Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መልካም አገልጋዮች ይብዙ

ከመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ የተቸናቸው፣ እንዲታረሙ ኡኡ ያልንባቸው፣ በምሬት አደባባይ የወጣንባቸው፣ የበላይ አካል ይመልከትልን ያልንባቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው፡፡

ሕዝብን ጉቦ እየጠየቁ በማረር የሚታወቁ፣ ተገልጋዩን በማሸማቀቅና በማሳዘን ስማቸውን ያገነኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ባለሟሎች፣ ዛሬ ታርመዋል፤ እጃቸውን ሰብስበዋል ለማለት ይከብዳል፡፡ ከበፊቱ ተስተካክለዋል፣ ተሽለዋል ያልናቸው ተቋማትና ሠራተኞች ውለው ሳያድሩ ታጥቦ ጭቃ ሲሆኑም አይተናል፡፡ በርካታ መንግሥታዊ ተቋማት የተመሠረቱበትን ዓላማ በወጉ ሳይወጡና ተግባራቸውን በሚገባ ሳያሳዩን፣ አገልግሎት ፍለጋ በሄድን ቁጥር መከራ የሚያሳዩን ተቋማት አሉ፡፡ የዚያኑ ያህል መልካም ተግባር እያከናወኑ ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱን›› ተላብሰው ለደምበኛው ምቹ ከባቢ በመፍጠር ጭምር የሚታትሩ ሞገሳም አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም ከበፊቱም የላቀ ለውጥ እያሳዩ በመሆናቸው ማመሥገናችን ተገቢ ነው፡፡

ይህን እንበል እንጂ ተቋማት ተግባርና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የተጀማመሩ ሥራዎች እንዳሉ ቢታወቅም፣ እንቅስቃሴያቸው ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር ሊመጣጠን አልቻለም፡፡ ዛሬም በአግባቡ መስተናገድ አልቻልንም የሚሉ ድምፆች በየመሥሪያ ቤቱ ይደመጣሉ፡፡ ሌብነት አልጠፋም፡፡ በእጅ ሳይባል ጉዳይ የማይፈጸምባቸው መሥሪያ ቤቶች አሁንም አሉ፡፡ ጉዳይ ገዳይ የሚባሉና በቢሮ ከሚገኙ የሌብነት ተጣማሪዎቻቸው ጋር የሕዝቡን ስቃይ የሚያባብሱ ደላሎች ዛሬም መጠናቸው ይብዛም ይነስም በየመሥሪያ ቤቶች ደጃፍ አሉ፡፡ በሕጋዊ ተቋም ውስጥ የተዘረጋው ሕገወጥ ተግባራቸው አልቆመም፡፡ አልተገታም፡፡

የአገልጋይነትን መንፈስ የሚበርዙ፣ የአገርና የሕዝብ ጥቅምን ወደጎን በማለት የሚፈጸሙ ውጫዊና ውስጣዊ ውንብድናዎች አሉ፡፡ ሕዝብን ከሚያማርሩ አሠራሮች ለመላቀቅ ብዙ መልፋትን ይጠይቃል፡፡ ብዙ መክፈልንና ብዙ መድማትን ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ያለውን ችግር ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻል እንኳ፣ ለመቀነስ መበርታት ይበጃል፡፡ ይህ ካልተቻለ ግን ብሶቶች ተጠራቅመው የከፋውን ሊያስከፍሉን ይችላሉ፡፡ ከላይ የሚለፋውን ያህል ከታች ያሉትስ ምን እያደረጉ ነው፣ ሕዝቡን በሥርዓቱ እያስተናገዱ ነው ወይ ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡

በድሮ የሚደነባበሩ አካላት ሊፈጥሩ የሚችሉት ችግር የመንግሥትን ስም በከንቱ የሚያስነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ ለአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል አንዱ ምክንያት ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት መሆኑ አይታበልም፡፡ መልካም አገልግሎት ለመስጠት የሚችል አመራር ከሌለ፣ ከታችኛው ሠራተኛ ምን መልካም ሊጠበቅ ይችላል? በግልም ሆነ በጋራ የሚፈጸም ያልተገባ ተግባር፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ያንሻፍፋል፡፡ ለአገልግሎት መስተጓጎል ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ተገልጋዮችን በተለያየ መልኩ ይጎዳል፡፡ ከአገልግሎት መጓደል ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው ጉዳት  በገንዘብ የማይታመንና የከፋ ነው፡፡ ገንዘብና ጊዜ ይጠፋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ዜጎችን ተስፋ የሚያሳጣ መጥፎ ስሜት ውስጥ ይከታል፡፡ ክፉውን ብቻ እንዲያሰቡ፣ በአገራቸው የተገፉ፣ መንግሥት ለእነሱ ግድ የሌለው ሆኖ ይሰማቸዋል፡፡ ለበቀልም ያነሳሳቸዋል፡፡

እንዲህ ያለውን ጉዳት ያደረሱ ተቋማት በደርዘን አፍርተናል፡፡ በአግባቡ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት ችግር አድርሰዋል ብለን ጣታችንን ከምንጠቁምባቸው መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ግን እኔን እንደ ከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ፈተናዎች ኤጀንሲ ያሳዘነኝ የለም፡፡

ተቋሙ የተማሪዎችን ውጤት ባሳወቀ በቀናት ልዩነት ወይም ሰዓታት በኋላ ተፈታኞችንና ወላጆችን ያበሳጨ ስህተት መፍጠሩ ታወቀ፡፡ በእርግጥ የወላጆችና የተማሪዎች ኡኡታ ሲሰማ ተቋሙ ስህተት መፍጠሩን አምኖ አርማለሁ ብሏል፡፡ ከዚያ በኋላ የተደረገው ዕርማትና ችግሩን ምን ያህል አስተካክሏል የሚለው ጥያቄ መነጋገሪያ ባይሆንም፣ ስህተቱ የተፈጠረበት ምክንያት እንደሆነ የተገለጸው የማረሚያ ኮድ በአግባቡ ባለመጫን የተፈጠረ መሆኑ ሲነገር አናዶኛል፡፡ ይህ ስንኩል ምክንያት የአገሪቱን ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ የሚወስን ተቋም የፈጠረው ሲሆን፣ ደግሞ ምንኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሚጠበቅበት ተቋም የፈጠረው መሆኑ ሲታሰብም ጭምር ያሳፍራል፡፡ በዚህ ኃላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጡት ሁሉ ሊያስጠይቃቸው ይገባል፡፡

ዜጎች ለዓመታት የለፉበትን የትምህርት ውጤት በተቋሙ ንዝህላልነት ገደል ሲገባ ከመመልከት በላይ ምን የከፋ ነገር ይኖራል? በአግባቡ ባለመሥራቱ የተፈጠረው ችግር ተማሪዎችና ወላጆችን እንዴት እንደሚያስደነግጣቸው መገመቱ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ተቋሙ ሥራውን በአግባቡ ባለመሥራቱ የተፈጠረው ችግር በመጥፎ የአገልግሎት አሰጣጥ ሳቢያ ምን ሊከሰት እንደሚችል ያመላከተ ነው፡፡ ከላይ የጠቀስነው ተቋም የተፈጠረውን ችግር ቢያስተካክል እንኳ፣ በአገር ደረጃ የፈጠረውን ትርምስ እንዴት ያካክሰው ይሆን?

ስለዚህ የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል ኃላፊነትን በአግባቡ አለመከወንና የሚከናወነው ሥራና ተግባር በትክክለኛው መንገድ ስለመፈጸሙ ማረጋገጥ አለመቻል የማይሽር ጠባሳ ሊያሳርፍ እንደሚችል የምንማርበት ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹ብልህ ከሰው፣ ሞኝ ከራሱ ይማራል›› እንደሚባለው ከሌሎች ስህተቶች የሚማሩ ተቋማት እንጂ፣ በራሳቸው ችግር ራሳቸውንና ተጠቃሚውን ለአደጋ የሚጥሉ መሥሪያ ቤቶች ሊኖሩን አይገባም፡፡

እግረ መንገዴን አንድ ነገር ላክል፡፡ መልካም ዜጋ ለመፍጠር ተማሪዎች በአዲስ መነቃቃት፣ በፅዱ ሥፍራ እንዲማሩ ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስተባባሪነት የመማሪያ ሥፍራዎችን አድሶ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተደረገ ያለውን ጥረት ማድነቅ እሻለሁ፡፡ የመንግሥት ተማሪዎች የመማሪያ ደብተርና የደንብ ልብስ በነፃ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሠራ ያለው መልካም ሥራ እንዲሁም በቅንነት ማገልገል የሚቻልበትን የደግነት መልዕክት የሚያስተላልፍ በመሆኑ ይበል ሊባል ይገባል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት