Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ልማት ባንክ 14 ቢሊዮን ብር ገደማ ለማበደር ማቀዱን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከፍተኛ የተበላሸ ወይም መመለሱ አጠራጣሪ ብድር የተከማቸበት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ በ2012 ዓ.ም. ከ13.76 ቢሊዮን ብር በላይ ለማበደር ማቀዱንና በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ከ10.7 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማሠራጨቱን አስታወቀ፡፡ ባንኩ 40 በመቶ የተበላሸ ብድር እንዳስመዘገበ ይታወቃል፡፡  

ባንኩ የ2011 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙንና የወደፊት ዕቅዶቹን በተመለከቱ አጀንዳዎች ላይ ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ዓመታዊ የማኔጅመንት ስብሰባ ላይ እንደተገለጸው፣ በ2012 ዓ.ም. 13.76 ቢሊዮን ብር ብድር ለመልቀቅ እንዳቀደና ከዚህ ውስጥም 11.96 ቢሊዮን ብር ለተበዳሪዎች ለማሠራጨት እንደወሰነ የባንኩ መረጃ ይጠቁማል፡፡

ባንኩ በድረገጹ ያሠፈረው መረጃ  እንደሚያሳየው፣ በ2012 ሒሳብ ዓመት ለፕሮጀክትና ለሊዝ ፋይናንስ ከተሰጠው ብድር ውስጥ 7.87 ቢሊዮን ብር ለማስመለስ አቅዷል፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የዕቅዱን 71 በመቶ ያሳካበትን የ4.93 ቢሊዮን የብድር ዕዳ፣ ለፕሮጀክትና ለካፒታል ሊዝ ፋይናንስ ካዋለው ብድር ላይ እንዳስመለሰ ባንኩ አመላክቷል፡፡

ልማት ባንክ በ2011 ዓ.ም. የነበረውን አፈጻጸም በተመለከተ እንደተጠቀሰው፣ እስከ ሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ 11.8 ቢሊዮን ብር ብድር አፅድቋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 10.76 ቢሊዮን ብር ለተበዳሪዎች አሠራጭቷል፡፡ በተሸኘው በጀት ዓመት ለብድር ፈላጊዎች ለመልቀቅ ያቀደው የገንዘብ መጠን ከዕቅዱ አኳያ ሲታይ አፈጻጸሙ የ138 በመቶ ውጤት የታየበት መሆኑን ባንኩ አስታውሷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ከቦንድ ሽያጭ የ1.3 ቢሊዮን ብር እንዳሰባሰበ ባንኩ አስታውሷል፡፡

የተበላሸ የብድር መጠኑ ከ40 በመቶ በላይ ስለመድረሱና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመገኘቱ በተደጋጋሚ ሲነገርበት የከረመው ልማት ባንክ፣ በተለይ ለሰፋፊ እርሻዎች፣ ያውም ለውጭ የአበባ፣ የጨርቃጨርቅና የቆዳ ኩባንያዎች የለቀቃቸው ትልልቅ ብድሮች አጣብቂኝ ውስጥ ከተውታል፡፡ በቅርቡ ሐራጅ ያወጣበትና ከስምንት ሺሕ በላይ ሠራተኞችን የሚያሰተዳድረው የቱርኩ አይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፣ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ሊመልስለት ባለመቻሉ ፋብሪካውን፣ ያመረታቸውንና ጥሬ ዕቃዎቹን ብሎም ሌሎችም ንብረቶች ለጨረታ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ለግብርና ኢንቨስትመንት ከሰጠው ውስጥ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ሊመለስ የማይችልበት ደረጃ መድረሱን ብሔራዊ ባንክ ማስታወቁና ጠቅላላ የተበላሸ የብድር መጠኑም 40 በመቶ መድረሱን መግለጹ አይዘነጋም፡፡

ከብድር ጋር የተያያዙ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ባንኩን እንደ አዲስ ለማደራጀት በብሔራዊ ባንክ አዲስ ዕቅድ እንዲያቀርብ መታዘዙ አይዘነጋም፡፡ የሰሞኑ የማኔጅመንት ስብሰባ በተመለከተ የወጣው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው ባንኩ ካለበት ችግር ለማላቀቅ ቦርዱ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፎ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ይፋ አድርጓል፡፡ ባንኩ የ2011 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙና የወደፊት ዕቅዶቹን ጠቆም ከማድረጉ በቀር ስለትርፍና ኪሳራው ይፋ ያደረገው መረጃ አልሰፈረም፡፡

በርካቶች ልማት ባንክ በውድቀት አፋፍ ላይ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ሲጽፉና ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡ የባንኩን የካፒታል መጠን ከሥጋት ምጣኔው (ካፒታል አዲክዌሲ ሪስክ ሬሾ) አኳያ የተመለከቱ ባለሙያዎችም የባንኩን ችግሮች አግዝፈው አመላክተዋል፡፡ የካፒታሉና የሥጋት ምጣኔው ለልማት ባንኮች ከተቀመጠው ዝቅተኛው የ15 በመቶ ምጣኔ አኳያ ልማት ባንክ በ13 በመቶዎቹ ላይ የሚገኝ መሆኑም ለፋይናንስ ዘርፉ ባለሙያዎች ባንኩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መገኘት አንዱ ጠቋሚ ነጥብ ነው፡፡

የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 83 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነዶችን በመግዛት ያገኘው ገቢ ያበረከተው አስተዋጽኦ አበርክቶለታል፡፡ 43 ቢሊዮን ብር ከብድርና ከመሳሰሉት መስኮች ያሰባሰበው ገቢ ለባንኩ ሀብት ማደግ ድርሻ እንደነበረው የባንኩ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች