Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር ኃይል አመሠራረትና ተግዳሮቶቹ

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር ኃይል አመሠራረትና ተግዳሮቶቹ

ቀን:

በታደሰ ገብረማርያም

ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ (1923- 1967) ከአልጋ ወራሽነታቸው ጀምሮ በተለያዩ አገሮች በሚያደርጉት ጉብኝት ላይ ለክብራቸው የሚደረግላቸውን ወታደራዊ ሠልፍና ሥነ ሥርዓት እየተመለከቱ ኢትዮጵያም እንዲህ ዓይነት ሠራዊት እንዲኖራት ይመኙና ይፈልጉ ነበር፡፡ እንዲሁም ለውትድርና ሙያ ያላቸው ፍቅርና አክብሮት ከፍተኛ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ለምኞታቸውና ፍላጎታቸው ማሳያ የሚሆነው በቀጣይ ዘመናቸው ዘመናዊ የውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ማቋቋማቸው ሲሆን የፍቅርና የአክብሮት ማሳያቸው ደግሞ በአገር ውስጥ ክብረ በዓልና በውጭ አገር ጉብኝት ላይ ወታደራዊ ዩኒፎርም መልበሳቸው ነው፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም. ንጉሠ ነገሥት ከሆኑ በኋላ ሠራዊታቸውን ዘመናዊ ለማድረግም ልዩ ልዩ ዕርምጃዎችን መውሰድ ቀጠሉ፡፡ ከወሰዱትም ዕርምጃዎች መካከል አንዱና ዋነኛው 12 ወጣቶች ወደ ፈረንሣይ ሄደው በውትድርና ሙያ ሠልጠጥነው እንዲመለሱ ማድረጋቸው ይገኝበታል፡፡ ተመላሽ ሠልጣኞቹም በክብር ዘበኛ ተመድበው በአሠልጣኝነት እንዲያገለግሉ ተደረጉ፡፡ ግርማዊነታቸው ወጣቶቹን ለማሠልጠን ያነሳሳቸው የፋሺስት ጣሊያን ጦር በኦጋዴን በኩል ጠብ በመጫሩና ይህ ዓይነቱንም ጠብ ለመግታት ወይም ለማቆም የተቃና አመራር ሰጪ መኖር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑን የመከላከያ ቬተራን አሶሴሽን ዋና ጸሐፊ ኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር ወንድአፈራሁ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር ኃይል አመሠራረትና ተግዳሮቶቹ

 የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ 127ኛ ዓመት ልደት ባለፈው ወር መጨረሻ በተከበረበት ሥነ ሥርዓት ላይ ‹‹በግርማዊነታቸው ዘመነ መንግሥት የዘመናዊ ጦር ኃይሎች አመሠራረትና አደረጃጀት›› በሚል ርዕስ ኮሎኔል ገብረእግዚአብሔር ባቀረቡት ጽሑፍ እንዳመለከቱት፣ በዚህ ሁኔታ መቀጠል አመርቂ ባለመሆኑና የጣሊያን ጠብ አጫሪነት እየጨመረ በመምጣቱ የጦር ትምህርት ቤትን ማቋቋም ግድ ሆነ፡፡ አሠልጣኞችም ገለልተኛና ወዳጅ ከሆነችው ስዊድን የመጡ ሲሆን፣ 148 ወጣቶችም ለዕጩ መኮንንነት ከርሰ ተመልምለው ጥር 21 ቀን 1927 ዓ.ም. ለሥልጠና ገነት ጦር ትምህርት ቤት ገቡ፡፡ በምልመላውና በዝግጅት ወቅት ግርማዊ ቀዳማዊ  አፄ ኃይለ ሥላሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ምልምሎቹንም በታላቁ ቤተ መንግሥት ተቀብለው አሸኛኘት ባደረጉላቸው ወቅት ‹‹ቤት ያለምሰሶ ሊቆም ወይም ያለ ግድግዳ ከቁር ሊያድን እንደማይችል ሁሉ የጦር ኃይል የሌለው አገር ከአደጋ ሊሰወር አይችልም›› በማለት ዕጩ መኮንኖቹ የተጣለባቸው ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝቧቸዋል፡፡ ሥልጠናው ግን በተያዘለት የጊዜ ሰንጠረዥ መሠረት እንዳይካሄድ ልዩ ልዩ እንቅፋቶች እንደተጋረጡበት ነው ዋና ጸሐፊው የተናገሩት፡፡

የመጀመርያውም እንቅፋት የፋሺስት ጣሊያን ጦር በደቡብ በኩል ድንበር ጥሶ ለመግባት መሰናዶ እያደረገ መሆኑንና በሰሜን በኩል ደግሞ መረብ ወንዝ ተጠግቶ መስፈሩ መታወቁ ነው፡፡ ሁለተኛው ተግዳሮት መንግሥት ቤልጅግ ከሚገኘው ‹‹ፋብሪካ ናሲዮናል›› ልዩ ልዩ ዓይነት የጦር መሣሪያዎችን (ረጃጅምና አጫጭር ጠመንጃዎች፣ መትረየሶች፣ መድፎች፣ ብረት ለብሶ የጦርና ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች) ለመግዛት ያደረገው እንቅስቃሴ መክሸፉ ነው፡፡ ግዥው ያልተሳካውም እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ጣሊያን ማናቸውም የጦር መሣሪያ በቅኝ ግዛቶቻቸው አልፎ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በ1922 ዓ.ም. ማዕቀብ በመጣላቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ግዢው ባይሳካላትም ከ40 ዓመት በላይ ዕድሜ ባለው አሮጌ የጦር መሣርያ ወረራውን መከላከል የሚያስችል ዝግጅቷን እንዳጧጧፈች፣ በዚህም ለዘጠኝ ወራት ያህል በሥልጠና ላይ የነበሩት ዕጩ መኮንኖች ሥልጣን አቋርጠው በመውጣት የጦሩን አመራር እንዲይዙ ግድ ሆነ፡፡ ለእያንዳንዳቸውም የሙሉ መቶ አለቅነት ማዕረግ የተሰጣቸው መሆኑን ከኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዚህም ዘመናዊ ሠራዊት አደረጃጀት በምን እርከንና መሠረት ሊከናወን ይችላል በሚለው ሐሳብ ላይ ምክክር ከተደረገ በኋላ ሁለት ሬጅመንት፣ የትምህርትና ሥልጠና መምርያና ልዩ ልዩ ኪነታዊ ክፍሎች ያሉት አንድ ብርጌድ እንዲቋቋም ተወሰነ፡፡ ብርጌዱም ‹‹ኃይለሥላሴ ብርጌድ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶት የአቋም ሠንጠረዥም በአስቸኳይ ተሠራ፡፡ ከመካከላቸውም ሹመትና ኃላፊነት የተሰጣቸው የብርጌድ ኃይለሥላሴ ዋና አዛዥ ሌተና ኮሎኔል ክፍሌ ነሲቡ፣ ዋና ኤታማዦር ሹም ሌተና ኮሎኔል ነጋ ኃይለሥላሴ፣ የአንደኛ ሬጅመንት አዛዥ ሌተና ኮሎኔል ከተማ በሻህ፣ የሁለተኛ ሬጅመንት አዛዥ ሌተና ኮሎኔል በላይ ኃይለአብ ናቸው፡፡ ስዊድናውያን አሠልጣኞች ደግሞ በአማካሪነት ተመድበዋል፡፡

እንደ ኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር ገለጻ በዚህ መልኩ የተደራጀውም ብርጌድ ለዘመቻ እንዲዘጋጅ ተደረገ፡፡ የፋሺስት ጣሊያን ጦር መስከረም 1928 ዓ.ም. በኦጋዴን፣ በደቡብና በሰሜን ወረራውን በይፋ መጀመሩን ተከትሎ መስከረም 25 ቀን 1928 ዓ.ም. አዲግራትን ያዘ፡፡ ግርማዊነታቸውም ወደ ሰሜን ጦር ግምባር ዘምተው ጊዜያዊ ማዘዣ ጣቢያቸውን ደሴ ላይ አደረጉ፡፡ ብርጌድ ኃይለሥላሴም በፍጥነት ወደ ውጊያው ገብቶ ከክብር ዘበኛ ጦር ጋር እንዲሠለፍ ቢታዘዝም ማይጨው ላይ ተፈታ፡፡

ጃንሆይ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ የፋሺስት ጣሊያን ጦር ቀድሞ አደጋ እንዳያደርስ በማሰብ የብርጌድ ሁለተኛ ሬጅመንት ጣርማ በር ላይ የጠላትን ጉዞ አንዲገታ የተደረገ ሲሆን፣ አንደኛው ሬጅመንትም ሚያዝያ 25 ቀን 1928 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገባ፡፡ ጃንሆይም የስዊድን መኮንኖችን አስጠርተው ስለመልካም ተግባራቸውና ዕርዳታቸው ካመሰገኗቸው በኋላ የቅጥር ውላቸው መሠረዙን ገልጸው አሰናበቷቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ጃንሆይ ወደ ጂቡቲ እንደተጓዙ ነው ዋና ጸሐፊው ያመለከቱት፡፡

ብርጌዱም ወደ ሆለታ አቅንቶ ትግሉን እንደቀጠለ፣ በትግሉም በርካታ ሲቪሎች ስለተቀላቀሉት የመጀመርያውን መጠሪያ ስሙን ቀይሮ ‹‹የጥቁር አንበሳ ጦር›› በሚል መጠሪያ እንደተተካና በጠላትም ላይ የሽምቅ ውጊያውን እንዳፋፋመ ነው የተናገሩት፡፡ ጃንሆይም በስደት ከቆዩበት እንግሊዝ ወደ ሱዳን ተመልሰው አርበኞችን ማሰባሰብና የግንኙነት መሥመራቸውንንም የማጠናከሩን እንቅስቃሴ ተያያዙት፡፡ በዚህም ሱዳን ውስጥ ልዩ ስሙ ‹ሶባ› በሚል ሥፍራ በእንግሊዝ መንግሥት የሚደገፍ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ሠፈር እንዲቋቋም መደረጉን ሳይጠቅስ አላለፉም፡፡

በብዙ ድካምና ጥረት በኋላ በጎረቤት አገር የተቋቋመው ይህ ማሠልጠኛ የአርበኞችን የትግል እንቅስቃሴ በሠለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ፣ ጃንሆይም በቀጥታ የሚያዙት የራሳቸው ጦር ለማግኘት እንዳስችላቸውም ከዋና ጸሐፊ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሠራዊቱን በሠለጠነ መንገድ ማደራጀትና ኢትዮጵያውያን መኮንኖችን እንዲመሩ ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ፡፡ በዚህም መሠረት በጣሊያን ወረራ ወቅት ተቋርጦ የቆየው ሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ሰኔ 1933 ዓ.ም. እንደገና የማሠልጠኑን ተግባር ጀመረ፡፡ 39 ዕጩ መኮንኖችም ሥልጠናውን ተያያዙት፡፡ ቀደም ሲል በስደትና በአርበኝነት የነበሩ መኮንኖቹም ከእንግሊዞች ጋር ተቀላቅለው እንዲያስተምሩ ተደረጉ፡፡ ‹‹ወደፊት የሚቋቋመው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አመራርን ከእንግሊዞች የሚረከቡ መኮንኖችን እናፍራ›› ከሚል ቀና ምኞት በስተቀር ለትምህርት ቤቱ ማቋቋሚያ አዋጅ ወይም ደንብ እንዳላወጣለት ነው ዋና ጸሐፊው ያመለከቱት፡፡

ከዚህም ሌላ እያንዳንዳቸው ሦስት ድጋፍ ሰጪ ሻለቆች ያላቸው በድምሩ አራት ክፍለ ጦሮች ተመሠረቱ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ክፍለ ጦር የክብር ዘበኛ ሲሆን ቀዳሚ ተግባሩም የንጉሠ ነገሥቱን ደኅንነት መጠበቅ ነው፡፡ በሥሩ ካሉት ብርጌዶች አንደኛው ብርጌድ ሐረር ለሚገኘው ሦስተኛ ክፍለ ጦር ተደራቢ ሆኖ በአጋዴን ሲመደብ፣ ሁለተኛው ብርጌድ የወሎና የጎጃምን ጠቅላላ ግዛቶች ይጠበቃል፡፡ ሦስተኛው ብርጌድ ቤተ መንግሥቱንና ንጉሠ ነገሥቱ በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ሁሉ የእጀባ ሥራ ሲያካሂድ፡፡ አዲስ አበባንና አካባቢውንም ይጠብቃል፡፡ እንደየሁኔታው አስፈላጊነት ሦስቱም ብርጌዶች የሚቀያየሩበት አጋጣሚ እንደነበር ከዋናው ጸሐፊ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹የሁለተኛ ክፍለ ጦር በሰሜን ኢትዮጵያ፣ ሦስተኛ ክፍለ ጦር በሐረርጌ፣ አራተኛ ክፍለ ጦር ባሌ ተመደቡ፡፡ ከኮርያ ዘመቻ መልስ የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያን መከላከያን በሰው ኃይል ጨምሮ የማጠናከሩ ሥራ ተያይዘው፡፡ በዚህም ወታደራዊ ተራድኦ ማለትም ‹‹ሚሊተሪ አሲስታንስ ኤንድ አድቫይዘሪ ግሩፕ (ማግ)›› በኢትዮጵያ በቋሚነት ተመድቦ ሙያዊ እገዛ ማድረግ ጀመረ፡፡ የተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎችን ለመቅሰም በየዓመቱ በርካታ መኮንኖችና የበታች ሹሞች ወደ አሜሪካ መላካቸው ቀጠሉ፤›› ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ በ1939 ዓ.ም. የክብር ዘበኛ ጦር አካዳሚ እንዲቋቋም በማድረግ ለሦስት ዓመት የሚሰጥ ወታደራዊ ትምህርት በስዊድኖች ተጀምሮ ማስመረቅ የቻለው ሦስት ኮርሶችን ብቻ ነው፡፡ የተቋረጠውን አካዳሚ ዳግም ለማቋቋም የተነሳሱት ንጉሠ ነገሥቱ በሠለጠነው ዓለም ዘመናዊ አካዳሚዎች እንዳሉ በመረዳታቸውና ከአካዳሚዎችም ልምድ መቅሰም አስፈላጊ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ የእንግሊዝ ሮያል ሳንድህርሰት፣ የፈረንሣይ ሳንሴር ሚሊታሪ፣ የአሜሪካ ዌስት ፖይንት፣ የሕንድ ናሽናል ዲፌንስና የእስራኤል ሚሊተሪ አካዳሚዎችን በመጎብኘትም ተመሳሳይ አካዳሚም በኢትዮጵያ እንዲቋቋም ጽኑ ፍላጎት አድሮባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የሕንድ መንግሥት በኢትዮጵያ ሚሊተሪ አካዳሚ ለማቋቋም ባሳየው ፍላጎትና ባቀረበው ድጋፍ መጠን ተመራጭ ሆነ፡፡ በዚህም የተነሳ በ1949 ዓ.ም. በጄኔራል ራውሊ የሚመራ የሕንድ ከፍተኛ መኮንኖች ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የተወሰኑ አካባቢዎችን ከጎበኘ በኋላ ሐረርና አካባቢው ያለው መልክዓ ምድር ለወታደራዊ ትምህርት መስጫ ተመራጭ መሆኑ በመታመኑ በሐረር ከተማ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጦር አካዳሚ ለመቋቋም ችሏል፡፡

ንጉሠ ነገሥቱም በ1950 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (አዲስ አበባ) ዩኒቨርሲቲ ሄደው ከመጀመርያ ዓመት ተማሪዎች መካከል የተወሰኑትን ወጣቶች መርጠው ለዕጩ መኮንንነት ኮርስ ወደ አካዳሚው እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ አካዳሚውም በሦስት ዓመት ቆይታ 180 ዕጩ መኮንኖችን የመያዝ አቅም ቢኖረውም በዓመት የመቀበል የአቅሙ 60 ዕጩ መኮንኖችን ነበር፡፡ የወታደራዊም ሆነ የአካዳሚው መምህራን በሙሉ ከሕንድ ‹‹ፑና ናሽናል አካዳሚ›› የመጡና በየሦስት ዓመቱ የተቀያየሩ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዋናው ጸሐፊ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው ጀኔራል ራውሌ የአካዳሚው ዋና አዛዥ ሆነው ለብዙ ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በ1959 ዓ.ም. ሜጀር ጄኔራል ኃይሌ ባይከዳኝ ኃላፊነቱን በመረከብ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ አዛዥ ሆነው ተሹመዋል፡፡ አካዳሚውም የመጀመርያውን ኮርሶች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመለመለ በኋላ ቀጣዩን ከ14ቱም ጠቅላይ ግዛቶች ከሚገኙ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 12ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ ወጣቶች እየመለመለ የማሠልጠኑን ሥራ ተያያዘው፡፡

ከቅኝ ግዛት ነፃ ለወጡ የአፍሪካ አገሮችና ከቅኝ ግዛት ለመውጣት ትግል ያካሂዱ ለነበሩ ለነፃነት ታጋዮች አካዳሚው የሥልጠና ዕድል በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ይህ ዓይነቱን ነፃ የትምህርት ዕድል በርካታ ተማሪዎቿን በመላክ በሚገባ የተጠቀመችበት ናይጄሪያ ስትሆን ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ ኤኤንሲና የናምቢያ ታጋዮችም በተደጋጋሚ ጊዜ ገብተው በመሠልጠን እንደተመረቁ ነው ኮሎኔሉ የጠቆሙት፡፡

የወታደራዊ ትምህርቱ ፕሮግራም ከዓመት ወደ ዓመት ዕድገት እያሳየ በመምጣቱ የልዩ ልዩ አገሮች መሪዎች፣ ባለሥልጣኖችና ሚሊታሪ  አታሺዎች፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ ሮያል ሳንድህርሰት ሚሊተሪ አካዳሚ፣ ከፈረንሣይ ሚሊታሪ አካዳሚ አዛዦች እየመጡ አካዳሚውን ጎብኝተውታል፡፡ በሚሰጠውም ትምህርት ተደንቀዋል፡፡ በአካዳሚው የአንደኛ ዓመት ትምህርት የጨረሱ ዕጩ መኮንኖችም ሳንድህርስት ሚሊታሪ አካዳሚ ተልከው በመሠልጠን ተመርቀዋል፡፡ በትምህርታቸውም የላቀ ውጤት ካስመዘገቡት ወጣቶች መካከል ዕጩ መኮንን በኋላ ኮሎኔል ተስፋዬ ትርፌ አንዱ ሲሆኑ መኮንኑም ከንግሥት ኤልሳቤጥ ሁለተኛ የክብር ሻምላ በመሸለም አድናቆትን ተጎናጽፈዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላም ኮሎኔል ተስፋዬና ሻምበል ንጉሤ ተስፋማርያም ወደ እንግሊዝ ተመልሰው በዚሁ አካዳሚ ለአንድ ዓመት እንግሊዞችን አስተምረዋል፡፡

‹‹ይህም የሚያሳየው ነገር ቢኖር ሐረር የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጦር አካዳሚ በተቋቋመ አጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም ዝነኛና ታዋቂ መሆኑን ነው፡፡ ይሁን እንጂ አካዳሚው በ1968 ዓ.ም. በአድሃሪው የሞቃዲሾ መንግሥት የግፍ ወረራ ሰበብ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዕዛዝ ተዘጋ፡፡ ወራሪው የሶማሊያ ጦር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከኢትዮጵያ ተጠራርጎ ሲወጣ አካዳሚው ግን ወደ ቀድሞው ይዞታው እንዲመለስ አልተፈለገም፡፡ ይህ አካዳሚ ለኢትዮጵያ ክብር፣ ለመከላከያ ዕድገትና መከበር የሚጨነቅ መንግሥት ሲመጣ እንደሚከፈት ይታመናል፤›› ብለዋል ኮሎኔል ገብረእግዚአብሔር፡፡

የኦጋዴን መልከአ ምድር አቀማመጥ ሜዳማ ከመሆኑ አኳያ በ1961 ዓ.ም. ‹‹የአሥርኛ ሜካናይዝድ ብርጌድ›› በጅግጅጋ እንደተቋቋመ፣ ይህም ብርጌድ የሦስተኛ ክፍለ ጦርን አቅም እንዳሳደገ፣ ይህ ሁሉ መሰናዶ ጂቡቲ ከፈረንሣይ ቅኝ ግዛት ተለቅቃ ከኢትዮጵያ ጋር የመወሃዷ ጊዜ መቃረቡን ምክንያት በማድረግ የሶማሊያ መንግሥት ችግር ቢፈጥር ቅጽበታዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ወይም ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ እንዲያመች ተደርጎ የተከናወነ ዝግጅት እንደሆነ ነው ያመለከቱት፡፡

እንደ ዋና ጸሐፊው ገለጻ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአገሪቱን የአየር ክልል ለማስጠበቅና ለማስከበር የተቋቋመው በ1936 ዓ.ም. ሲሆን በአጭር ዓመታት ውስጥም በአገር ውስጥና በውጭ አገር በቀሰመው ትምህርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ ከኮሪያ ዘመቻ መልስም ዘመናዊ ተዋጊ ጄት የጦር አውሮፕላኖች ለአየር ኃይል ተሰጠ፡፡ አየር ኃይሉም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትዕዛዝ ኮንጎ በመዝመት አገልግሎት አበርክቷል፡፡ እንዲሁም በቀድሞው የኮንጎ ኪንሳሻ ፕሬዚዳንት ሞቡቱ ሴሴሴኮ ጥያቄ በድጋሚ ዛየር ሄዶ አገልግሏል፡፡ የሞቃዲሾ መንግሥት በ1969 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ላይ በከፈተው ወረራ ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሠራው ተአምር የሚረሳ አይደለም፡፡

በዚሁ የአየር ላይ ውጊያ በርካታ ኢትዮጵያን አብራሪዎች ታሪክ የማይረሳ ጀግንነት ፈጽመዋል፡፡ ከእነዚህም ጀግኖች አብራሪዎች መካከል የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጦር አካዳሚ የሰባተኛ ኮርሰ ምሩቅና የአየር ኃይል ተዋጊ ጀት አብራሪ ብርጋዲር ጀኔራል ለገሰ ተፈራ ይገኙበታል፡፡ ጀኔራል መኮንኑ ከሌሎች የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች ጋር ሆኖ ከፍተኛ ብልጫ የነበረውን የሶማሊያን አየር ኃይል በስድስት ወራት ውስጥ ከሰማይ በማውረድ በምትኩ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአየር የበላይነት እንዲቀዳጅ አድርገዋል፡፡ በዚህም ምድር ጦሩ ያለምንም ሥጋት ወራሪውን ጦር ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ ለማውጣት ጊዜ እንዳልፈጀበት ተናግረዋል፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጦር አካዳሚ በርካታ ምሩቃንም የኢትዮጵያን አየር ኃይል በመቀላቀል አገልግለዋል፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ አየር ኃይል የራሱን አካዳሚ እንዲያቋቋም አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ግርማዊነታቸው የንግድ መርከብን የማስፋፋትና የባህር ኃይልን የማቋቋም ጽኑ ፍላጎት እንደነበራቸው የጠቆሙት ኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር፣ በቀድሞው ቤጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ጣና ሐይቅ ዳርቻ በሚገኘው ጎርጎራ ወደብ ‹‹ዳኘው›› የተባለውን መርከብ ጥር 29 ቀን 1943 ዓ.ም. ሲመርቁ ‹‹ለመሬትና ለአየር ትምህርት ቤት እንዳቋቋምን ሁሉ ለመርከቡም ትምህርት ቤት ለማቋቋም አስበናል›› በማለት ፍላጎታቸውን እንዳንፀባረቁ አስረድተዋል፡፡

ፍላጎታቸውንም ተግባራዊ ለማድረግ ባካሄዱት እንቅስቃሴ መሠረት በቀይ ባህር አካባቢ ቀደም ሲል የጣልያን የባህር መደብ በነበረውና ኮማንዶማሪና አብድልቃድር እየተባለ በሚጠራው ደሴት ላይ የኢትዮጵያ የባህር ኃይል የመሠረት ድንጋይ እንዲጣል በወቅቱ የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ለነበሩት ለቢትወደድ ራስ አንዳርጋቸው መሳይ ትዕዛዝ እንዳስተላለፉ በዚህም መሠረት የመርከበኝነት (ሲ-ሜን) ትምህርት ቤት ተቋቁሞ ታኅሣሥ 23 ቀን 1948 ዓ.ም. በግርማዊነታቸው ተመርቆ እንደተከፈተ ዋና ጸሐፊው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በምፅዋ የባህር ኃይል መደብ ሲቋቋም የመጀመርያው አዛዥ የኖርዌይ ካፒቴን ሐሩሊሰን ሲሆኑ ምልምሎችም ከአዲስ አበባ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ናቸው፡፡ የመጀመርያዋ፣ ፈር ቀዳጇና ዘመናዊ የባህር መርከብ ደግሞ ማርሻል ብሮዝ ቲቶ ለግርማዊነታቸው ያበረከቱላቸው ‹‹ሮዝሜሪ›› ትባላለች፡፡ ግርማዊነታቸው ታኅሣሥ 28 ቀን 1948 ዓ.ም. የባህር ኃይል ኮሌጅን መርቀው እንደከፈቱ፣ የባህር ጠረፍ ጠባቂ ጦር መመሥረትን የሚያመላክት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዚሁ ዕለት እንዳውለበለቡ፣ የባህር ኃይል አባላትንም ወደ ተለያዩ አገሮች በመላክ እንዳስተማሩ ነው ኮሎኔል የተናገሩት፡፡

 በተለይ ‹‹ኢትዮጵያ›› የተባለችው መርከብ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመዘዋወር የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እንዳስተዋወቀች፣ ባህር ኃይሉም በአጭር ጊዜ ችሎታውን በማዳበር ከውጭ ድጋፍ ተላቅቆ በራሱ መርከበኞች ዓለምን በመዞር በበርካታ አገሮች የወደብ ጉብኝት አድርጓል፡፡ በዓለም የሚገኙ ትላልቅ ውቅያኖሶችን በመቅዘፍም ብቃቱን አስመስክሯል፡፡

ግርማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ኢትዮጵያ ዘመናዊና ጠንካራ የጦር ኃይል እንዲኖራት ያደረባቸውን ምኞትና ፍላጎት በጥራትና በበቂ ሁኔታ አሳክተዋል፡፡ ነገር ግን በ1966 ዓ.ም. በተከናወነው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ባሳደጓቸውና ባስተማሯቸው ወታደሮች ተገድለዋል፡፡ ለዘመናት የደከሙበትን የጦር ኃይሎች አደረጃጀት ከማፈራረስ ባሻገር የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ጦር አካዳሚንም ዘጉት፡፡ የሠራዊቱንም ሞራል ለማኮላሸት አዛዦቻቸው በወታደሮቻቸው እንዲገደሉ አደረጉ፡፡ አዛዦቹም ጦራቸውን ለማዘዝ በማይችሉበት ጫፍ ላይ ደረሱ፣ ወታደራዊ ካድሬዎችና ደኅንነቶች ይቆጣጠሯቸው ጀመር፣ በመጨረሻም ሲያቅታቸው የኢትዮጵያን ጦር አጥፍተው እነሱም እንደጠፉ ከኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ