Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች በአንድ ዓመት 215 ቢሊዮን ብር በላይ አበድረዋል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንግድ ባንክ በ129 ቢሊዮን ብር ሲመራ አዋሽ ባንክ በ15 ቢሊዮን ይከተላል  

የገንዘብ አቅርቦት እጥረት ቅሬታ ሲቀርብበት የከረመ፣ የብድር አቅርቦትም እየተመናመነ ስለመሆኑ ቢነገርም ባንኮች የሚሰጡት የብድር መጠን ግን ከዓመት ዓመት እያደገ ይገኛል፡፡   

ከሰሞኑ ከፋይናንስ ተቋማቱ የሚወጡ ግርድፍ አኃዞች እንደሚያሳዩት፣ ሁለቱ የመንግሥት ባንኮችና 16ቱ የግል ባንኮች በ2011 ዓ.ም. ያፀደቁትና ለብድር ጠያቂዎች የለቀቁት የብድር መጠን ከ215 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻውን በተሸኘው በጀት ዓመት የፈቀደውና የለቀቀው የብድር መጠን ከ129 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ የባንኩ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በ2011 ዓ.ም. የተፈቀደውና የተለቀቀው የብድር መጠን ከ2010 ዓ.ም. ብልጫ አለው፡፡ ባንኩ በካቻምናው በጀት ዓመት የፈቀደውና የለቀቀው ብድር 100 ቢሊዮ ብር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክም 11 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ብድር መፍቀዱ የሚታወስ ነው፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም 13 ቢሊዮን ብር ለማበደር ማቀዱ አይዘነጋም፡፡ 

ከፍተኛ እመርታ እንዳሳየ የሚጠቀሰው ሌላው የግል ባንኮች የ2011 በጀት ዓመት አፈጻጸም ነው፡፡ የግል ባንኮች የብድር መረጃ እንደሚያሳየው፣ 16ቱም ባንኮች ያፀደቁትና የለቀቁት የብድር መጠን ከ2010 ዓ.ም. አኳያ በ29 በመቶ ዕድገት በማስመዝብ 76 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ታውቋል፡፡

የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የሚያስፈልገውን ያህል ገንዘብ ባንኮች እንደማያቀርቡለት በሚተቹበት ወቅት በሌላ ጎኑ ግን የባንኮች የብድር መጠን እያደገ መምጣቱን ከሚያሳየው መረጃ አንፃር፣ ከፍተኛ የብድር መጠን በማቅረብ ንግድ ባንክ ቀዳሚነቱን ይዟል፡፡ ለግሉ ዘርፍ ብቻ ከ22.5 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡

 አገሪቱ ኢኮኖሚያዊውም ሆነ ፖለቲካዊ መረጋጋት ባጣችበት ወቅት፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባለበትና የወጪ ንግድ ገቢ ቁልቁለት በወረደበት ወቅትም ባንኮች የሰጡት ብሎም ያፀደቁት የብድር መጠን ከሚጠበቀውም በላይ እየጨመረ ነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት የአገሪቱን ኢኮኖሚ የተፈታተኑ ፖለቲካዊ ችግሮች በመንሰራፋታቸው የኢኮኖሚ ዕድገት ምጣኔውን ሳይቀር የሚስቡት ችግሮች፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጫናውና ቀውሱ አለመንፀባረቁ እየታየ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ የሚያረጋግጠውም፣ የባንኮች የብድር መጠን ዕድገት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡ ከወቅታዊ የአገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት አንፃር፣ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ጋሬጣ የሆኑ ክስተቶች እያየሉ መምጣታቸው ከሚነገርበት ከ2007 ዓ.ም. ወዲህም ሲታይ ባንኮችን ከትርፍ አትረፊነት አልነቀሳቸውም፡፡ በ2008 ዓ.ም. እንኳ የሁሉም ባንኮች ጠቅላላ የብድር መጠን በ22 በመቶ በላይ ጨምሮ ነበር፡፡ በ2011 ዓ.ም. ከፍተኛ ብድር ከፈቀዱና ከለቀቁ የግል ባንኮች ውስጥ አዋሽ ባንክ በቀዳሚነት ተሰይሟል፡፡ የ2011 ዓ.ም. የብድር መጠኑም 15.8 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች