አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም የክልል ከተሞች ወርልድ ቴኳንዶ በወጣቶች መዘውተር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በአኅጉራዊና ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮችም በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአትሌቲክስ ቀጥሎ በውጤታማነቱ መጠቀስ ጀምሯል፡፡
በሰሜን አፍሪካዊቷ ሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳሊያ በዚሁ ስፖርት በ63 ኪሎ ግራም በወጣቱ ታሪኩ ግርማ አማካይነት አስመዝግባለች፡፡ በሴቶች ጸባኦት ጎሳዬና ሰለሞን ቱፋ ደግሞ በ53 እና በ54 ኪሎ ግራም በተወዳደሩባቸው መድረኮች የነሐስ ሜዳሊያ ማስመዝገባቸው ታውቋል፡፡
በንጉሥ ማሌይ አብደላህ ስታድየም በድምቀት የተጀመረውና 54 የአፍሪካ አገሮች እየተሳተፉበት በሚገኘው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች፣ በአጠቃላይ 6,000 አትሌቶች በ18 የስፖርት ዓይነቶችና በ26 በመከናወን ላይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በምትሳተፍባቸው 13 የስፖተርት ዓይነቶች ማለትም በአትሌቲክስ፣ በቦክስ፣ በብስክሌት፣ በውኃ ዋና፣ በጅምናስቲክ፣ በወርልድ ቴኳንዶ፣ በቼዝ፣ በሴቶች ቅርጫት ኳስ፣ በክብደት ማንሳት፣ በጠረጴዛ ቴንስ፣ በሜዳ ቴኒስ፣ በካራቴና በባድሜንተን 188 አትሌቶች በራባት፣ ካዛብላንካና በሌሎችም ከተሞች በመሳተፍ ላይ ትገኛለች፡፡
አኅጉራዊ ስያሜውን ይዞ ለመጀመርያ ጊዜ በኮንጎ ብራዛቪል አስተናጋጅነት የተጀመረውና አምስት አሠርታትን እንዳስቆጠረ የሚነገርለት የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች፣ ለአፍሪካውያን የአብሮነት ተምሳሌት ተደርጎ ከመወሰዱም ባሻገር ለፓን አፍሪካኒዝም ማቆጥቆጥ በተምሳሌትነቱም ይነገርለታል፡፡ በውድድሩ ልቀው የሚወጡ አትሌቶች ለቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ትልቅ ስንቅ እንደሚሆናቸው ጭምር እምነት የሚጣልበት ነው፡፡
ኢትዮጵያ በመድረኩ ከወርልድ ቴኳንዶ ቀጥሎ ሜዳሊያ ታስመዘግብበታለች ተብሎ በትልቁ እምነት ተጥሎበት የቆየው የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ቡድን ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ተጠቃሎ ሞሮኮ ራባት መግባቱ ታውቋል፡፡