የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ከፈረንሣይ መንግሥት በተገኘ 85 ሚሊዮን ዩሮ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ነው ያለውን የፈጣን አውቶቡሶች መንገድ፣ በአዲሱ በጀት ዓመት ለመገንባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያጠናቀቀ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የፈጣን አውቶቡስ ትራንዚት (BRT) ከፍተኛ ጥራት ባላቸው አውቶቡሶች ላይ የተመሠረተ ምቹ፣ ፈጣንና ወጪ ቆጣቢ የሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት መሆኑን የገለጸው የባለሥልጣኑ መረጃ፣ ለፈጣን አውቶቡሶች መንገድ ግንባታ ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት መደረጉን ይጠቁማል፡፡
ከጨረታ ሒደቱ ጎን ለጎንም የወሰን ማስከበር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ጠቁሞ፣ የግንባታ ጨረታ ውጤት እንደታወቀም ወደ ግንባታ ይገባል ብሏል፡፡
የፈጣን አውቶቡሶች መንገድ ጠቅላላ ርዝመት 17.4 ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ ከ25 እስከ 40 ሜትር የጎን ስፋት ይኖረዋል፡፡ ከ25 እስከ 40 ሜትር የጎን ስፋት ውስጥ ሰባት ሜትሩ የፈጣን አውቶቡሶቹን መንገድ ሌሎች ተሽከርካሪዎች እንዳይሄዱበት የሚከላከል የመለያ ኮንክሪት ይሠራለታል ተብሏል፡፡
የፈጣን አውቶቡስ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ ተያያዥ ግንባታዎችን በማካተት ለፈጣን አውቶቡሶቹ ማደሪያ፣ ነዳጅ መሙያና የእጥበት አገልግሎት የሚሰጥበት ዴፖና አገልግሎቱን መቆጣጠሪያ ማዕከል በመካኒሳ አካባቢ እንደሚገነባለት ታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፈጣን መንገዱ በሚያልፍባቸው ስምንት ቦታዎች የሕዝብ ማረፊያ ሥፍራዎች ግንባታ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የፈጣን አውቶቡሶች መስመር 23 ፌርማታዎች ሲኖሩት፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው ማለትም ገበያ፣ ትምህርት ቤት፣ የእምነት ተቋማትና በመሳሰሉ አካባቢዎች በ500 ሜትር ልዩነት ሲገነቡ፣ በሌሎች ሥፍራዎች ደግሞ በ800 ሜትር ልዩነት ይገነባሉ ተብሏል፡፡ በመንገድ ኮሪደሩ በአጠቃላይ 160 ፈጣን አውቶቡሶች የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡ፣ ከእነዚህ ውስጥ 87 ያህሉ 18 ሜትር ርዝመት እንደሚኖራቸው የባለሥልጣኑ መረጃ ያስረዳል፡፡ ቀሪዎቹ 73 አውቶቡሶች ደግሞ 12 ሜትር ርዝመት እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል፡፡
የፈጣን አውቶቡሶች አገልግሎት በቀን ለ16 ሰዓታት ማለትም ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ እንደሚሆን፣ በሰዓት 6,500 ለሚሆኑ መንገደኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል፡፡
የፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት ከከተማ ባቡር አገልግሎት ጋር የሚስተካከልና ተመሳሳይነት አለው፡፡ የፈጣን መንገዱ ግንባታ ከሚካሄድበት የከተማዋ አካባቢ ከዊንጌት ተነስቶ በአውቶቡስ ተራ፣ ተክለ ሃይማኖት፣ ሰንጋ ተራ፣ ሜክሲኮ፣ ቡልጋሪያ፣ ቄራ፣ ጎፋ፣ ጀርመን አደባባይ አድርጎ ጀሞ የሚዘልቀው መንገድ አንዱ ሲሆን፣ መንገዱን ለመገንባት የጨረታ ውጤት ይጠበቃል፡፡ የፈጣን አውቶቡሶች መንገዱ ከአዲስ አበባ ሰሜን ጫፍ ተነስቶ ደቡብ ጫፍ የሚዘልቅ ነው፡፡ ይህም በአዲስ አበባ ውስጥ ካሉት ክፍላተ ከተሞች ውስጥ ግማሽ የሚሆኑትን ጉለሌ፣ ልደታ፣ አዲስ ከተማ፣ ኮልፌ ቀራኒዮና ንፋስ ስልክ ላፍቶን የሚሸፍን ይሆናል፡፡
የፈጣን አውቶቡሶች መንገድ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር፣ በአዲስ አበባ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍና ዘመናዊ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋፋት ትልቅ ዕገዛ ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበትም ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡
በአዲሱ ዓመት ይጀመራል ከተባለው ግንባታ በተጨማሪ በቀጣይ ሌሎች የፈጣን አውቶቡሶች መንገዶች ግንባታ ለማከናወን ዕቅድ ተይዟል፡፡ በቀጣይ የሚገነባው የፈጣን አውቶቡሶች መንገድ ከጦር ኃይሎች ቦሌ፣ ከቦሌ ለገሃር፣ ከሽሮ ሜዳ መገናኛና ከዊንጌት አየር ጤና ድረስ ያሉት መስመሮች ይገኙበታል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አዲስ አበባ ከተማ የፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት እንዲኖራት ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በ2012 በጀት ዓመትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመንገዶች ግንባታ ከ5.5 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ይዟል፡፡