Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በሐሰተኛ መታወቂያዎች ለችግር መዳረጉን ገለጸ

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በሐሰተኛ መታወቂያዎች ለችግር መዳረጉን ገለጸ

ቀን:

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 373 ሚሊዮን ብር ሰብስቧል

የፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ለሚሰጣቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚቀርቡለት የነዋሪዎች መታወቂያዎች ወጥነት የጎደላቸውና በሐሰት የተዘጋጁ የሚገኙበት በመሆኑ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጡን ገለጸ፡፡ ከተጋረጡበትም ችግሮች ንብረት አላግባብ እንዲዘዋወር የማድረግና ውክልና የመሰጠት ሥራዎች ይገኙበታል፡፡

የኤጀንሲው ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ረዳት ኃላፊ አቶ ዓለምእሸት መሸሻ፣ መታወቂያዎቹ ወጥነት የጎደላቸውና አንዳንዴም አግባብነት የሌለው መሆኑን፣ የሰጪው ባለሥልጣን ትክክለኛ ስም፣ ኃላፊነትና ደረጃ የሚገልጽ ቲተር (የስም ማኅተም)  በመታወቂያው ላይ አለመኖሩንና ቢኖርም ሊነበብ በማይችል መልኩ ተቀምጦ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

ከዚህም ሌላ መታወቂያው ላይ ድብቅ የሆኑ መለያዎች (ሰኩሪቲ ፊቸር) አለመኖር ለችግሩ ውስብስብነትና መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተው፣ በተሳሳተ የነዋሪነት መታወቂያ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ሲሰጡ የተደረሰባቸው የኤጀንሲው ባለሙያዎች ተጠያቂ የሆኑበት አካሄድ እንዳለም አስረድተዋል፡፡

ኤጀንሲው ይኼንን ችግር ለመቅረፍ ብዙ ጥረቶች እንዳደረገ፣ ካከናወናቸውም ጥረቶች መካከል ለባለሙያዎች ከፎረንሲክ ጋር የተያያዘ ሥልጠና እንደሰጠ፣ ይህም በቂ ሆኖ እንዳላገኘውና ሐሰተኛውንም መታወቂያ ከትክክለኛው ሊለይ የሚችል በቂ መሣሪያ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በኤሌክትሮኒክ የሚታገዝ የነዋሪነት መታወቂያ በማዘጋጀት በተወሰኑ ቀበሌዎች ላይ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት መቋረጡን ረዳት ኃላፊው ጠቁመው፣ ይህ ዓይነት መታወቂያ ሙሉ በመሉ በሥራ ላይ ቢውል ኖሮ የኤጀንሲውን ችግር በከፊል ያቃልል እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ይህም እንደተጠበቀ ሆኖ ወጥነት ያለው በቀላሉ አስመስሎ ለመሥራት (ፎርጅድ) በማያስችል መልኩ የነዋሪነት መታወቂያ ቢዘጋጅ፣ በኤጀንሲውና መታወቂያ በሚሰጡት መንግሥታዊ ተቋማት መካከል የኔትወርክ አሠራር ቢዘረጋ ለችግሩ ተጨማሪ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል፡፡

ከኤጀንሲውም የመነጨው ሰነድ ምናልባት በሕዝብና በመንግሥት ላይ ሊመለስ የማይችል ጉዳት የሚያስከትል ከሆነ ኤጀንሲው የመነጨውን ሰነድ ከጥቅም ውጭ የማድረግ፣ የመሰረዝና የማገድ ኃላፊነት በአዋጅ 922/2008 ተሰጥቶታል፡፡ ይህንን የሚያደርገው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት አቅርቦ በማስወሰን ነው፡፡

እንደ አቶ ዓለምእሸት፣ ዕድሜው 18 እና ከዚህም በላይ የሆነና የአዕምሮ ጤነነት ያለው ማንኛውም ሰው የነዋሪነት መታወቂያ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ የመንጃ ፍቃድ፣ ፓስፖርት ይዞ በመምጣት ከኤጀንሲው የሚፈልገውን አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳለው አመልክተው፣ የነዋሪነት መታወቂያው በዘመኑ የታደሰ፣ ፎቶግራፍ የተለጠፈበት፣ ስርዝ ድልዝ የሌለው፤ መታወቂያውን የሰጠው ባለሥልጣን ስምና ፊርማ በቲተር ወይም በጽሑፉ ያረፈበት መሆን ይኖርበታል፡፡ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከሆነ ደግሞ ይህንን የሚያረጋገጥ ማስረጃ ከዩኒቨርሲቲው ማምጣት ግድ ይላል፡፡ አሁን ላይ ለግል ዩኒቨርሲቲና ለከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ኤጀንሲው አገልግሎት እንደማይሰጥ፣ የግል ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች  አገልግሎቱን የሚያገኙበት መንገድ በመጠናት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ተገልጋዮቹን ለማርካት አደረጃጀቱንና አሠራሩን በማዘመን ላይ መሆኑን ረዳት ኃላፊው አመልክተው፣ ከዚህ አኳያ ከ16 ዓመታት በላይ ሲሰጥ በነበረው የአገልግሎት ክፍያ ላይ መጠነኛ የዋጋ ማሻሻያ አድርጓል፡፡ 1,000 ብርና ከዚያም በላይ የሆኑ የአገልግሎቱ ክፍያዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል እንዲፈጸም ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡   

የዋጋ ማሻሻያ የተደረገው ከሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን፣ የአገልግሎት ክፍያ ኤጀንሲው በከፈተው የባንክ ሒሳብ ቁጥር 1000001844311 ገቢ እንዲሆን የተደረገው፣ ነሐሴ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. መሆኑን አክለዋል፡፡

ማሻሻያ የተደረገውም የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት ክፍያዎች ለመወሰን በወጣው የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 451/2011 መሠረት ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በፊት በአንድ ኮፒ አምስት ብር ይከፍልበት የነበረው የውክልና ሥልጣን አሁን በኮፒ 30 ብር ሆኗል፡፡

የተሸከርካሪ አካላትና የሞተር ሳይክል ሽያጭ ውሎች ቀደም ሲል ለእያንዳንዳቸው በኮፒ አሥር ብር የነበረው ክፍያ በአሁኑ ጊዜ በነፍስ ወከፍ 50 ብር ሆኗል፡፡

ተገልጋዮች የውክልና ዕድሳት፣ የስጦታና የሽያጭ ውሎችን እየከፈሉ በውጭ ጸሐፊዎች ያጽፉ እንደነበር፣ የዋጋ ማሻሻያ ከተደረገበት ዕለት ጀምሮ ግን የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ውሎች በኤጀንሲው ባለሙያዎች እንደሚያጽፉ፣ አንድ ውክልና ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም አመልክተዋል፡፡

ኤጀንሲው በከፈተው www.dara.Gov.et ገብተው ቅጾችን በማውጣትና ሲስተሙ የሚሰጠውን ቁጥር በመጨመር አዲስ አበባና ድሬዳዋ በሚገኙት የኤጀንሲው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እየቀረቡ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ ረዳት ኃላፊው ማብራሪያ፣ ኤጀንሲው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 819,535 ጉዳዮችን ለማስተናገድ፣ ለ1,802,297 ተጠቃሚዎች አገልግሎት ለመስጠትና ከዚህ ዓይነቱ መስተንግዶና አገልሎት ላይ 400 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ፣ 803,032 ጉዳዮችን በማስተናገድ፣ ለ1,486,273 ተጠቃሚዎች አገልግሎት በመስጠት 373 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ችሏል፡፡ በዚህም የዕቅዱን 93.2 በመቶ ያሳካ ሲሆን፣ የተሰበሰበውም ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ15 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡

በኤጀንሲው ከ73 ዓመት በላይ የቆዩና ለጥናትና ምርምር የሚያግዙ 471 አቃፊ ሰነዶችም ለብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ መተላለፋቸውንም ገልጸዋል፡፡

በተያዘውም በጀት ዓመት 893,524 ጉዳዮችንና 1,862,593 ተገልጋዮችን በማስተናገድ 450 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ መሆኑንም ረዳት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...