Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የፋርማሲ ዘርፍን በአራት ምሰሶዎች ለመድረስ

ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ ገብርኤል ዳንኤል በአሜሪካ ሜሪላንድ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፋርማሲ ተመርቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በማኔጅመንት ሳይንስ ፎር ሔልዝ ለ17 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ በአሜሪካ ‹‹ኢትዮጵያን ፋርማሲስት ኤንድ ፋርማሲዩቲካል ሳይንቲስትስ አሶሲዬሽን ኢን ዘ ዳያስፖራ›› አባልና አማካሪ ናቸው፡፡ በአሶሲዬሽኑ ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፋርማሲስቶች በሙያችሁ ዙሪያ ትኩረት ያደረገ አሶሲዬሽን አቋቁማችኋል፡፡ እንዴት አቋቋማችሁት?

አቶ ገብርኤል፡- በአሜሪካ ልዩ ልዩ ግዛቶች ውስጥ የምንገኝ ወደ 100 የምንጠጋ የፋርማሲ ባለሙያዎች እንዴት አድርገን ነው በፋርማሲ ዘርፍ አገራችንን መርዳት የምንችለው በሚለው ጉዳይ ላይ ከተወያየን በኋላ፣ ‹‹ኢትጵያን ፋርማሲስት ኤንድ ፋርማሲዩቲካል ሳይንቲስት አሶሲዬሽን ኢን ዘ ዳያስፖራ›› (ኢፓድ) አቋቋምን፡፡ በስቴት ኦፍ ቨርጂኒያ የተቋቋመው ይህ አሶሲዬሽን የቦርድ አባላት ያሉት ሲሆን፣ በአገሩ ሕግ መሠረት ሕጋዊ ዕውቅና አለው፡፡ ከታክስ ነፃ የመሆን መብት አግኝቶም አሜሪካ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ አሶሲዬሽኑ ከተቋቋመ አሥር ወራት ሆኖታል፡፡ የምሥረታውንም ስብሰባ ያካሄድነው በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ነው፡፡ ስብሰባው አሶሲዬሽኑን ለመመሥረት ከማስቻሉም በላይ ሁለት ትልልቅ ጥቅሞችን አስገኝቷል፡፡ ከጥቅሞቹም መካከል አንደኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ከ30 እና 40 ዓመታት በፊት በአንድ ትምህርት ቤት እንማር የነበርነው ጓደኛሞች ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኘንበት አጋጣሚ ሲሆን፣ ሁለተኛው ጥቅም ደግሞ በአሜሪካ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፋርማሲስቶች በአንድ መድረክ ተሰባስበው ለመተዋወቅ መቻላቸው ነው፡፡ ከስብሰባው በኋላ የአባላቱ ቁጥር ወደ 110 ከፍ ብሏል፡፡

ሪፖርተር፡- አሶሲዬሽኑ ሥራውን የሚያንቀሳቅስበት በጀት ከየት ይገኛል?

አቶ ገብርኤል፡- አሁን ለጊዜው የአባላት ወርኃዊ ክፍያ አለ፡፡ ከዚህም ሌላ አንዳንድ ለየት ያሉ ተነሳሽነቶች አሉ፡፡ በዚህም ተነሳሽነት በግለሰብ ደረጃ ከኪሳችን ገንዘብ እያዋጣን የምንተጋገዝባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ወደፊት ግን ዕርዳታ ለጋሾች ድጋፍ እንዲያደርጉልን የመጠየቅ ዕቅድ አለን፡፡

ሪፖርተር፡- አሶሲዬሽኑ በፋርማሲ ዙሪያ ለኢትዮጵያ ምን ዓይነት ዕገዛና ትብብር ያደርጋል?

አቶ ገብርኤል፡- ብዙ ጊዜ ፕሮፌሽናል አሶሲዬሽን የሚቋቋሙት የአባሎቻቸውን ፍላጎት ለማርካት ነው፡፡ ይህኛው ግን ለየት የሚያደርገው በፋርማሲ ዘርፍ ኢትዮጵያን ለመርዳት ዓላማ አድርጎ መነሳቱ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በአሜሪካ ባካሄድነው መሥራች ስብሰባ ላይ ዓላማችንን ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉንን አራት ምሰሶዎችን መርጠናል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ምሰሶ ኢንቨስትመንት ተኮር ነው፡፡ ይህም ማለት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የመድኃኒት ፋብሪካ የማቋቋም እንዲሁም መድኃኒት ማስመጣትና ማሠራጨት ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ይህም ሲባል ለትርፍ ብቻ ያለመ ሳይሆን ጥራታቸውና ፍቱንነታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶችን ለአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች ማቅረብን ቀዳሚ ያደረገ ነው፡፡ በመድኃኒት ዙሪያ የሚታዩትን ወይም የተደረሰባቸውን አዳዲስ ግኝቶችም በተቻለ መጠን ወደ ኢትዮጵያ እንዲደርሱ ሁሉን አቀፍ ጥረት ማድረግ በአንደኛው ምሰሶ ላይ ከታቀፉት ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ሁለተኛው ምሰሶ ደግሞ የአቅም ግንባታ ሥልጠናንና ትምህርትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በአሜሪካ የሚገኙ የአሶሲዬሽኑ አባላት በዕረፍት ጊዜያቸው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በፋርማሲ ትምህርት ቤቶችም ሆነ ከፋርማሲ ጋር ተያያዥነት ላላቸው ባለሙያዎችና ተማሪዎች ሌክቸር የሚያደርጉበትንና የዕውቀት ሽግግር የሚያካሂዱበትን ሁኔታ የማመቻቸትና የማደራጀት ሥራን የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ ሦስተኛው ምሰሶ በፖሊሲና በቁጥጥር አካባቢ የሚኖሩትን አንዳንድ ክፍተቶች አቅም በፈቀደ መጠን እንዲሸፈኑ ለማድረግ የታለመ ነው፡፡ አራተኛው ምሰሶ የበጎ አድራጎት ሥራን ይመለከታል፡፡ ይህም ማለት የኢኮኖሚ አቅም ማነስ ላለባቸው ችግረኛ የፋርማሲ ተማሪዎች ስኮላርሺፕ የመስጠት እንዲሁም መጽሐፍንና ጆርናሎችን የማቅረብ ሥራ ያካትታል፡፡ በተለይ ሴት ተማሪዎች የወር አበባቸው ሲመጣ የሚቆጣጠሩበት ሳኒተሪ ፓድ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት እስከ አራት ቀን ግፋ ሲል ደግሞ እስከ አምስት ቀን ከክፍል/ከትምህርት የሚቀሩበት ጊዜ አለ፡፡ ስለዚህ ይህንን ችግራቸውን ለመወጣት የሚያስችል ተገቢውን ድጋፍ ልናደርግላቸው አስበናል፡፡ እንደ መቄዶኒያ ከመሳሰሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋርም በመድኃኒት አቅርቦት ዙሪያ የምንተጋገዝበት አቅጣጫ ለመቀየስ ተሰናድተናል፡፡    

ሪፖርተር፡- ዕቅዱ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ ከወዲሁ የወሰዳችሁት ዕርምጃ አለ?

አቶ ገብርኤል፡- ዕቅዳችንን ለማሳካት ልዩ ልዩ ዓይነት ዕርምጃዎችን ወስደናል፡፡ ከወሰድናቸው ዕርምጃዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የበጎ አድራጎትና መንግሥታዊ ድርጅቶችን ጎብኝተን አነጋግረናቸዋል፡፡ የሥራ ባህሪያቸው ምን እንደሚመስልም ለመገንዘብ ችለናል፡፡ የጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ በየሄድንባቸው ወይም በጎበኘናቸው ድርጅቶች ሁሉ በጣም ቀና የሆነ አመለካከትና ዝግጁነት እንዳለ ለመገንዘብ ችለናል፡፡ ተመሳሳይ ጉብኝትና ውይይት በድጋሚ እናደርጋለን፡፡ ይህ ዓይነቱ ግንኙነት በዕቅድ ለያዝነው ሥራ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በሚገባ ተረድተናል፡፡

ሪፖርተር፡- በፋርማሲና በፋርማሲዩቲካል ዙሪያ ያለውን ዕድገት፣ ጠንካራና ደካማ ጎን እንዴት ገመገማችሁት?

አቶ ገብርኤል፡- ብዙ ዕድገት ታይቷል፡፡ እኔ ራሴ እዚህ አገር ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ አንድ የፋርማሲ ትምህርት ቤት ብቻ ነበር፡፡ በየዓመቱ የሚመረቁም ተማሪዎች ከአሥር እስከ 12 ቢሆኑ ነው፡፡ ዛሬ ግን የትምህርት ቤቶቹ ቁጥር ወደ 18 ከፍ ሲል በሺዎች የሚቆጠሩ ተመራቂዎች አሉ፡፡ ይህ ቀላል ዕድገት አይደለም፡፡ ለወደፊቱም ዕድገታችን ትልቅ መሠረት ነው፡፡ በመድኃኒት ፋብሪካና የማዘጋጀት ዘርፍን ስንመለከት ደግሞ ድሮ ኢፋርም ይባል የነበረው አንድ መድኃኒት ፋብሪካ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን የፋብሪካዎች ቁጥር ወደ አሥር ከፍ ብሏል፡፡ ይህም ቀላል ዕድገት አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር ቀስ እያለ ነው የሚሻሻለው፡፡ ከጥፋታችን እየተማርን ነው የምንሄደው፡፡ በፋርማሲ ደረጃ ሲታይም ድሮ የነበሩት ፋርማሲዎች በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ ዛሬ ሁሉም ቦታ አሉ፡፡ ይህም ማለት ግን መድኃኒቶች በጥራት ይመረታሉ ማለት አይደለም ወይም በፋርማሲ አገልግሎት ደረጃ ጥሩ የሆነ አገልግሎት እየተሰጠ ነው ለማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በአንድ ፋርማሲ መስኮት ወደ 20 እና 30 ሰዎች ተኮልኩለው ይታያሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የተጠቃሚውን ፍላጎት በጠበቀ መልኩ ሊሻሻል ይገባዋል፡፡ የሚሻሻለውም በየፋርማሲው የቴሌፎን ቦክስ የሚመስል ተሠርቶ ተጠቃሚው ቦክሱ ውስጥ ለብቻው ገብቶ ተገቢውን ምክር አግኝቶና የታዘዙለትን መድኃኒት ተቀብሎ እንዲሄድ የሚያደርግ አሠራር ሲተገበር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር በአዲስ አበባና በሌሎችም አካባቢዎች በሙከራ ደረጃ ተሠርቶ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል፡፡ ስለሆነም በሌሎችም አካባቢዎች ሁሉ መስፋፋት ይኖርበታል፡፡ አልፎ አልፎም የመድኃኒት ዕጥረትም ይታያል፡፡ ይህም እውነት ነው፡፡ ግን እጥረቱ እውነተኛ ነው? ወይስ ሰው ሠራሽ ነው? የሚባለው መታየት ይኖርባታል፡፡ አንድ ዓይነት መድኃኒት ጠፋ ማለት ሌላ ተመሳሳይ የሆነ ወይም ልክ የጠፋውን ዓይነት የመሰለና የሚሠራ ሌላ መድኃኒት የለም ማለት አይደለም፡፡ ባለሙያው በዚህ በኩል ጥንቃቄ ማድረግ፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መሥራት ይገባዋል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን አንዳንድ ጊዜ ከሐኪሞች ጋር ኅብረት መፍጠርን ወይም መስማማትን ይጠይቃል፡፡ የፋርማሲው ባለሙያ የተማረው ስለመድኃኒት ነው፡፡ በዚህ ሙያው ኤክስፐርት ነው፡፡ የሠለጠነውም ሐኪሙን፣ ነርሱንና ሌላውም ሊረዳ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ዓይነቱ መረዳዳትና እምነት መኖር አለበት፡፡ አሁን ግን ፋርማሲ ውስጥ ያለ አንድ ፋርማሲስት የሚታየው መድኃኒት ሻጭ ብቻ በሚመስል መልኩ ነው፡፡ ይህ አመለካከት መቀየር አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማኅበርም በዚህ ዙሪያ ለአባላቱ ትምህርትና መስጠት ፋርማሲስትነት ባለሙያነትና ዕውቀት መሆኑን ሕዝቡ እንዲያውቀው መሥራት አለበት፡፡   

ሪፖርተር፡- በመድኃኒት አጠቃቀም ዙሪያ የሚሰጡት አስተያየት አለ?

አቶ ገብርኤል፡- መድኃኒት በአግባቡ መወሰድ አለበት፡፡ ብቻውንም ምንም ማድረግ እንደማይችል መታወቅ አለበት፡፡ ስለሆነም መድኃኒት የአመጋገብ ሥርዓትን በማስተካከል ሊታገዝ ይገባል፡፡ አመለካከትንና አስተሳሰብንም ማስተካከል ወይም ማረቅ ለመድኃኒት ፍቱንነት የበኩሉን ዕገዛ ያደርጋል፡፡ በተረፈ ጭንቀት ራሱ በሽታ ነው፡፡ ይህንን ለመቆጣጠር ራስን ከአደገኛ ዕፆች ጫትና ትምባሆ መጠበቅ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማዘውተር ቢቻል በዓመት አንድ ጊዜ የጤንነት ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በመድኃኒት ላይ ብቻ ከተተኮረ ሌላውንና በራሳችን ጥረት ልናሻሽል የሚገባውን ነገር ሁሉ እንድንዘናጋ ወይም እንድንረሳ ሊያደርገን ይችላል፡፡ መድኃኒት የምንለው ከውጭ ተሠርቶ የመጣውን ብቻ ሳይሆን የእኛ ወይም የራሳችን የሆኑና ለስንት ዓመታት የተሞከሩ የባህል መድኃኒቶችና ዕውቀቶችንም ነው፡፡ እነዚህም ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በዓለም ቻይና አፍሪካ ውስጥ ደግሞ ጋና በባህል መድኃኒቶቻቸው እንደሚጠቀሙና በዚህም ዝናን እንዳተረፉ ይነገራል፡፡ ከተጠቀሱትና ከሌሎችም አገሮች ተሞክሮና ልምድ በመቅሰም የራሳችን የሆነውን የባህል መድኃኒትና ዕውቀት ልናዳብረው ይገባል፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...