Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን በ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የሚቀላቀለው አማራ ባንክ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ 2011 ዓ.ም. በተለየ የሚታይበትን ክስተት አስተናግዷል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለማቋቋም የሚጠይቀውን የተከፈለ ካፒታል መጠን ከ100 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር ካሳደገ ወዲህ፣ ላለፉት ሰባት ዓመታት አንድም ባንክ አሳይቋቋም ቆይቶ ዘንድሮ ግን ሰባት ያህል ባንኮች ለምሥረታ መዘጋጀታቸው ነው፡፡ እነዚህ ባንኮች በአዲሱ ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገቡ በማስታወቅ የአክሲዮን ሽያጭ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በዕቅዳቸው መሠረት ከተጓዙ በቀጣዩ ዓመት የአገሪቱ ባንኮች ቁጥር ወደ 25 ያድጋል፡፡ እስከ ቀጣዩ ዓመት አጋማሽ ድረስ ወደ ሥራ ለመግባት ካቀዱትና በወራት ውስጥ የአክሲዮን ሽያጫቸውን ጨርሰው የባንክ ኢንዱስትሪውን እንደሚቀላቀሉ ካስታወቁት ውስጥ አንዱ፣ አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ነው፡፡ በሁለት ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታልና በ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ወደ ሥራ እገባለሁ ያለውን አማራ ባንክ አደራጅ ኮሚቴውን በሰብሳቢነት የሚመሩት፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው፡፡ የባንኩ የፕሮጀክት አስተባባሪ በመሆን የተሰየሙት ደግሞ የቀድሞ የልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ከዚያም የዓባይ ባንክ የመጀመርያዋ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥ ናቸው፡፡ ወ/ሮ መሰንበት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በመሆንም እያገለገሉ ነው፡፡ አማራ ባንክ ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የአክሲዮን ሽያጩን በይፋ የጀመረበት ሥነ ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል ሲሆኑ፣ የአማራ ባንክ መመሥረት ወቅታዊና ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ባንኩ ሐበሻ፣ ጎህና አማራ የሚባሉትን መጠሪያዎች በመያዝ በተለያዩ መንገዶች ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን ወደ አንድ በማምጣት፣ አማራ ባንክ በሚለው ስያሜ ላይ ስምምነት ተደርጎ ወደ ሥራ መግባቱን አቶ መላኩ ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም አማራ የሚለውን ስያሜ በተመለከተ አግባብ ያልሆነ አተያይ ያላቸውን ወገኖች ገስፀዋል፡፡ የአክሲዮን ሽያጩን መጀመሩን ለመግለጽ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦች የተገኙ ሲሆን፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔና የቀድሞው የፍትሕ ሚኒስትር አቶ ብርሃን ኃይሉ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በምሥሉ ላይ አቶ መላኩ አለበል፣ አቶ መላኩ ፈንታና ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥ ይታያሉ፡፡ 

በሁለት ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል አማራ ባንክ ምሥረታ ተጀመረ 

አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የተሰኘ አዲስ ባንክ፣ የአክሲዮን ሽያጭ እንደጀመረና ከምሥረታው በኋላም በመላ አገሪቱ በመንቀሳቀስ እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡

በምሥረታ ላይ የሚገኘው የአማራ ባንክ አደራጆች ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረጉት፣ ባንኩ በ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና በሁለት ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል ይቋቋማል፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥም የተከፈለ ካፒታሉን አሰባስቦ ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

የባንኩን አክሲዮኖች ለመሸጥ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ካገኘ ጀምሮ አስፈላጊውን ካፒታል ለማሰባሰብ ውክልና በወሰዱ ግለሰቦች አስተባባሪነት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አክሲዮኖች እየሸጠ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ባንኩን ለማቋቋም ምሁራን፣ የአማራ ክልልን ጨምሮ በርካታ የአገር ተቆርቋሪ አካላትን በመሰባሰብ እየተደራጀ እንደሚገኝ የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ ገልጸዋል፡፡ የባንኩ ስያሜ አማራ እንዲሆን የፀናበትን ምክንያትም አብራርተዋል፡፡ የስያሜ አሰጣጡ በተለያዩ ቡድኖች ‹‹ሐበሻ››፣ ‹‹ጎኅ››፣ ‹‹አማራ›› በሚሉ ስያሜዎች ባንክ ለመመሥረት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ የገለጹት አቶ መላኩ፣ እነዚህን እንቅስቃሴዎች ‹‹ወደ አንድ ብናመጣቸው ጠንካራና አቅም ያለው ባንክ መመሥረት እንደሚቻል ውይይት ተደርጎ ወደ አንድ እንዲመጣና ከቀረቡት አማራጮችም አማራ ባንክ፤›› የሚለው ስያሜ ሊመረጥ እንደቻለ አብራርተዋል፡፡    

የአክሲዮን ሽያጩን እንደጀመረ ያስታወቁትና ንግግር ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፣ የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር በአሁኑ ወቅት ወደ ገበያ ለመግባት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተገቢ እንደሆነና ወቅታዊነት እንደተላበሰ ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳ የባንኩ ስያሜ አማራ ባንክ ይሁን እንጂ፣ ተቋምነቱና አገልግሎቱ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን መሆኑ አያጠራጥርም ያሉት አቶ መላኩ አለበል፣ ‹‹አማርኛ ቋንቋ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲገናኙ ድልድይ ሆኖ እንዳገለገለው ሁሉ አማራ ባንክም ሁሉንም ኢትጵያውያን በማሰባሰብ በዘር፣ በሃይማኖና በብሔር ከተፈጠረው ግንኙነት ይልቅ እንደ ሠለጠነው ዓለም በቢዝነስ፣ በመጠቃቀምና አብሮ በማደግ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ አንድነትን በመገንባት አዎንታዊ አስተዋጽኦ፤›› እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡ የሥራ አድማሱንም ኢትዮጵያና ኢትጵያውያውያንን ከማድረግ አልፎ ዓለም አቀፋዊ ገጽታ በመላበስ እንደሚንቀሳቀስ፣ የአገሪቱን የልማት ዘርፎች በመደገፍና ለፋይናንስ ዘርፉ ዕድገት ጉልህ ሚና በመጫወት አማራ ባንክ የድርሻቸውን እንደሚወጣ ያቸላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ከባንኩ ስያሜ ጋር ተያይዘው የሚንፀባረቁ አሉታዊ አስተያየቶችን በተመለከተ አቶ መላኩ ፈንታ ሲናገሩ፣ ባንኩን በማደራጀት ሒደት ካጋጠሙ ችግሮች አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ባንኩን ለማደራጀት በሚደረገው እንቅስቃሴ ወቅት የተለያዩ ችግሮች አጋጥመዋል ያሉት አቶ መላኩ ፈንታ፣ ትልቁ ችግርም ይኼው ከስያሜው ጋር የተገናኘው እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ የተሳሳተ ትርጓሜ በመስጠት የሚሰነዘሩ ሐሳቦች እንዳሉ አውስተዋል፡፡ ‹‹በባንኩና በባንኩ አደረጃጀት፣ ‹‹አማራ›› የሚለውን በማንሳትና አቃፊነቱን በመዘንጋት፣ ባንኩ የፖለቲካ ተፅዕኖ ያረፈበት ለማስመሰል የሚደረግ ጥረት›› እንደሆነ የተናገሩት አቶ መላኩ ፈንታ፣ ይህ አመለካከት መሠረት ቢስ እንደሆነ በመግለጽ አጣጥለውታል፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ የባንኩን ምሥረታ የሚያደናቅፍ ብሎም የክልሉንና የአገሪቱን የልማት ጥረት ለማስተጓጎል የሚደረግ እኩይ ተግባር ነው በማለትም ከስያሜው አኳያ የሚነሱትን ቅሬታዎች ኮንነዋል፡፡

አቶ መላኩ ፈንታ አያይዘውም፣ ባንኩ ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅትና ከፖለቲካ አመለካከት ጋር ያልወገነ ስለመሆኑ፣ በኢትዮጵያ የንግድና የፋይናንስ ሕግ መሠረት የሚተዳደርና ለሕዝብ ልማት ተቆርቋሪ በሆኑ አደራጆች እንደሚመራ በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡ የባንኩ ምሥረታም የራሱ መነሻ ምክንያት እንዳለው በመጥቀስ ዋና ዋና ያሏቸውን አራት ጉዳዮች ጠቅሰዋል፡፡

እነዚህም በክልል፣ በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠሩ ለልማት የመነሳሳት ፍላጎቶችን በተግባር ለመግለጽ የፋይናንስ አቅርቦት ወሳኝ መሆኑ አንደኛው ነው፡፡  ሕዝብ ለልማት የመነሳሳቱን ፍላጎት ወደ ውጤት ለማምጣት በአማራ ክልልም ሆነ በአገር ደረጃ በእኩል ተጠቃሚነት መርህ ለውጥ ለማምጣት ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ ማድረግ የባንኩ ተነሳሾች ዓላማ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ የባንክና የሌላውም የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታይ ሰፊ የገበያ ክፍተት ያለበት በመሆኑ፣ የባንኮች ቁጥር ከሚሰጡት አገልግሎት ጋር ተዳምሮ ውስን በመሆኑ ጭምር አማራ ባንክን ለመመሥረት ፍላጎቱ የነበራቸውን አካላት እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል፡፡ በዘርፉ የሚገኘው ትርፍም ከፍተኛ በመሆኑና ጥናቶች እንደሚያመክቱትም ወደፊትም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገቱ እየጨመረ መሄዱ የማይቋረጥ በመሆኑ፣ ባለአክሲዮኖች ከባንኩ አገልግሎቶች እንዲጠቀሙ ማስቻልም ለባንኩ ምሥረታ መነሾ ከሆኑት ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ያወጣቸው ማሻሻያዎችና በአዲሱ የባንክ ንግድ አሠራር አዋጅ መሠረትም ዳያስፖራው ተሳታፊ የሚሆንበትን መንገድ በማመቻቸት መንቀሳቀስ ባንኩ ከያዛቸው ስትራቴጂዎች መካከል እንደሚጠቀስ በንግግራቸው አመልክተዋል፡፡  

ከባንኩ መሥራቾች ገለፃ ለመገንዘብ እንደተቻለው የአንድ አክሲዮን ዋጋ አንድ ሺሕ ብር ሆኖ መግዛት የሚቻለው ዝቅተኛው የአክሲዮን ብዛት አሥር አክሲዮን ወይም አሥር ሺሕ ብር ነው፡፡

በአቶ መላኩ ፈንታ ንግግር መሠረት፣ የባንኩ የተፈቀደ ካፒታል ሁለት ቢሊዮን ብር በመሆኑ፣ አንድ የባንኩ ባለአክሲዮን እስከ 100 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች መግዛት ይችላል፡፡ አነስተኛ የአክሲዮን መጠኑ አሥር አክሲዮኖች በመደረጉም አነስተኛ ገቢ ያለውን ኅብረተሰብም በባለቤትነት ለማካተት ታስቦ እንደሆነ አክለዋል፡፡

ሌሎች ባንኮች ከሚከተሉት አሠራር ወጣ ያሉ አካሄዶችን እንደሚከተል ሲገልጹም የአማራ ባንክ አደራጆቹ ባንኩን ዕውን ለማድረግ በሚሠሩት ሥራና በአደራጅነታቸው ምክንያት በሕግ የሚፈቀድላቸውንና ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅማ ጥቅም በመተው ባንኩን ያለ ክፍያ ለማቋቋም መነሳታቸውን አቶ መላኩ ፈንታ ተናግረዋል፡፡  

የአማራ ባንክ ዕውን እስኪሆን ድረስ ፕሮጀክቱን እንዲያስተባብሩ የተሰየሙት የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥ ናቸው፡፡ ወይዘሮ መሰንበት በተመሳሳይ መንገድ ዓባይ ባንክን በማቋቋም ይታወሳሉ፡፡ የአማራ ባንክን ወቅታዊ እንቅስቃሴ ሲያብራሩም፣ ገበያ ውስጥ ለመግባትና አትራፊ ኩባንያ እንዲሆን፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ተወዳዳሪ የሚያደርገውን ሥልት እንደሚከተሉም ወ/ሮ መሰንበት ገልጸዋል፡፡

በሰው ኃይል ልማት ላይ የለየለ አካሄድ እንደሚኖር የጠቀሱት ወ/ሮ መሰንበት፣ በዚህ ረገድ ሊሠሩ የታቀዱ ሥራዎች ባንኩን ውጤታማ እንደሚያደርጉት እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ የአማራ ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ ይፋ በተደረገበት ወቅት ባንኩ የሚያስፈልጉት የአሠራር ሥልቶችም እንደሚቀረፁም ተገልጿል፡፡

የባንኩ ምሥረታ አስፈላጊነትን በተመለከተ በተጨማሪ ማብራሪያ በንግግራቸው ያወሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፣ ‹‹አሁን በምንገኝበት የዓለም አቀፍ የንግድ ፉክክር ውስጥ ከፍተኛ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትና ፍላጎት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ የሚፈልጋቸው አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶች ፍጥነትና የባንክ ተጠቃሚ ያልሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ወደ ኢንዱስትሪው የሚገቡ ባንኮች ከፍተኛ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ይገመታል፤›› ብለዋል፡፡

በባንክ ዘርፍ ውስጥ ተፎካካሪና ውጤታማ ሆኖ ለመውጣት ሰፊ ዝግጅት፣ ራዕይ፣ አደረጃጀትና አመራር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት በመግለጽ፣ በመቋቋም ላይ የሚገኘው ባንክም ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ድህንነት በመቅረፍ፣ የሥራ ዕድል በመፈጠርና ለአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ የሆነ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡   

ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ አማራ ባንክ ሁሉ ሌሎች በምሥረታ ላይ የሚገኙ ባንኮችም ተቀዛቅዞ የቆየውን የባንክ ምሥረታ ሒደት እንደ አዲስ በማጧጧፍ በ2011 ዓ.ም. ወደ አክሲዮን ሽያጭ የገቡበት ዓመት ሆኗል፡፡ የብሔራዊ ባንክ የባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ የሚፈቅደው ዝቅተኛው የተከፈለ ካፒታል ቀድሞ ከነበረበት የ100 ሚሊዮን ብር መጠን ወደ 500 ሚሊዮን ብር እንዲያሻቅብ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ለሰባት ዓመታት አንድም ባንክ ሊቋቋም እንዳልቻለ ይታወቃል፡፡ በምሥረታ ሒደት ላይ ከነበሩት መካከል ‹‹ኮከብ ባንክ›› እና ‹‹ዘምዘም ባንክ›› የተሰኙ ባንኮች ከምሥረታ ሒደት በመውጣት እንቅስቃሴያቸውን ማቋረጣቸውም የሚታወስ ነው፡፡

ሆኖም በ2011 ዓ.ም. ባንክ ለማቋቋም የሚጠየቀውን ግማሽ ቢሊዮን ብር አሟልተው ወደ ሥራ ለመግባት እየተዘጋጁ የሚገኙ ሰባት ባንኮች በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አራቱ ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት እየተደራጁ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከአራቱ መካከል ሦስቱ አክሲዮኖችን መሸጥ እንደጀመሩ አስታውቀዋል፡፡

ገዳ ባንክ የተሰኘውና በምሥረታ ላይ የሚገኘው ባንክም የአክሲዮን ሽያጭ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ‹‹ዳያስፖራ ባንክ›› የተሰኘ ባንክ ለመመሥረት ውጥኑ ያላቸው ግለሰብም የንግድ ፈቃድ አውጥተው መንቀሳቀስ ስለመጀመራቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቤቶችና ተያያዥ የባንክ አገልግሎቶች ለመስጠት እየተሰናዳ የሚገኝ ባንክም በዚሁ የጉዞ መስመር ውስጥ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

ከጊዜ ወዲህ የታዩት የባንክ ምሥረታ እንቅስቃሴዎች ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ናቸው የሚል ጥያቄና ትችት ቢያስነሳም በተለይ ወለድ አልባ ባንክ ለመመሥረት እንቅስቃሴ የጀመሩት አደራጆች ግን ዓላማቸው ይህ እንዳልሆነ እየገለጹ ነው፡፡ በምሥረታ ላይ የሚገኙት ባንኮች አክሲዮን ሽያጭ ከጀመሩ በኋላ የሚፈልጉትን ካፒታል በጥቂት ወራት ውስጥ አሟልተው አብዛኞቹ በመጪው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገቡ እያስታወቁ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ አንድ መቶ ሚሊዮን ብርና ከዚያም በታች አሰባስቦ ባንክ ለመመሥረት ሁለት ዓመትና ከዚያም በላይ ይፈጅ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር በ2011 ዓ.ም. አክሲዮን መሸጥ ከጀመሩና በምሥረታ ላይ ከሚገኙ ባንኮች መካከል አብዛኞቹ በጥቂት ወራት ውስጥ ግማሽ ቢሊዮን ብር አሰባስበው ወደ ሥራ እንደሚገቡ በልበ ሙሉነት ሲገልጹ መደመጣቸው በኢንዱስትሪው አዲስ ክስተት ሳይሆን እንደማይቀር ይጠበቃል፡፡

በምሥረታ ላይ የሚገኙት ባንኮች ባሰቡት ልክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ከገቡ የአገሪቱ ባንኮች ቁጥር ከ25 በላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡ ይህም ቢሳካ ግን በቂ  እንደማይሆን የሚገልጹ አሉ፡፡ የአማራ ባንክ አደራጆችም ይህንኑ አንፀባርቋል፡፡ የአማራ ክልል ምክትል መስተዳድር አቶ መላኩ አለበል ይህንን በተመለከተ ሲናገሩ፣ ‹‹ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የግል ባንኮችን የሥራ አፈጻጸም ስንመለከት፣ የገዘፈ ሀብት በማንቀሳቀስ፣ ቁጠባን በማሻሽል፣ ብድርን በማጠናከርና ትርፋማ በመሆን የሚያስመሠግን ደረጃ ላይ ይገኛሉ፤›› ብለው፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው፣ ተፈላጊ  የባንክ አገልግሎቶችን በማቅረብ በኩል፣ ለአብዛኛው የገጠሩ የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ የፋይናንስ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ግን ብዙ እንደሚቀራቸው አመላክተዋል፡፡

የኬንያ ባንኮች ብዛት 42 እንደሆነ በአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ሕግ መሠረት ተቋቁመውና ፈቃድ አግኝተው ከሚንቀሳቀሱት በተጨማሪ ሰባት የውጭ ባንኮች ቅርንጫፎች ታክለውበት በአጠቃላይ 49 ባንኮች በኬንያ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ መላኩ አለበል፣ በናይሮቢ ከተማ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጎዳና መካከል የሚገኘው የኬንያ ማዕከላዊ ባንክ መረጃም ይህንኑ እንደሚያመለክት ጠቅሰዋል፡፡ የባንኮቹ መብዛት ስለሚኖረው ፋይዳም ገልጸዋል፡፡ በአማራ ባንክ የአክሲዮን ሽያጭና የምሥረታ ሒደት ይፋ በተደረገበት ፕሮግራም ላይ በርካታ ታዋቂ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔና የቀድሞው የፍትሕ ሚኒስቴር አቶ ብርሃን ኃይሉ ከሚጠቀሱት መካከል ነበሩ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች