Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናመንግሥት በፓርላማ እንዲፀድቅ የተደረገውን ዓለም አቀፍ የትምባሆ ኮንቬንሽን በመጣሱ ቅሬታ ቀረበበት

መንግሥት በፓርላማ እንዲፀድቅ የተደረገውን ዓለም አቀፍ የትምባሆ ኮንቬንሽን በመጣሱ ቅሬታ ቀረበበት

ቀን:

መንግሥት ተስማምቶ የፈረመውንና በኋላም በፓርላማ ያፀደቀውን የዓለም የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽንና ኮንቬንሽኑን ለማስፈጸም በፓርላማው የወጣውን የምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ የሚጥስ ተግባር እየፈጸመ መሆኑን፣ የትምባሆ ቁጥጥር ተሟጋች የሲቪክ ተቋማት አስታወቀ፡፡ የሕግ ጥሰቱን በፈጸሙ የመንግሥት ተቋማት ላይም ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ታማኝ ግብር ከፋዮችን ዕውቅና ለመስጠት በቅርቡ አካሂዶት በነበረው ዝግጅት ላይ በአገሪቱ ብቸኛ የሆነውን የትምባሆ ኢንዱስትሪ በታማኝ ግብር ከፋይነት የፕላቲኒየም ደረጃ ዕውቅና መሸለሙ ኮንቬንሽኑን የሚጥስ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የተቀበለችውና በፓርላማዋ ያፀደቀችው ዓለም አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥር ማዕቀፍ ኮንቬንሽን፣ እንዲሁም ኮንቬንሽኑን ለማስፈጸም ፓርላማው ያፀደቀው የምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/ 2011፣ ማንኛውም የመንግሥት አካል የትምባሆ ኢንዱስትሪን ከሚያበረታታ ማንኛውም ዓይነት ድርጊት መቆጠብ ይኖርበታል ይላሉ፡፡ በሕግ ካልተፈቀደና ለቁጥጥር ዓላማ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር፣ የመንግሥት ተቋማትም ሆኑ ኃላፊዎች ከትምባሆ አምራች ኢንዱስትሪ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው እንደማይገባ መደንገጉንም ያስረዳሉ፡፡

- Advertisement -

 ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥት ተቋማትም ሆኑ ኃላፊዎች የትምባሆ ምርትንና ድርጅትን በበጎ መንገድ ሊያስተዋውቅ ከሚችል ማንኛውም ተግባር መቆጠብ እንዳለባቸው በግልጽ መደንገጉን ተቋማቱ ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም የገቢዎች ሚኒስቴር ጃፓን ቶባኮ ኢንተርናሽናል ለተባለው ግዙፍ ዓለም አቀፍ የትምባሆ አምራች የተሸጠውን ብሔራዊ የትምባሆ ኢንተርፕራይዝ በታማኝ ግብር ከፋይነት በቅርቡ መሸለሙ፣ ኮንቬንሽኑንም ሆነ በፓርላማ የፀደቀውን ማስፈጸሚያ አዋጅ የሚጥስ ተግባር መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጽ የተናገሩ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡትም የቁጥጥር ሥራቸው በትምባሆ አምራች ድርጅቶች እንዳይሰናከል ሲሉ ብቻ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

እነዚሁ የትምባሆ ቁጥጥር ተሟጋቾች እንደሚሉት ፓርላማው በጥር ወር 2011 ዓ.ም. ያፀደቀው የምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ትምባሆ ማጨስ በማኅበረሰብ ጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ካስቀመጣቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁት ጥብቅ የቁጥጥር ድንጋጌዎች መካከል፣ የመንግሥት ተቋማት ከትምባሆ አምራች ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት የተጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ የተቀመጠው ድንጋጌ ተጠቃሽ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ይኸው አዋጅ መንግሥት የትምባሆ ምርት ቁጥጥር ጉዳዮችን፣ በዓለም የጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ማዕቀፍ ኮንቬንሽንና የኮንቬንሽኑን ማስፈጸሚያ መመርያ መሠረት አድርጎ ይቆጣጠራል የሚል ድንጋጌ መያዙንም አስረድተዋል፡፡ ኮንቬንሽኑና ኮንቬንሽኑን ለማስፈጸም የወጣው ዓለም አቀፍ መመርያ ካስቀመጣቸው ድንጋጌዎች መካከል፣ ማንኛውም ኮንቬንሽኑን የተቀበለ አገር ከትምባሆ አምራች ድርጅቶች ጋር የሚኖረው ግንኙነት በመንግሥትና በትምባሆ አምራቹ መካከል የትምባሆ ምርትን፣ እንዲሁም የድርጅቱን ተያያዥ ተግባር ለመቆጣጠር አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር፣ ምንም ዓይነት የሥራ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደማይችል ይደነግጋል፡፡

ነገር ግን ከትምባሆ አምራቹ ጋር መገናኘትን የግድ የሚል ከሆነ ግንኙነቱ መፈጸም ያለበት በመንግሥትና በትምባሆ አምራቹ መካከል መልካም የትብብር ግንኙነት እንዳለ አድርጎ የሚያሳስት ግንዛቤን በማኅበረሰቡ ላይ ሊፈጥር በማይችልበት መንገድ፣ እንዲሁም የትምባሆ ምርትንና የትምባሆ ድርጅቱን በበጎ መንገድ ሊያስተዋውቅ ወይም ‹ፕሮሞት› ሊያደርግ የማይችል መሆን እንዳለበት እነዚህ ሰነዶች እንደሚያስረዱ፣ በትምባሆ ቁጥጥር ላይ የሚሠሩ ተሟጋቾች ጠቁመዋል፡፡

የትምባሆ ምርትና የትምባሆ አምራች ድርጅት በማንኛውም ሁኔታ እንዳይተዋወቅና በመልካም ተግባር ስሙ እንዳይገለጽ ለማድረግ ሲባልም፣ ኮንቬንሽኑ በትምባሆ አምራች ድርጅቶች ወይም እነሱ በወከሏቸው ማናቸውም አካላት የበጎ አድራጎት ተግባራትን በማከናወንና በማኅበራዊ ኃላፊነት (Social Responsibility) ስም የሚከናወኑ ሥራዎችን በመጠቀም፣ የትምባሆ አምራቹ በማኅበረሰቡ ዘንድ በመልካምነት እንዲታወቅና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ትምባሆ ምርትን የማስተዋወቅ ተግባር መፈጸም እንዳይችሉ ክልከላ መጣሉን ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ኮንቬንሽኑን በማፅደቋ ብቻ ይህንን ድንጋጌ ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ ቢኖርባትም፣ መንግሥት ግን ተጨማሪ ርቀት በመሄድ ኮንቬንሽኑን መሠረት አድርጎ ባወጠው የምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር ተመሳሳይ ክልከላ መጣሉን ያስረዳሉ፡፡

ኮንቬንሽኑን የተቀበሉ አገሮች በትምባሆ አማካይነት የሚመጣን የዜጎች ሕይወት ማጣትና አሰቃቂ በሽታዎችን ቦታ በማይሰጥ ሁኔታ ለትምባሆ አምራች ኢንዱስትሪ የንግድ ሥራና አትራፊነት ሊጠቅም የሚችል ማናቸውንም ዓይነት ጥቅማ ጥቅሞች መስጠት እንደማይችሉ፣ በኮንቬንሽኑ ማስፈጸሚያ መደንገጉንና ኢትዮጵያም ይህንኑ በአዋጅ ቁጥር 1112/ 2011 በማካተት መደንገጓን አመልክተዋል፡፡

 የትምባሆ ምርትን ማስተዋወቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማይቻል በመሆኑ ትምባሆ አምራቾች የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ከፍተኛ ወጪ በማውጣትና በመተግበር ስማቸው በመልካም እንዲነሳ የማድረግ ሥልት በመከተል፣ ምርቱንም ሆነ አምራች ድርጅቱን ቀጥታ ባልሆነ መንገድ እያስተዋወቁ መሆናቸውን በማስተዋል፣ የዓለም አገሮች ይህንን የሚከላከል ኮንቬንሽን ማውጣቸውን ተሟጋቾቹ አብራርተዋል፡፡

 ኢትዮጵያም ኮንቬንሽኑን በመፈረም እንዲሁም ራሱን የቻለ ማስፈጸሚያ አዋጅ በማውጣት ክልከላ ማስቀመጧን አክለዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት ራሱ ይህንን ክልከላ በመጣስ፣ ትምባሆ አምራች ድርጅትን መልካም ስም በመስጠትና በመልካም ተግባር በመሸለም የማስተዋወቅ ተግባር ውስጥ መገኘቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ለትምባሆ አምራች ድርጅቱ የሰጠው የፕላቲንየም የዕውቅና ሽልማት ሕግን የጣሰ ከመሆኑ ባሻገር፣ የዕውቅና ሽልማቱን እንዲበረከት ያደረገው በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር አማካይነትና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በታዳሚነት በተገኙበት ፕሮግራም መሆኑ፣ የተፈጸመውን ጥሰት የከፋ እንደሚያደርገው በቅሬታ ገልጸዋል፡፡ ይህ ድርጊት ትምባሆ አምርቶ መሸጥ የማኅበረሰብን ጤና በእጅጉ የሚጎዳ ሳይሆን፣ የሚያስከብር መልካም ተግባርና አዋጭ ተደርጎ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዲቆጠር ያደረገ መሆኑን በመጥቀስ ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡

ከገቢዎች ሚኒስቴር በተጨማሪ በዚሁ ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የጉምሩክ ኮሚሽንም በሰኔ ወር 2011 ዓ.ም. ከትምባሆ አምራች ድርጅቱ ጋር የትምባሆ ኮንትሮባንድ ንግድን በጋራ ለመዋጋት የትብብር መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ የገለጹ ሲሆን፣ ይህ የኮሚሽኑ ተግባር ደግሞ የለየለት የሕግ ጥሰት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከትምባሆ ድርጅቱ ጋር ይህንን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረም በተጠቀሱት ሕጎች ፈጽሞ የተከለከለ ሆኖ ሳለ፣ የማኅበረሰብ ጤናን የሚያውክ ሸቀጥ የሚያመርት የትምባሆ ድርጅት የኮንትሮባንድ ንግድ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት እንደሚጨነቅ ተደርጎ ስምምነት መፈራረሙንና ይህም በመገናኛ ብዙኃን እንዲነገር መደረጉን ወቅሰዋል፡፡

በጥር ወር የወጣው የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር አዋጅ፣ ማንኛውም የመንግሥት አካል እንዲሁም በጤና ፖሊሲ ላይ የሚሠራ የመንግሥት ሠራተኛ ከትምባሆ ኢንዱስትሪ የሚሰጥ የዓይነትም ሆነ የገንዘብ ስጦታ መቀበል እንደማይችል ይደነግጋል፡፡ የመንግሥት አካል ከትምባሆ ኢንዱስትሪ የበጎ አድራጎት ስጦታ መቀበል የሚችለው የስጦታው ዓላማ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የትምባሆ ምርትን የማያስተዋወቅ ሲሆን፣ ስጦታውም በማንኛውም መንገድ ለሕዝብ ይፋ በማይሆንበት መንገድ እንደሆነ መደንገጉን ከሕግ ሰነዱ ለመረዳት ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ ያወጣችው ይህ አዋጅ ኮንቬንሽኑን ለማስፈጸም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከወጡ ሕጎች መካከል እጅግ ጥብቅና የመንግሥትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን በመገንዘብ ዓለም አቀፍ አድናቆትን ያስገኘ ከመሆን አልፎ፣ አዋጁን ያፀደቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዓለም የጤና ድርጅት የዕውቅና ሽልማት እንዲበረከትለት አስችሏል፡፡

የኮንቬንሽኑና የማስፈጸሚያ ሕጉ ድንጋጌዎች ሥራ ላይ መዋላቸውን የመከታተልና ሲጣሱም ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት በሕግ የተሰጠው ለኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው፡፡ ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የባለሥልጣኑ የሕግ አማካሪ አቶ ደረጀ ሽመልስ ቅሬታው ተገቢና ትክከለኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮንቬንሽኑ ማስፈጸሚያ አዋጅ የወጣው በቅርብ በመሆኑ የመንግሥት ተቋማት ስለተጣለባቸው ክልከላና ግዴታ ግንዛቤ ባለመውሰዳቸው የተፈጠረ ጥሰት ሊሆን እንደሚችል፣ ኃላፊነት የተሰጠው ባለሥልጣንም ሕጉን ለማስፈጸም የሚረዳ ደንብና መመርያ በማርቀቅ ሥራ ላይ በመጠመዱ ሕጉን ለተቋማት የማስተዋወቅ ሥራ ካለመሥራት ጋር ተያይዞ የተከሰተ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ይህንን ጉዳይ ከሚመለከታቸው የገቢዎች ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጋር በማንሳት ባለሥልጣኑ እንደሚወያይበትም አስረድተዋል፡፡ ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ተመሳሳይ ተግባር ከመፈጸም እንዲቆጠቡም፣ የሕጉን ይዘቶች የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡ የተነሳውን ቅሬታ በተመለከተ የገቢዎች ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችን ምላሽ ለማካተት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...