ለመጀመርያ ጊዜ ዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን የሆነው መቐለ 70 እንደርታ እና የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው ፋሲል ከነማ በጊዜ ከአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ውጪ ሆነዋል።
ሁለቱ ክለቦች በሳምንቱ መጨረሻ በመቐለና ዳሬሰላም ከተሞች ባደረጓቸው ጨዋታዎች ከቅድመ ማጣርያ ወደ አንደኛ ዙር የሚያሻግራቸውን ውጤት ማስመዘገብ አልቻሉም። በደርሶ መልስ ጨዋታዎች ከውድድር ውጭ ሆነዋል።
ነሐሴ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በመቐለ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የመልስ ጨዋታውን ያደረገው መቐለ 70 እንደርታ ከኢኳቶሪያል ጊኒው ካኖ ስፖርት ጋር በአንድ እኩል ተለያይቷል። ፍጹም ቅጣት ምትን ጨምሮ ያገኘውን ዕድል ወደ ውጤት መቀየር አልቻለም። ከሁለት ሳምንት በፊት ካኖ ስፖርት 2ለ1 በማሸነፉ በአጠቃላይ ውጤት 3ለ2 አሸንፎ አንደኛውን ዙር ተቀላቅሏል።
በሌላ በኩልም በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ከሳምንታት በፊት በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም አዛም ስፖርትን 1ለ0 አሸንፎ የነበረው ፋሲል በዳሬሰላም ውጤቱን ማስጠበቅ አልቻለም። ከአዲሱ አሠልጣኙ ሥዩም ከበደ ጋር ያቀናው ክለቡ ነሐሴ 18 ቀን ከአዛም ስፖርት ጋር ባደረገው ጨዋታ 3ለ1 በመረታቱ ሩጫው ተገቷል። ለአኅጉራዊ ውድድሮች እንግዳ የሆኑት ሁለቱም ክለቦች በጊዜ የተሰናበቱት በተመሳሳይ አጠቃላይ ውጤት 3ለ2 ተረትተው ነው።