Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኤርትራን ጨምሮ ከአጎራባች አገሮች ጋር በመንገድ መሠረተ ልማት የመተሳሰር እንቅስቃሴ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር መተግበር አለባቸው ተብለው ከተያዙት ክንውኖች መካከል፣ የመንገድ መሠረተ ልማት አንዱ ነው፡፡ በመንገድ ልማት ዘርፍ አካባቢውን ለማስተሳሰር ያስችላሉ የተባሉ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ሥራ ላይ ለማዋል፣ በኢትዮጵያ በኩል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የምሥራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር የጀመሩት እንቅስቃሴ፣ ኢትዮጵያ ከአጎራባች አገሮች ጋር የሚኖራትን ግንኙነት ለማጠናከር የመንገድ ግንባታዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው መደረጉን ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን የመንገድ መሠረተ ልማት ለማጠናከር አዲስ የተያዘው ስትራቴጂ፣ ከኤርትራ ጋር የሚያገናኙ መንገዶችንም በዋናነት ታሳቢ አድርጎታል፡፡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን አጠቃላይ ግንኙነት ለማጠናከር ሁለቱን አገሮች በየብስ የሚያገናኙ መንገዶች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህም ዘንድሮ ነባሮቹን መንገዶችና ድልድዮች በመጠገን የተጀመረ ሲሆን፣ በ2012 በጀት ዓመት ደግሞ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማካተት የሁለቱን አገሮች የመንገድ ትስስር ለማጠናከር ታሳቢ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኤርትራን ጨምሮ ሌሎች አጎራባች አገሮችን ታሳቢ ያደረጉ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተቀርፀዋል፡፡ እነዚህንም ፕሮጀክቶች ለማስጀመር የኢትዮጵያ መንግሥት በ2012 በጀት ዓመት በጀት ይዟል ብለዋል፡፡

‹‹በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ምሥራቅ አፍሪካን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰርና የጋራ የገበያ ዕድሎችን በጋራ ለመጠቀም እያከናወኑ ያሉት ሥራ፣ አዳዲስ ኮሪደሮችን ለመክፈት የሚያስችሉ የመንገድ ግንባታዎችን ለመሥራት ያግዛል፤›› ያሉት ሀብታሙ (ኢንጂነር)፣ ይህም የአካባቢውን አጠቃላይ ትስስር እንደሚያጠናክር ታስቦ የሚካሄድ ነው ብለዋል፡፡

ከአጎራባች አገሮች ጋር የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር  ከኤርትራ፣ ከኬንያ፣ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከጂቡቲ ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ተመርጠው እንዲጀመሩ ይደረጋል፡፡ ከዚህ አንፃር በ2012 በጀት ዓመት ይጀምራሉ ተብለው ከሚጠበቁት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዳንዶቹ፣ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ ያልነበሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መሆናቸውንም ከዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም ወደ ኤርትራ የሚያመሩ መንገዶችን ለመጠገን ወይም ለመገንባት ይታሰብ ስላልነበረ፣ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አካል ይሆናሉ ተብሎ አይጠበቅም ነበር፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አሁን ግን በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላም ስለወረደ ኤርትራን ታሳቢ ያደረገ አዲስ ፕሮጀክት እንዲቀረፅና ወደ ሥራ እንዲገባ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡   

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው የተበላሸ ግንኙነት ሲታደስና መግባባቱ ሲመጣ፣ የአሰብ ወደብን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ከኤርትራም ወገን እየተሠራ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በኢትዮጵያ በኩል ወደ አሰብ ወደብ የሚወስደው መንገድ ግንባታው ተጀምሮ መቋረጡን ያስታወሱት ሀብታሙ (ኢንጂነር)፣ አሁን ከቆመበት ለመቀጠል የኢትዮጵያ መንግሥት በጀት ይዟል ብለዋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ቀደም ብሎ ሶጃ የተባለው የፈረንሣይ ሥራ ተቋራጭ ጀምሮት የነበረው ከማንዳ ቡሬ ድረስ ያለው መንገድ ነው፡፡ የዚህ መንገድ ዲዛይን ተጠናቆ ያለቀ በመሆኑ፣ በአዲሱ በጀት ዓመት ግንባታው ይጀመራል ተብሏል፡፡ በመንግሥት በጀት የተያዘ በመሆኑ መንገዱን ለሚገነቡ ተጫራቾች በቅርቡ ጨረታ እንደሚወጣም ይጠበቃል፡፡ ግንባታው በሲሚንቶ ኮንክሪት የሚከናወን ነው፡፡

ከዚሁ መንገድ ጋር የተያያዘውና በሶጃ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የተገነባው ቀሪው ወደ አሰብ የሚወስደው መንገድ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አሁን አዲስ የሚሠራው መንገድ ቀድሞ ያልተጠናቀቀውን የመንገድ ክፍል ማስጨረስ ነው ብለዋል፡፡ መንገዱ ከ20 ዓመታት በላይ አገልግሎት ያልሰጠ በመሆኑ የተወሰነ ማስተካከያ ሊያስፈልገው ይችላል እንጂ፣ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ከዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በኤርትራ በኩል ያለው መንገድም ቢሆን ጥገና ቢያስፈልገውም፣ ተጨማሪ መንገድ መሥራት አያስፈልገውም ተብሏል፡፡ ምናልባት ትራፊኩ ሲጨምር ማስፋት ካልሆነ በቀር በጥሩ ይዞታ ላይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ አሰብ ወደብ ከሚደርሱ መንገዶች ውስጥ አንዱ 60.6 ኪሎ ሜትር ጥገና እንደተካሄደለት የሚታወስ ሲሆን፣ በሁለት ኮንትራቶች ተከፍሎ እንዲከናወን ተደርጓል፡፡ የመጀመርያው የኤሊዳር-ማንዳ 30.6 ኪሎ ሜትር መንገድ በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ተጠግኗል፡፡ ሁለተኛው ከማንዳ-ቡሬ 30 ኪሎ ሜትር መንገድ ደግሞ በኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ተጠግኗል፡፡ ለሁለቱም መንገዶች ከባድ ጥገና ማከናወኛ ከመንግሥት ከ121 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉም ታውቋል፡፡

ስድስት ወራት የፈጀው ጥገና በዋነኝነት የተጎዳውን የመንገዱን ክፍል እንደ አዲስ በተመረጠ ጠጠር ማልበስ፣ እስከ አራት ሜትር ድረስ ጠባብ የሆኑትንና ምንም ዓይነት የመንገድ ትከሻ ያልነበረባቸውን መንገዶች ወደ አሥር ሜትርና አሥራ ሁለት ሜትር የመንገድ ግራና ቀን ትከሻን ጨምሮ ማስፋት፣ የቆረጣ ሥራ ማከናወን፣ የውኃ መፍሰሻ ፉካና ቦዮችን መገንባት፣ እንዲሁም ተራራማ በሆኑ ቦታዎች ላይ ናዳን ለመከላከል የሚረዳ የአቃፊ ግንብ ሥራ ማካሄድ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ከአዲስ አበባ-አዋሽ-ሰመራን አልፎ በዲቼቶና በጋላፊ መካከል ወደ ግራ ተገንጥሎ ነው የአሰብ መዳረሻ መንገድ የሚገኘው፡፡ ከአዲስ አበባ አሰብ 882 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ አለው፡፡ ከዚህም ውስጥ 811 ኪሎ ሜትር በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ፣ 71 ኪሎ ሜትር ደግሞ በኤርትራ ውስጥ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

ከኤርትራ ጋር ያለውን የየብስ ግንኙነት ለማጠናከር የታሰበው በዚህ ብቻ ሳይሆን፣ በአዲሱ በጀት ዓመት በመረብ በኩል የሚያሻግረው ድልድይና የሑመራ ድልድይ ከፍተኛ ጥገናና ዕድሳት ይደረግላቸዋል፡፡ በተለይ የሑመራ ድልድይ ያረጀና የተጎዳ በመሆኑ፣ ድልድዩን ለመሥራት መታቀዱም ታውቋል፡፡

ወደ ኤርትራ ከሚወስዱ መንገዶች በተጨማሪ በ2012 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ መንግሥት በጀት ከተያዘላቸው ውስጥ፣ የምሥራቅ አፍሪካን ትስስር ለማጠናከር ሚና ያላቸው ከሶማሊያና ከኬንያ ጋር የሚያስተሳስሩ መንገዶችም ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በተለይ ከሶማሊያ ጋር ከዚህ በፊት ወጥነት በሌለው ሁኔታ ሲከናወን የነበረውን የየብስ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ መደበኛ ወደ ሆነ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነት ለመቀየር ይረዳ ዘንድ፣ የነገሌ ቦረና-ፊልቱ-ዶሎአዶ-መልካ ሱፍቱ መንገድ ይሠራል ተብሏል፡፡ ከነገሌ እስከ ዶሎአዶ ድረስ የሚከናወነው ከጠጠር ወደ አስፋልት ደረጃ የማሳደግ ሥራ ይሆናል፡፡

እንዲሁም ከዶሎአዶ እስከ መልካ ሱፍቱ ያለውን መንገድ ደግሞ በአዲስ የአስፋልት ኮንክሪት ለመገንባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ይኼው መንገድ በተመሳሳይ ከኬንያ ጋር ያለውን የመንገድ ትራንስፖርት የሚያሳልጥ እንደሆነም መረጃው ያሳያል፡፡  

ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን በተመለከተ ደግሞ የነጆ-ጃርሶ-ቤጊ-ያዩ መንገድ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ከነጆ እስከ ጃርሶ ድረስ ያለውን የጠጠር መንገድ ወደ አስፋልት ደረጃ ለማሳደግ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ከቤጊ እስከ ያዩ ድረስ አዲስ መንገድ ለመገንባት እንዲሁ በዕቅድ የተያዘ ሲሆን፣ እነዚህ መንገዶች ሲገነቡ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለው ግንኙነት እንደሚጠናከር ታሳቢ ተደርጓል፡፡  

ከመንገድ ኮሪደሮቹ ጋር የተያያዙት ግንባታዎች አዲስ ብቻ ሳይሆኑ ነባር መንገዶችን ማጠናከርን ጭምር ያጠቃልላል፡፡ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው ከጂቡቲ ጋር ደግሞ ከድሬዳዋ መልካ ጀብዱ ሌላ አማራጭ መንገድ ተደርጎ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በዚህ መስመር ከጂቡቲ ጋር ያለውን የመንገድ ትስስር አማራጭ እንዲኖረው ለማስቻል ከሜኤሶ-ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ለመሥራት መታቀዱን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሀብታሙ (ኢንጂነር) አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች