Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለግል ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ጥንካሬ የመንግሥት ድጋፍና ትብብር ያስፈልገዋል›› ወንድወሰን ታምራት (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፣ የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ መሥራችና ፕሬዚዳንት

የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተለያዩ ፈተናዎች ቢገጥሟቸውም በርካታ ተማሪዎችን በየዓመቱ ይቀበላሉ ያስመርቃሉ፡፡ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን ለውይይት ያበቃሉ፣ ያሳትማሉ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ተካሂዷል፡፡ 30 ያህል ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበዋል፡፡ በግል ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍና በከፍተኛ ትምህርት ዓለም አቀፋዊነት ዙሪያ የኮንፈረንሱ አዘጋጅ የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ መሥራችና ፕሬዚዳንት ወንድወሰን ታምራት (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ከጋዜጠኞች ጋር ያካሄዱትን ቃለ ምልልስ ታደሰ ገብረማርያም እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡

ጥያቄ፡- በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጠንካራና የሚሰጡት የትምህርት ዓይነትም ጥራቱ የተጠበቀ ነው ይባላል፡፡ ይህንን ወደ አገራችን ለማምጣት ምን መደረግ አለበት?

ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- በትምህርት ጥራታቸው በጣም የታወቁ የዓለም ክፍሎች አሉ፡፡ በተለይ ካደጉት የዓለም ክፍሎች ታዋቂ የሆኑት የአሜሪካና የጃፓን የግል ዩኒቨርሲቲዎች ይገኙባቸዋል፡፡ በእነዚህ አገሮች ውስጥ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዙ ዓመታት ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ ለግል ተቋማቱ የሚደረግላቸው የፖሊሲ ድጋፍና የሥራ ማመቻቸት ሁኔታም ሰፋ ያለ ነው፡፡  ዘርፉን በማበልጸግ በመንግሥት የሚሰጠውን የከፍተኛ ትምህርት ጫና ለመቀነስ መንግሥት በፖሊሲ ደረጃ ቀረጾ የሚሠራቸውም ሥራዎች አሉ፡፡ ይህንን በተመለከተ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ በአሁኑ ጊዜ እስከ 86 በመቶ ያህሉ ተማሪዎች በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የግል ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ግን አዲስ ነው፡፡ ልምድና ተሞክሮ ይጠይቃል፡፡ ችግሮቹን ተቋቁሞ የሚወጣባቸውን ድጋፎች ይሻል፡፡ እነዚህ እንዳሉ ሆነው መልካም የሆኑ ፖሊሲዎች፣ ተከታታይ የሆኑ የመንግሥት ድጋፍና ትብብር ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዙሪያ የሚሠራውን የምርምር፣ የንግግርና የጋራ ሐሳቦችን የመወራረስ ሥራ ይጠይቃል፡፡ በአጠቃላይ ለግል ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ጥንካሬ የመንግሥት ድጋፍ ግን በዋነኛነት አስፈላጊ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ወደፊት የመንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫ ምን ይሆናል ይላሉ?

ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- ይህንን ለመመለስ ባልችልም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ 50 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እያስተናገደች ያለችበት ወቅት ነው፡፡ ከዚሁ አኳያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን በማስፋፋት ብቻ የአገሪቱን የከፍተኛ ትምህርት ፍላጎት ማሟላት የሚቻልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ለዚህ ነው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው፡፡ ይህም የቁጥር ዕድገት ብቻ እንዳይሆን ተቋማቱን የመደገፍ፣ አመቺ የሆኑ ፖሊሲዎችን የማዘጋጃ ሥራ በመንግሥት በኩል ይጠበቃል፡፡ ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጀምሮ ዘርፉን አላስፈላጊ ወደሆነና የንግድ ስሜት ወዳለው አቅጣጫ እንዳይሄድ፣ መንግሥትና ሕዝቡ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በመወጣት ወደ ተሻለ የጥራት ደረጃ መድረስ ይጠበቅባቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ጥያቄ፡- የከፍተኛ ትምህርት ዓለም አቀፋዊነት ምን ማለት ነው?

ተባባሪ ፕሮፌሰር ታምራት፡- በአሁኑ ወቅት ዓለም ግሎባላይዜሽን (ሉላዊነት) በምንለው ሥርዓት ውስጥ ትገኛለች፡፡ በዚህ የግሎባላይዜሽን ሥርዓት ውስጥ በማንኛውም መስክ ከፍተኛ ትምህርት ላይ የሚታዩና ሰፋፊ የሆኑ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የመምህራንና የተማሪዎችን ንቅናቄ ብንወስድ ተማሪዎች ከአንድ አኅጉር ወደ ሌላ አኅጉር እየሄዱ የሚማሩበት፤ እንዲሁም መምህራን ከአንዱ አኅጉር ወደ ሌላው አኅጉር በመሄድ የሚሠሩበት ሁኔታ አለ፡፡ በምርምርም በኩል ሲታይ እንደዚሁ ተቋማት ብቻቸውን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ተቋማት ጋር በመነጋገርና አብረው በመሆን የግል፣ የጋራ፣ የአካባቢና የአገሮች ችግሮችን የሚፈቱበት የትብብር መስክ አለ፡፡ ከዚህ የትብብር መስኮች በአጠቃላይ በተለምዶ አባባል ኢንተርናላይዜሽን ወይም ዓለም አቀፋዊነት የምንለውን ዘርፍ አቅፈዋል፡፡ ተቋትም ለዚህ ዓይነቱ ዓለም አቀፋዊ ንቅናቄ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይገባቸዋል፡፡ በተለይ በምርምር ዙሪያ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ተቋማት ከሌሎች ተቋማት ጋር የሚያደርጉት ተሳትፎ፣ እርስ በርስ ያለ ግንኙነት ወሳኝ ነው፡፡ ዛሬ የምናዘጋጃቸው ተማሪዎችም ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ዓለም አቀፋዊ ባህሪ ያላቸው፣ የትም ቦታ ሄደው መሥራት የሚችሉ፣ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለዚህም የሚሆን የትምህርት ሥርዓት ቀርጾ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው የትምህርት አካሄድ መኖር ግድ ይላል፡፡

ጥያቄ፡- ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ በግል ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን በየዓመቱ ማካሄድ ከጀመረ 17 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ምን አነሳሳው? በዚህስ የተገኘው ጥቅም ምንድነው?

ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- ኮንፈረንሱን የዛሬ 17 ዓመት ስንጀምረው የግል ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ አዲስና ብዙም የሚታወቅ አልነበረም፡፡ የሚታይበትም መንገድ በአብዛኛው በጥርጣሬና ከንግድ ጋር በተያያዘ ብቻ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች ያሰብነው ነገር ቢኖር ይህ ዘርፍ የተሻለና የሚከበር ዘርፍ ሆኖ ካልተገኘ፤ አንደኛ ተቋሙ ብቻ የሚሠራው ብዙም ትርጉም ላይኖረው እንደሚችል፣ ስለዚህ የግል ተቋማቱ  በቁጥርም ሆነ በጋራ ሊከበሩ የሚችሉት በዘርፉ የተሻለ ዕውቀት ሲኖርና ምን ዓይነት ጥራት እንዳለ ሕዝቡ፣ መንግሥትና ተጠቃሚው ሲያውቁት ብቻ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስን፡፡ በዚህም የተነሳ በግል ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ዙሪያ ያተኮሩ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ማካሄድ ጀመርን፡፡ በጉባዔዎቹም ላይ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ተመራማሪዎች ጭምር በቀረቡት የጥናትና ምርምር ውጤቶች በርካታ ጥቅሞች ተገኝተዋል፡፡ አንዱና መሠረታዊ ጥቅሙ ፖሊሲ አውጪዎች፣ አመንጪዎችና ፖሊሲውን ወደ ተግባር መውሰድ የሚፈልጉ አካላት ሁሌ መረጃ ሲፈልጉ በተደራጀና በተጠና መልክ እንዲደርሳቸው አስችሏል፡፡ በየዓመቱ የሚደረጉ ጥናቶች በጽሐፍ መልክ አሳትመን አስፈላጊ ለሆነ ሥራ፣ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎችና ፖሊሲውን ለሚያስፈጽሙ ሁሉ እንዲደርሱ አድርገናል፡፡ ሌላው ያስገኘው ጥቅም በግል
ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ላይ የሚሠሩ ሌሎች ተመራማሪዎች የበለጠ ሥራቸውን እያጠናከሩ የሚሄዱበትና ሥራቸው ደግሞ ለህትመት በቅቶ የሚሠራጭበትን መንገድ ለማመቻቸት ተችሏል፡፡ የህትመት ሥራዎቻችን ለአገራችን ብቻ ሳይሆን በአኅጉርም ደረጃ አገልግሎት ላይ እንዲውል እየተደረገ ነው፡፡ በግል ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የሚታወቀው ዕውቀት በአገራችን ተወስኖ እንዳይቀር ከአሶስዬሽን ኦፍ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተባብረን እየሠራን ነው፡፡ አሶሴሽኑ ደግሞ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመተባበር የከፍተኛ ትምህርትን  ሥራ በኃላፊነት እየወሰደ የሚያከናውን ትልቅ አኅጉራዊ አካል ነው፡፡ በዚህም በኩል የግል ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ መንግሥት በፖሊሲ አቅጣጫ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ የበኩሉን እገዛ ያደርጋል፡፡

ጥያቄ፡- የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ለማስፋፋት እየተደረገ ያለው ጥረትና ያጋጠመውስ ተግዳሮት ምን ይመስላል?

ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ እንደማንኛውም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቦታና የግንባታ ችግር አለበት፡፡ አሁንም በአንዱ ሳይት ላይ የድህረ ምረቃ መርሐ ግብሮችን ለማስፋፋት ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን የቅድመ ምሩቃን ሥራ የሚያካሂደው ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አካባቢ በተከራየው ሕፃ ውስጥ ነው፡፡ በእኛ በኩል ትልቁ የማስፋፋት ሥራ ብለን የምናምነው ለተግባራዊነቱም የምንንቀሳቀሰው ጥራት ላይ አትኩሮት ሰጥተን የተሻሉ ተማሪዎችን የማውጣትና የተሻለ የምርምርና ጥራት ያለው የትምህርት ተቋም ሆኖ መገኘትን ነው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ጠንክረን እየሠራን ነው፡፡ በሕትመትም ደረጃ በአሁኑ ወቅት የምናሳትማቸው ጆርናሎች በቁጥር ሦስት ደርሰዋል፡፡ አንደኛው በቢዝነስ፣ ሁለተኛው በሕግ፣ ሦስተኛው በአግሪካልቸርና ዴቨሎፕመንት ስተዲስ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ እነዚህ በአኅጉር አቀፍ ደረጃም የተሻለ ዕውቅናና ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ለኅብረተሰቡ የምንሰጠውን አገልግሎት አጠናክረን የመቀጠል ሥራ ሌላው የትኩረት አቅጣጫችን ነው፡፡ ይህም ማለት አቅመ ደካማ ለሆኑና ራሳቸውን መርዳት ለማይችሉ ተገቢውን እገዛና ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ በዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረግላቸው ድጋፍ ላይ በመተባበር ብቻ ሳንወሰን ዩኒቨርሲቲው ይህንን ተግባር የሚያከናውንና ራሱን የቻለ አካል በማቋቋም ተማሪዎች የሚሳተፉበት መንገድ እያመቻቸን ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...

ከጎዳና ከማንሳት ራስን እስከማስቻል የሚዘልቀው ድጋፍ

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን...