Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሼክ አል አሙዲ እንደሚጎበኟቸው የሚጠበቁት የሚድሮክ ፕሮጀክቶች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር የሚተዳደሩ ኩባንያዎች ከወትሮው የተለየ እንቅስቃሴ እያካሄዱ ነው፡፡ የማስፋፊያ ሥራዎች እያካሄዱ አሉ፡፡ ኩባንያዎቹን እንደ አዲስ የማደራጀት፣ አንዳንዶቹንም ሙሉ በሙሉ የመለወጥ ሥራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሚድሮክ ማስፋፊያቸውን ያጠናቀቁ ኩባንያዎችን ከሰሞኑ በማስመረቅ ላይ ሲሆን፣ እስካሁን በአምስት ኩባንያዎቹ ላይ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት በማካሄድ ለአገልግሎት ማብቃቱ ይታወሳል፡፡ ሚድሮክ ኩባንያዎቹን የማስፋፋትና በአዳዲስ ቴክኖሎጂ የማደራጀት ብሎም ለሥራ ምቹ ወደ ሆነ አካባቢ የማዛወር ሥራ በሌሎች ኩባንያዎቹ ላይ እያከናወነ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡

 ሐሙስ ነሐሴ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ዴይላይት ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከሚያመርታቸው ውስጥ ሁለት የተለዩ ምርቶች ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገባቸው አስታውቋል፡፡ ሚድሮክ የአዳዲስ ምርቶች ፋብሪካም ለሥራ አብቅቷል፡፡

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋ ይርዳው (ዶ/ር) ይህ ዓይነቱ ኢንቨስትመንትና አዳዲስ አካሄድ ለምን እንዳስፈለገ ሲጠየቁ እንዲህ ብለው ነበር፣ ‹‹አዲስ መንግሥት ተፈጥሯል፡፡ አዲስ አሠራር ስላለና እኛም መለወጥ ስላለብን ነው፤›› በማለት የሚድሮክን የሰሞኑን እንቅስቃሴ አብራርተዋል፡፡ 

የማስፋፋትና አዳዲስ ግንባታዎችን የማከናወን ተግባሩን በተከታታይ ተፈጻሚ እንደሚያደርግ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በሳምንታት ልዩነት ውስጥ  የማስፋፊያ ግንባታ የተደረገባቸውና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የተካሄደባቸውን ኩባንያዎች ለአገልግሎት ማብቃቱን እንደሚገፋበት አስታውቀዋል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ኤልፎራ ነው፡፡ ሆም ዴፖም ከእዚህ ውስጥ ይካተታል፡፡ ትምህርት ቤቶችም ለሥራ ዝግጁ እንደሚደረጉ አረጋ (ዶ/ር) ይፋ አድርገዋል፡፡

ሐሙስ፣ ነሐሴ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ለምርቃት የበቁት ሁለት ማምረቻዎች ትኩረት ስበዋል፡፡ አምፑል ይመረትበት የነበረውና በአሁኑ ወቅት ግን ምርቱን አቋርጦ ወደ ቆርኪ፣ ጣሳና የምግብ ማሸጊያ ማምረቻነት የተለወጠው ፋብሪካ አንዱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ቀዳሚ የአምፑል ምርት በመሆን በ1986 ዓ.ም. የተዋወቀውና ‹‹ሣራ አምፑል›› በተሰኘው መለያ ሥራ የጀረመው ይህ ፋብሪካ ፣ምርቱን ብዙም ሊገፋበት አልቻለም፡፡ የአምፖል ምርቱ አዋጭ ባለመሆኑ ፋብሪካው ሥራ ለማቆም እንደተገደደ አረጋ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ የፋብሪካውን ታሪክ ሲገልጹም፣ ዴይላይት አፕላይድ ቴክኖሎጂስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ቀድሞ ሣራ አምፑል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሚል ስያሜ በ1986 ዓ.ም. አምፖል ለማምረት በ35 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ድርጅት ነበር፡፡ ድርጅቱ ለተወሰነ ጊዜ ሲሠራ ከቆየ በኋላ በገጠመው የገበያ ችግር ምክንያት ምርቱን ለማቆም በመገደዱ ለዓመታት ሥራውን አቋርጦ ቆይቷል፡፡ በገበያ እጦት የተዘጋው ፋብሪካ ዕጣ ፈንታ ምን ይሁን? በሚለው ጉዳይ ላይ ጥናት ተካሂዶ ምላሽ እንደተሰጠበት ተብራርቷል፡፡

የአደራጀጀትና የቴክኖሎጂ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በባለሀብቶቹ በመታመኑ፣ በ1996 ዓ.ም. ኩባንያው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕን እንዲቀላቀል በማድረግ ቀስ በቀስ አሁን ማምረት ወደ ጀመራቸው ምርቶች ሊሸጋገር ችሏል፡፡

ኩባንያውን እንደገና በማዋቀርና የምርት ዓይነቱን በመቀየር የመጠጥ ጠርሙሶች፣ የጠርሙስ መክደኛዎች፣ ቆርኪዎችና የምግብ ማሸጊያ ጣሳዎች የማምረት ሥራዎች ላይ እንዲሰማራ ማድረግ ችሏል፡፡ አዳዲስ ምርቶች ለማካተት የሚያስችሉ የማስፋፊያ ሥራዎችን ታሳቢ ያደረገ፣ በጠቅላላው 229 ሚሊዮን ብር ለፋብሪካው ወጪ መደረጉም ተገልጿል፡፡

በኪሳራ የተዘጋውን የአምፑል ማምረቻ ወደ ጠርሙስ፣ ቆርኪና የምግብ ማሸጊያ ጣሳዎች ማምረቻነት ለመቀየር የአምፖል ማምረቻ የነበረውን ማሞቂያ በመቀጠምና ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ወደ የመጠጥ ጠርሙሶች ማምረቻነት የተቀየረ የተሟላ የጠርሙስ ማምረቻ መሣርያ ሥራ ላይ ለማዋል ተችሏል፡፡ ፋብሪካው በዓመት 12 ሚሊዮን ጠርሙስ የማምረት አቅም ያለው ሆኖ ተገንብቷል ነው፡፡

የቆርኪ ማምረቻውም ከጅምሩ በፈረቃ 700,000 ቆርኪዎች የማምረት አቅም ኖሮት ከጀመረ በኋላ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 1.4 ሚሊዮን ቆርኪ የማምረት አቅም ከፍ እንዲል ተድረጎ እያመረተ ይገኛል ተብሏል፡፡ ከቆርኪ ምርታቸው ብቻ 72 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉ ገልጿል፡፡

በዴይላይት መመረት ከጀመሩት አዳዲስ ምርቶች ውስጥ የምግብ ማሸጊያዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አረጋ (ዶ/ር) ገለጻ፣ ለምግብ ማሸጊያነት የሚውሉ ጣሳዎችን ከውጭ በማስገባት ለደንበኞች ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ሚድሮክ በኤልፎራ በኩል ለመከላከያ ኃይል፣ ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለክልል ፖሊሶችና ለሌሎችም ተቋማት የታሸገ ምግብ ሲያቀርብ የቆየው የማሸጊያ ጣሳውን ከውጭ በመስመጣ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ግን የምግብ ማሸጊያውን በአገር ውስጥ ምረት ለመተካት በመወሰን፣ ለዚህ የሚረዳ የማስፋፊያ ሥራ በማካሄድ ለምግብ ማሸጊያነት የሚውሉ ጣሳዎችን እዚሁ ማምረት ጀምሯል፡፡ ይህ የምግብ ማሸጊያ ጣሳ የሚያመርተው ፋብሪካ ሦስት የተለያየ መጠን ያላቸው ጣሳዎችን ማምረት የሚያስችለውን መሣርያ በ57 ሚሊዮን ብር ወጪ ተክሏል፡፡

‹‹ዴይላይት ምግብ ነክ የኢንዱስትሪ ውጤቶች›› ማምረቻ ቅጥር ግቢ፣ ከምግብና መጠጥ ጋር የተያያዙ ሌሎችም የምርት ግብዓቶች ማቅረብ እንዲችል አስፈላጊ የተባሉ የማስፋፊያ ሥራዎችን ተካሂደውበታል፡፡ በመሆኑም የምግብ ዓይነቶችን የማሸግ ሥራዎችን ለማከናወን የሚቻልበት ተጨማሪ ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝ የገለጹት  አረጋ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት በዴይላይት የማምረቻ ግቢ ውስጥ ባለው የማምረቻ ሥፍራ ተጨማሪ የምግብ ማሸጊያ ማሽነሪዎች እንደሚተከሉ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ በክብር እንግድነት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታዎች የተገኙ ሲሆን፣ በተለይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ የጣሳ ማምረቻው መከፈት እየተገነቡ ለሚገኙት የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግብዓት በማቅረብ ሊጫወት ስለሚችለው ሚና ተናግረዋል፡፡

ለእነዚህ ኢንቨስትመንቶች የሼክ መሐመድ አላሙዲን እገዛ እንደነበረበት አረጋ (ዶ/ር) ገልጸው፣ የማስፋፋት ሥራና ተጨማሪ ኢንቨስትመነት እየተካሄደባቸው የሚገኙ ኩባንያዎችን የሚድሮክ ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ አሊ አል አሙዲ በቅርቡ ወጥተው ይጎበኙዋቸዋል የሚል ተስፋቸውንም አንፀባርቀዋል፡፡ ሼክ መሐመድ አላሙዲን በኢትዮጵያ 74 ኩባንያዎች እንዳሏቸው ሲገለጽ፣ 26ቱ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ሥር የሚተዳደሩ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች