ኢትዮጵያ በሰባት ሜዳሊያ 15ኛ ደረጃ ይዛ ቀሪ ውድድሮችን ትጠብቃለች
ፍጻሜውን ሊያገኝ የሁለት ቀን ዕድሜ በቀረው 12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ እስከ አሁን ሰባት ሜዳሊያዎች አስመዝግባ 15ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ግብጽ 94፣ ደቡብ አፍሪካና አስተናጋጇ ሞሮኮ 56 እና 51 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ይገኛሉ፡፡
በአጠቃላይ 188 አትሌቶች እያሳተፈች የምትገኘው ኢትዮጵያ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ፣ በካራቴ አንድ የወርቅ፣ ሁለት የብርና አራት የነሐስ በድምሩ ሰባት ሜዳሊያዎችን አስመዝግባለች፡፡ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ውጤት የተመዘገበባቸው ስፖርቶች በካራቴ ታሪኩ ግርማ የወርቅ፣ ጸባኦት ጎሳዬና ሰለሞን ቱፋ የነሐስ፣ በቦክስ 52 ኪሎ ግራም ዳዊት በቀለ የነሐስ፤ በአትሌቲክስ 3,000 ሜትር መሰናክል ወንዶች ጌትነት ዋሌ የብር እንዲሁም 5,000 ሜትር ሐዊ ፈይሳና ዓለሚቱ ታሪኩ የብርና የነሐስ ሜዳሊያዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ተጨማሪ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያዎችን ከምታስመዘግብባቸው ውድድሮች የ5,000 ሜትር የወንዶች ሩጫ ይጠበቃል፡፡ ካራቴ፣ ቅርጫት ኳስና ዋና ውድድሮች የተጠናቀቁ መሆናቸውም ታውቋል፡፡