ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የትብብር መሥሪያ ቤት (ድፊድ) ምክትል ሚኒስትር አሎክ ሻርማ፣ ከገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ ጋር የ4.23 ቢሊዮን ብር ወይም የ120 ሚሊዮን ፓውንድ ስተርሊንግ የዕርዳታ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ከክልል ባለሥልጣናት ጋር የተገናኙት ምክትል ሚኒስትሩ፣ በኢትዮጵያ በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ እየተካሄዱ የሚገኙ ሥራዎች በተለይም የዛፍ ችግኝ ተከላና የሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴዎች እንዳስተደሰቷቸው ገልጸዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ጋር በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን አውስተዋል፡፡
መንግሥታቸው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ትኩረት ከሚሰጣቸው አገሮች አንዷ እንደሆነች በመግለጽ፣ ከሰሜን አፍሪካ በታች ካሉ አገሮች አኳያም ኢትዮጵያ ምናልባትም ቀዳሚዋ የእንግሊዝ ዕርዳታና ድጋፍ የሚቀርብላት አገር ነች ብለዋታል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታ አድማሱ በበኩላቸው የእንግሊዝ መንግሥት ለኢትዮጵያ ከሰጠው ዕርዳታ ውስጥ 95 ሚሊዮን ፓውንዱ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ሥርዓት ውስጥ በሚካተቱት የውኃ፣ የሳኒቴሽንና ሐይጂን አገልግሎት ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ይውላል፡፡ በዚህ መስክ ቅድሚያ የተሰጣቸው ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑና ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ 1.2 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ የሚውል ድጋፍ ስለመሆኑም አቶ አድማሱ አስታውቀዋል፡፡ የተቀረው 25 ሚሊዮን ፓውንድ ለአራተኛ ዙር መተግበር የሚጀምረው የሴፍቲኔት ፕሮግራም ማስፈጸሚያነት ይውላል ተብሏል፡፡ ሁለቱም ፕሮግራሞች ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲተገበሩ ቆይተዋል ያሉት አቶ አድማሱ፣ ፕሮግራሞቹን በማስፈጸም በኩል የፋይናንስ ችግር ማነቆ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይህን ማነቆ ለማቃለል የሚያግዥ ድጋፍ ከእንግሊዝ መምጣቱን በመግለጽና አገሪቱ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ድጋፍ መጠንም ከፍተኛ የሚባል እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2017 ይፋ የተደረገው አኃዝ እንደሚያሳው እንግሊዝ በዓለም ላይ ትልቅ ድጋፍ ከምትሰጣቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን፣ በዚሁ ጊዜም የ334 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ ማድረጓን ድፊድ ይፋ አድርጓል፡፡ ፓኪስታን 463 ሚሊዮን ፓውንድ በማግኘት ቀዳሚዋ ስትሆን፣ ሶሪያ በ352 ሚሊዮን ፓውንድ ከኢትዮጵያ በመቅደም ስትቀመጥ፣ ናይጄሪያ በ320 ሚሊዮን ፓውንድ ኢትዮጵያን ትከተላለች፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ አፍኒስታን፣ ታንዛኒያ፣ ዮርዳኖስ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሴራሊዮንና ሶማሊያ ሲካተቱበት፣ በጠቅላላው እንግሊዝ ከ2.5 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ድጋፍ ማድረጓን መረጃው ያሳያል፡፡