ሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ በኢትዮጵያ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት መስክ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ በዋቢነት ይጠቀሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ 74 ኩባንያዎች እንዳሏቸውም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥም 26ቱ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አመራር ሥር ይተዳደራሉ፡፡
አንዳንዶቹ ኩባንያዎች በተለያየ መንገድ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እየፈሰሰባቸውና የማስፋፊያ ሥራዎችም እየተካሄዱባቸው እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር ከሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች በሦስቱ ላይ ከ286 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በመመደብ የማስፋፊያ ሥራ ያካሄደባቸውን ድርጅቶች ከሰሞኑ አስመርቋል፡፡
ሐሙስ ነሐሴ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በዘመናዊ መንገድ የታደሱትና የማስፋፊያ ሥራ ተከናውኖባቸው የተመረቁት ሦስቱ ኩባንያዎች ሰሚት ፓርትነርስ፣ አዲስ ጋዝና ፕላስቲክ ፋብሪካ እንዲሁም ዋንዛ ፈርኒሺንግ የተሰኙት ናቸው፡፡ በሦስቱ ኩባንያዎች ላይ 286 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ዕድሳትና ማስፋፊያ እንደተከናወነባቸው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋ ይርዳው (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከሰጡት ማብራሪያ መገንዘብ እንደተቻለው፣ ሰሚት ፓርትነር ኩባንያ በኢንዱስትሪ ማዕከልነት እንዲያገለግልና ለተለያዩ ኩባንያዎችም የማምረቻ ቦታዎችን በኪራይ የማስተላለፍ ሥራ ጀምሯል፡፡ አረጋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ሰሚት ፓርትነርስ ኩባንያ የሥራ አድማሱን በማስፋትና ከዚህ ቀደም የነበረውን እንቅስቃሴ በመቀየር፣ በሪል እስቴት አልሚነት ለመሰማራት የሚችልበትን አደረጃጀት ዘርግቷል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘው 100,000 ካሬ ሜትር ይዞታውን በማልማት ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል፡፡
ድርጅቱ ግንባታቸው የተጠናቀቀና እየተመረተባቸው የሚገኙ፣ በግንባታ ሒደት ላይ ያሉና የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በተለይ ሕንፃና የመሠረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታን በማካተት የኢንዱስትሪ ማዕከል እንዲሆን ታስቦ የሪል ስቴት ሥራውንም በኢንዱስትሪዎች ላይ በማተኮር እያካሄደ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡ በሪል ስቴት ልማት ላይ እንዲሰማራ የተደረገው ሰሚት ፓርትነርስ፣ የኢንዱስትሪ ማዕከልነት ሚናውን በመላበስ ለተለያዩ ኩባንያዎች ማምረቻነት የሚውሉ ግንባታዎችን በማሰናዳት የሚንቀሳቀስ ተቋም እንደሚሆንም ተጠቅሷል፡፡
ሰሚት ፓርትነርስ እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴ ለሞሐ የለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ፣ ለአዲስ ጋዝ ፋብሪካ፣ ለዋንዛ ፋብሪካ፣ ለዘመናዊ የሕንፃ ኢንዱስትሪ ፋብሪካና ለዩናይትድ አውቶ ሜንቴናንስ ኩባንያዎች የገነባቸውን ሕንፃዎች በማከራየት አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻሉንም ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል፡፡ ከተጠቀሱት ውስጥ ሦስቱ በሳምንቱ አጋማሽ ተመርቀዋል፡፡ የሚድሮክ ኢንዱስትሪ ማዕከል ይሆናል የተባለው የሰሚት ፓርትነርስ ይዞታ፣ ለማምረቻነት የሚሆን ግንባታ ከማዘጋጀት በተጨማሪ የመመገቢያ ካፍቴሪያዎች፣ የልብስ መቀየሪያና የመታጠቢያ ሥፍራዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመሮች፣ የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገዶች፣ የአትክልት ሥፍራዎችና የደኅንነት ጥበቃ ማማዎችን አካተው የተገነቡ ናቸው፡፡ የሰሚት ኢንዱስትሪ ማዕከል እንዲህ ያሉ የመሠረተ ልማት አውታሮችን በማካተት አገልግሎቱን ለምርታማነትና ለሠራተኞች ደኅንነት ምቹ የሥራ ከባቢን ለመፍጠር ያስቻለ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡ ሰሚት ፓርትነርስ እንዲህ ያሉትን የመሠረተ ልማት አውታሮች ለመገንባትና ለማስፋፊያ ሥራዎች 170 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን የሚድሮክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስታውቀዋል፡፡ ሰሚት ፓርትነርስ በይዞታው ላይ ሌሎች ፋብሪካዎችን በመገንባት በኪራይ የማስተላለፍ ዕቅድ ያለው ሲሆን፣ ወደፊትም ቢሮዎች፣ የሕክምና ማዕከላት፣ የሕፃናት ማቆያዎችን ለመገንባት ከመንግሥት የሥራ ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የማስፋፊያና የዕድሳት ሥራዎች ተከናውኖላቸው በሰሚት ኢንዱስትሪ ማዕከል ውስጥ ከተመረቁት አንዱ አዲስ ጋዝና ፕላስቲክ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው የምርት አቅሙን ለመጨመር የሚያስችሉት ተጨማሪ ማሽነሪዎች ተገዝተውለት ሥራ እንዲጀምር ተደርጓል፡፡ ይህ ኩባንያ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት አማካይነት ከመንግሥት ተገዝቶ የፕላስቲክና የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ምርቶችን ለማምረትና ለማከፋፈል የተቋቋመ ድርጅት እንደሆነ ይታወሳል፡፡
አረጋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የመንግሥት ድርጅቶች ወደ ግል በሚዛወሩበት ጊዜ ኩባንያው ለሚድሮክ ሲሸጥ አብረውት የተላለፉት የማምረቻ መሣሪያዎች ዕርጅና የተጫናቸው፣ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉና ውጤታማነታቸውም ዝቅተኛ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በመሆኑም የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካትና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ይቻለው ዘንድ፣ ፋብሪካውን በዘመናዊ መሣሪያዎች ማደራጀት አስፈልጓል፡፡ ቀድሞ ከነበረበት አካባቢ ተነቅሎ ወደ ሰሚት ኢንዱስትሪ ማዕከል እንዲዛወር ተደርጓል፡፡ ለኩባንያው ምርት ሥራ የሚውሉ አዳዲስ መሣሪያዎች ተተክልዋል፡፡
ይህንን ኩባንያ ለማስፋፋትና የምርት ሥራዎቹን ለማሻሻል ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገ ሲገለጽ፣ የተለያዩ የፕላስቲክ ምርቶች፣ የጋዝና የኦክስጅን ጋዝ የሚመረቱበት ዘመናዊ ኩባንያ ለመሆን እንደበቃም ተጠቅሷል፡፡ ለአዲስ ጋዝ ማምረቻ ኩባንያ በተደረገው ኢንቨስትመንትም የኩባንያው የማምረት አቅም ከማደጉም በላይ አዳዲስ ምርቶችን በማካተት ሥራውን እንዳሻሻለ ተብራርቷል፡፡ ከምርቶቹ መካከልም ለስታዲየም የተመልካቾች መቀመጫ፣ የወተት ማጓጓዣ ሳጥንና ከፍተኛ የቀለም መያዣ ባልዲዎችን በማምረት የድርጅቱ የምርት ዕድገት እንዲስፋፋ መደረጉን ከአረጋ (ዶ/ር) ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የኩባንያውን አዳዲስ የምርት ዓይነቶች ሲጠቅሱ በዋቢነት ያነሱት የስታዲየም መቀመጫዎችን ነው፡፡ ‹‹በወልድያ ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታዲየም ለተገጠሙት ከ25 ሺሕ በላይ የተመልካች መቀመጫዎች አዲስ ጋዝና ፕላስቲክ ኩባንያ በማምረትና በቦታው በመትከል ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል፤›› ብለዋል፡፡ ኩባንያው ዕድሉን ካገኘ ለስታዲየሞች አገልግሎት መስጠት የሚችልበት አቅም እንደገነባ ገልጸው፣ ለወተትና ለቀለም አምራቾችም የምርት መያዣዎችን እዚሁ በአገር ውስጥ በማምረት አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ጋዝና ፕላስቲክ ኩባንያ በተገጠሙለት ዘመናዊ መሣሪያዎች እየታገዘ ከሚያርታቸው መካከል የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ጋዝ ይገኝበታል፡፡ በተደረገለት የማስፋፊያ ግንባታም 285 ኪሎ ግራም የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ጋዝ የማምረት አቅም ያለው ዘመናዊ መሣሪያ ከአሜሪካ አገር አስመጥቶ በመትከል አቅሙን ለማሳደግ ችሏል፡፡
በአንድ የኦክስጅን ጋዝ ማምረቻ ማሽን ተወስኖ የከረመው አቅሙ በሰዓት 10 ሜትር ኪዩብ ብቻ ለማምረት ያስችለው ነበር፡፡ ከማስፋፊያው በኋላ ግን የማምረት አቅሙን በሰዓት ወደ 18 ሜትር ኪዩብ ለማሳደግ እንዳስቻለው ስለሦስቱ ኩባንያዎች የማስፋፊያ ግንባታ ከቀረበው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል የሆነው ዋንዛ ፈርኒሽንግ ኩባንያም ሦስተኛው ማስፋፊያና ዕድሳት የተደረገለት ድርጅት ነው፡፡ ኩባንያው ከመንግሥት ወደ ሚድሮክ በግዥ የተላለፈ ነው፡፡ በኮምፒውተር በሚታገዙ ዘመናዊ መሣሪዎች እንዲደራጅ ሲደረግ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ለማስፋፊያና ሌሎች ማሻሻያዎች ወጪ እንደተደረገበት ታውቋል፡፡
የዋንዛ ፋብሪካ ማስፋፊያ በዓብይነት የአመራረት ሒደታቸው በሶፍትዌር የታገዘ፣ የተዘጋጁ ዲዛይኖችን ተቀብለው በቀጥታ ማምረት የሚችሉ መሣሪዎች የተገጠሙለት ሲሆን፣ እነዚህም ማንኛውንም ምርት በሚፈለገው ቅርፅና መጠን ለማምረት የሚያስችሉ፣ የእንጨት ውጤቶችን ለማሸግና መጠርዞችን ለማሳመር ተመራጭ መሣሪያዎች ናቸው ያሉት አረጋ (ዶ/ር)፣ በከፍተኛ ወጪ ከውጭ አገር የሚገቡ የእንጨት ውጤቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሪ በማዳን በኩል ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ስለ ማሽኖቹ በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል፡፡
ፋብሪካው እያደገ የመጣውን የቤትና የቢሮ የእንጨት መገልገያ አልያም የፈርኒቸር ምርቶችን ፍላጎት ለማሟላት፣ ዘመናዊ ቴክሎጂዎችን በመጠቀም አምርቶና አሽጎ ወደ መትከያ ቦታቸው ተወስደው የሚገጣጠሙ ምርቶችንም በብዛት እያመረተ ማቅረብ ይችላል ተብሏል፡፡ ያለቀላቸው የእንጨት ምርቶችን ከውጭ ከማስገባት ይልቅ እንዲመረቱ የሚፈለጉትን ውጤቶች በተፈለገው ዲዛይንና ዓይነት በማምረት፣ ከጥሬ ዕቃ ወዲህ ያሉ የማምረቻ ወጪዎችን ሁሉ በአገር ውስጥ ምርቶች በመተካት የውጭ ምንዛሪን ችግርን ለማቃለል ፋብሪካው አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
የማስፋፊያ ግንባታዎቹ በተመረቁበት ዕለት የተገኙት የንግና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ፣ የማስፋፊያ ሥራዎች ለአምራች ኢንዱስትሪው በአርዓያነት እንደሚታዩ ጠቅሰዋል፡፡ ከመንግሥት ተገዝተው ወደ ሚድሮክ የተዛወሩት ኩባንያዎች የነበራቸው የማምረት አቅም ሲጠቀሙባቸው ከነበሩት ኋላ ቀር መሣሪያዎችና የአሠራር ሥርዓታቸው ጋር እንደሚያያዝ አስታውሰው፣ እነዚህን ኩባንያዎች በማሻሻልና በማደስ ውጤታማና ትርፋማ ለማድረግ ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ መዋዕለ ንዋይ ወጪ በማድረግ እንዲለወጡ መደረጋቸው፣ ለአምራች ኢንዱትሪው ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አክለው እንደገለጹት፣ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገቡ የቤትና ቢሮ ዕቃዎች፣ የአልኮልና የለስላሳ መጠጦች መያዣ ሳጥኖችና የቀለም መያዣዎች በአገር ውስጥ ተመርተውና ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ ለገበያ ቀርበው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ብሎም እዚህ የተመረቱትን ወደ ውጭ ለመላክ የማስፋፊያ ግንባታዎቹ ሚና ትልቅ እንደሚሆን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል፡፡