እህት ኩባንያውን አዋሽ ባንክ ጋር የተመሠረተበትን 25ኛ ዓመት (ብርዩ ቤልዮ) ለማክበር ዝግጅት የጀመረው አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ 798 ሚሊዮን ብር የአረቦን ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡
ኩባንያው በተሸኘው በጀት ዓመት ከጠቅላላ መድን ዘርፍ 691.3 ሚሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ማግኘቱንና ከሕይወት መድን ዘርፍ 106.7 ሚሊዮን ብር ገቢ ማሰባሰቡን መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ በሁለቱም የመድን ዘርፎች በድምሩ 798 ሚሊዮን ብር በላይ የአረቦን ገቢ በመሰብሰብ የ18 በመቶ ዕድገት ያሳየንበትን ውጤት እንዳስመዝገበ የኩባንያው መረጃ ያሳያል፡፡ ከጠቅላላ የመድን ዘርፍ ያገኘው አርቦን በ2010 ዓ.ም. ካገኘው አንፃር የ14 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም. ከሕይወት መድን ዘርፍ ያገኘው ገቢም የ53 በመቶ ዕድገት እንደተመዘገበበት ታውቋል፡፡ ኩባንያው በሁለቱም ዘርፎች ያገኘው የአርቦን ገቢ በግል የመድን ድርጅቶች ዘንደ ከተገኘው አብላጫ ያለው እንደሆነም ተመልክቷል፡፡
ኦዲት ባልተደረገ የሒሳብ ሪፖርቱ መሠረት ኩባንያው ከታክስ በፊት 161 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ ኩባንያው በ2011 ዓ.ም. ከታክስ በፊት 140 ሚሊዮን ብር ማትረፉ አይዘነጋም፡፡ የ2011 ዓ.ም. አፈጻጸሙን የሚያመለክተው የኩባንያው መረጃ፣ በየዓመቱ የሚያደካሂደው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እያሳደገ መምጣቱንም አመላክቷል፡፡ በተሸኘው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት ማድረጉንም አስታውቋል፡፡
ኩባንያው ሦስት አዳዲስ ቅርንጫፎችንና ሁለት አገናኝ ቢሮዎችን በ2011 ዓ.ም. በመክፈት የቅርንጫፎቹን ብዛት አንድ የሕይወት ዓብይ ቅርንጫፍን ጨምሮ 48 ያደረሰ ሲሆን፣ ከእነዚህ በተጨማሪ ስድስት አገናኝ ቢሮዎችን በመጠቀም አጠቃላይ የአገልግሎት መስጫዎቹን ብዛት 54 አድርሷል፡፡
በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል 425 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የኩባንያው አጠቃላይ ሀብትም ከ2.3 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ ኩባንያው ከ24 ዓመታት በፊት ሲቋቋም በ456 ባለአክሲዮኖች አማካይነት እንደነበር መዛግብት ያሳያሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የባለአክስዮኖቹን ቁጥር 1,285 አድርሷል፡፡