የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሐምሌ 2011 ዓ.ም. ከ2.92 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን 51,174 ቶን ምርት ማገበያየቱን አስታወቀ፡፡ በአንድ ወር ውስጥ በምርት ገበያው ከተገበያዩ 75 ዓይነት ምርቶች ውስጥ 32,291 ቶን ቡና፣ 11,273 ቶን አኩሪ አተር፣ 5,817 ቶን ሰሊጥ፣ 1,765 ቶን ነጭ ቦሎቄና 28 ቶን አረንጓዴ ማሾ ምርቶች እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡
ቡና 63 በመቶ በግብይት መጠንና 81 በዋጋ ቀዳሚነቱን ሲይዝ፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ቡናም በግብይት መጠንና ዋጋ 67 በመቶ ድርሻ በመያዝ ከሰኔ ወር ጋር ሲነጻጸር የ23 የመጠን እንዲሁም የ30 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ተጠቅሷል፡፡
በሐምሌ ከተመዘገበው ግብይት ውስጥ 20,326 ቶን ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ያልታጠበ ቡና በ1.52 ቢሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ የኢሉአባቦራ ቡና 22 በመቶ የግብይት መጠን በማስመዝገብ ብልጫውን ወስዷል፡፡ የጊምቢ 19 በመቶ፣ የቄሌም ወለጋ 13 በመቶ ድርሻ ነበራቸው፡፡ 1,311 ቶን ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የታጠበ ቡና በ92 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ የሲዳማ ቡና የግብይቱን 50 በመቶ ድርሻ ወስዷል፡፡ የይርጋ ጨፌና የሊሙ ቡናዎችም የ23 እና የ13 በመቶ ድርሻ ነበራቸው፡፡
የታጠበ 3,676 ቶን የባለ ልዩ ጣዕም ቡና በ297.83 ሚሊዮን ብር ተገብይቷል፡፡ 1,056 ቶን ያልታጠበ ባለ ልዩ ጣዕም ቡናም በ113.98 ሚሊዮን ብር ግብይቱን አከናውኗል፡፡ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርብ 5,923 ቶን ቡና በ364.9 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ የቡና ግብይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ66 የመጠንና የ73 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ተጠቅሷል፡፡ አማካይ የቡና ግብይት ዋጋም የሰባት በመቶ ጭማሪ እንዳስመዘገበ የምርት ገበያው መረጃ ያሳያል፡፡
በሐምሌ ወር 11,273 ቶን አኩሪ አተርም በ170.2 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ የጎጃም አኩሪ አተር 49 እና 48 በመቶ በዋጋና በመጠን የግብይቱን ድርሻ ይዟል፡፡ እንዲሁም 5,817 ቶን ሰሊጥ በ320.17 ሚሊዮን ብር ሲገበያይ፣ ነጭ የሁመራ/ጎንደር ሰሊጥ 72 እና 73 በመቶ በመጠንና በዋጋ በመያዝ ተገበያይቷል፡፡ የሰሊጥ ግብይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸርም በዋጋ 69 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ በመጠን 57 በመቶ ጨምሯል፡፡ አማካይ የሰሊጥ የግብይት ዋጋም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ8.85 ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በዚህ ጊዜ ውስጥ 1,765 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ35.45 ሚሊዮን ብር ሲሸጥ ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር መጠኑ የ2.14 ጭማሪ ሲያሳይ ዋጋው ግን በ0.27 በመቶ ቀንሷል፡፡ በተጨማሪም በወሩ 28 ቶን አረንጓዴ ማሾ በ791.6 ሺሕ ብር ተገበያይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በተጠናቀቀው 2011 በጀት ዓመት ከ33 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን 681 ሺሕ ቶን የግብርና ምርቶች እንዳገበያየ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡