን ቢባል ‹‹ያለ ድምፅ ይሠራል›› በሚል ተክቶታል፡፡ ይህ ማሻሻያ ደግሞ ለአንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች የተለየ ዕይታ ሰጥቷቸዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የሕግ ባለሙያ እንዳስረዱት፣ ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በኋላ በምርጫ ወቅት እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ ያሳያል ብለዋል፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ኢሕአዴግ ከአሥር በላይ የሚሆኑ የራሱን የምክር ቤት አባላት ነው የሚያወዳድረው፡፡ እነዚህን አባላት የትምህርት ደረጃ ከማስትሬት በላይ እንዲሆኑ በማገዝ እነሱኑ ነው የሚያወዳድረው፡፡ በዚህም መሠረት በዚህ ምርጫም በአብዛኛው እነዚሁ አባላት እንደሚያወዳድር ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ስለዚህ እነዚህን የምክር ቤት አባላላት ያለ ደመወዝ በመጪው ምርጫ ሊያወዳድር የሚችል ሲሆን፣ በራሱ ላይ ብዙም ጫና እንደማይኖርበት ገልጸዋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ኢሕአዴግ ለስድስት ወራት ደመወዝ ባይከፈለው ዕጩ የሚሆን አባል ስለማያጣ፣ በሌላ በኩል ኢሕአዴግ ለፓርላማ ወንበር ለሚወዳደሩ 547 አባላቱ ደመወዝ አይከፍልም ማለት ነው ይላሉ፡፡

ይህ ድንጋጌ በአንፃሩ በተቃዋሚዎች ላይ ጫና መፍጠሩ እንደማይቀር ይናገራሉ፡፡ እንዲያውም የማድከሚያ መንገድ ሊሆን እንደሚችልም ባለሙያው ይገምታሉ፡፡ ከዚህ አንፃር አዲሱ አዋጅ ለኢሕአዴግ ሊጠቅም እንደሚችልም ባለሙያው ይገምታሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ማጠናከሪያ ተጨማሪ ሐሳብ ከአዋጁ ድንጋጌዎች የተገለጹትን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ ለአብነት በማንኛውም ዕጩ ተወዳዳሪ በዕጩነት ለመመዝገብ ከሚወዳደርበት የምርጫ አካባቢ በበፊቱ ሕግ መሠረት እንዲያሰባበሰብ የተቀመጠው የድጋፍ ፊርማ ቁጥር፣ ለተቃዋሚዎች ከባድ እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡

ኢሕአዴግ ግን ቢያንስ እስከ ስምንት ሚሊዮን የሚደርሱ አባላት ስላሉት፣ ከመራጮች ፊርማ ለማሰባሰብ ችግር የለበትም፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች አንፃር ነው አዲሱ አዋጅ ለኢሕአዴግ ያደላል የሚል መከራከሪያ የሚነሳው፡፡

በአንፃሩ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሻለ ድጋፍ ሊኖራቸው ይችላል ከሚባሉት ውስጥ ኢዜማና አብን ብቻ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚገልጹ አሉ፡፡ ይህንኑም ሐሳብ የሁለቱ ፓርቲዎች አመራሮች ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

የኢዜማው አቶ ናትናኤል ፓርቲያቸው በቁጥር ከታየ የተቀመጠው ድንጋጌ ብዙም ችግር እንደማያመጣባቸው ሲገልጹ፣ የአብን ምክትል ሊቀመንበር ሞላ በለጠ (ዶ/ር) በበኩላቸው ምንም እንኳ በአዋጅ ላይ ቀድሞ ከጠየቃቸው ነገሮች ውስጥ በአብዛኛው ባያስተቹዋቸውም በቁጥር በኩል ከአባላት ፊርማ የማሰባሰቡ ጉዳይ እንደማያሳስባቸው አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከነበሩ ልምዶች በመነሳት መራጩ ሕዝብ ተቃዋሚዎችን ቢደግፍ እንኳ፣ ከምርጫ በፊት ለዕጩዎች ስሙን ጠቅሶ ፊርማውን ያለ ፍርኃት ሊገልጽ ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ አሁንም ይነሳል፡፡ የሕግ ባለሙያው ለሪፖርተር ይህንኑ ሲያስረዱ፣ ‹‹የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች በምርጫው ዕለት ድጋፋቸውን ሊሰጡ ይችላሉ እንጂ፣ ከዚያ በፊት ማን ደፍሮ ለዕጩዎች (ለተቃዋሚ አባላት) በግልጽ ስሙንና ፊርማውን ሊሰጥ ይችላል?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

በእርግጥ የሕግ ባለሙያው ሐሳብ ሕጉ ከምርጫው በፊት ለተቃዋሚዎች ችግር ከመፍጠሩ በተጨማሪ፣ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 እና 38 አንፃር ሲታዩ ተፃራሪነት ያላቸው ናቸው፡፡ በዚሁ ሕገ መንግሥት ድንጋጌ መሠራት ማንኛውም ዕድሜው 18 እና ከዚያ በላይ የሆነ ዜጋ ያለ ምንም መድልኦና ገደብ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት ተሰጥቶታል፡፡

ከዚህ አንፃር አዲሱ አዋጅ በመንግሥት ሠራተኞች የዕጩነት ተሳትፎ ላይ አግላይ ሆኖ ይታያል ይላሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ የኢሕአዴግ አባላት የሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዛቸው ሳይከፈላቸው በዕጩነት መቅረብ ሲችሉ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ሆነው በመንግሥት ሥራ ተቀጥረው ለሚሠሩ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ፣ የመመረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው በተዘዋዋሪ መንገድ በአዲሱ አዋጅ ተገፏል ማለት ይቻላል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

‹‹ለእኔ እንደሚታየኝ ሕጉ (አዲሱ አዋጅ) ዕጩ መሆን ለሚፈልጉ የመንግሥት ሠራተኞች የሕገ መንግሥት መብታቸው ይጥሳል፡፡ እነዚህ ሰዎች ቤተሰብና ኑሮ አላቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ለስድስት ወራት መቆየት የሚችሉት?›› በማለት በጥያቄ መልክ የአዋጁን ድንጋጌ ይተቻሉ፡፡

ይህ ጉዳይ ደግሞ በተለይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተጨማሪ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ መገፋፋቱ አይቀርም የሚሉ ባለሙያዎች፣ ሕጉን ሊታገሉን ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡ በተለይም የተወሰኑ ወሳኝ ድንጋጌዎች ከሕገ መንግሥቱ አንፃር ያላቸውን ተፃራሪነት በመንቀስ፣ ወደ ሕገ መንግሥታዊ ተርጓሚ አካል መውሰድ እንዳለባቸውም ያሳስባሉ፡፡

ባለሙያውም በፓርላማው ላይ አግራሞት ያደረባቸው መሆኑን በመግለጽ፣ በአንድ ቀን እንዴት ሁለት ዓይነት አቋም ያሳያል ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በቅዳሜው ዕለት አስቸኳይ ስብሰባው ምክር ቤቱ ለምሳሌ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ሴትና ወንድ ሆነው በአንድ የምርጫ ጣቢያ እኩል ነጥብ ቢያስመዘግቡ፣ ለሴቷ ተመራጭ የአሸናፊነት ውሳኔ ይሰጣል የሚለውን የረቀቁን ድንጋጌ ውድቅ አድርጎታል፡፡ የዚህ ዓይነት ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ ያልተደገፈ በመሆኑ፣ በሕገ መንግሥቱ እኩል ነጥብ ያስመዘገቡ ማንኛቸውም ዕጩዎች ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ስለሚያዝ መሆኑን ፓርላማው አስረድቷል፡፡

በአንፃሩ ግን ይኼው ምክር ቤት የመንግሥት ሠራተኞች ለዕጩነት ከቀረቡ ሥራቸውን መልቀቅ አለባቸው ወይም ያለ ደመወዝ መቆየት አለባቸው የሚለውን ድንጋጌ፣ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚፋለስ ውሳኔን ማሳለፉ ነው የተስተዋለው፡፡

ባለፈው ዓመት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ሲመጡ ቃል ከገቧቸው ዋና ዋና ነገሮች ውስጥ፣ የምርጫ ሕጉን መቀየርና በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ የሚለው ይገኝበታል፡፡

ከዚህ አንፃር በምርጫ ሕጉ ላይ ቢደረግ ይሻላል የተባለው ማሻሻያም በከፍተኛ ደረጃ ሲጠበቅ የነበረ መሆኑም ይታወቃል፡፡ በማሻሻያነት የቀረበውም የምርጫ ሕግ ላለፉት ስምንት ወራት ብዙ ውይይትና ምክክር ሲደረግበት ቆይቶ ነው ቅዳሜ ዕለት የፀደቀው፡፡ ነገር ግን ማሻሻያው አሁን እያነጋገረና ጥያቄ ማስነሳቱን ቀጥሏል፡፡

መጪው የ2012 ዓ.ም. ምርጫ በወቅቱ ስለመካሄዱ ጥያቄው በቀጠለበት በዚህ ወቅት፣ ሕጉ አሁን ለአገሪቱ መንግሥትም ሆነ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የውዝግብ አጀንዳ ሆኖ እንዳቀጥል እያሠጋ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹የእኔ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃና ታማኝ፣ እንከን አልባ ምርጫ በማድረግ ኢሕአዴግ አሸንፎም ሆነ ተሸንፎ ማለፍ ነው የምፈልገው፤›› ያሉት ቃላቸው በቅርብ ጊዜ የሚታይ ነው ሲሉ የሚደመጡ አሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -