የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች ከዓርብ ሐምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በባንኩ ቅርንጫፎች ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንዳልቻሉና እስካሁንም ድረስ ገንዘብ ለማውጣትና ለማስገባት ረዥም ጊዜ እየወሰደባቸው ለሰዓታት በወረፋ እንደሚጠብቁ በመግለጽ ተቃውሞአቸውን አሰሙ፡፡ ባንኩ በበኩሉ አገልግሎቱን ያጓተተው የተፈጠው ጊዜያዊ ችግር እንደተቀረፈ አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፎች በኩል ገንዘብ ለማንቀሳቀስ፣ በተለይም የክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ ዲጂታል ማሽኖች (ኤቲኤም) በኩል ገንዘብ ማውጣት አዳጋች በመሆኑ፣ በርካታ የባንኩ ደንበኞች በቅርንጫፎቹ ብቻም ሳይሆን በማሽኖቹ ዙሪያ ለሰዓታት ተሠልፈው ሲጠባበቁ ታይተዋል፡፡
ደንበኞች እንደገለጹት፣ በአካልም መታዘብ እንደተቻለው፣ የባንኩ ደንበኞች ገንዘብ ማንቀሳቀስ ያልቻሉት የኔትወርክ ችግር አጋጥሟልና ሲስተም ተበላሽቷል የሚል ምክንያት እየቀረበላቸው ነው፡፡ በአንዳንድ ቅርንጫፎች ለሰዓታት ጠብቀው የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት ቢችሉም፣ በየቅርንጫፎቹ ይታይ በነበረው ከፍተኛ መጨናነቅ ሳቢያ አብዛኛው ተጠቃሚ አገልግሎት ሳያገኝ እንዲመለስ አስገድዶታል፡፡
በኤቲኤም ማሽኖች ገንዘብ ማውጣት አደጋች ሆኖ ሰንብቷል፡፡ የሞባይልም ሆነ የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎትም የማይታሰብ ሆኖ ነበር፡፡ በመሆኑም በኤቲኤም ገንዘብ ለማውጣት ሲሞክሩ የነበሩ ደንበኞች ገሚሱ ሲሳካለት አብዛኛው ማሽኑ ገንዘብ የለውም፣ አሁን አገልግሎት አይሰጥም የሚሉና ሌሎችም ምክንያቶችን ከመስጠት በቀር የተጠየቀውን ገንዘብ ማሽኑ ሳይሰጥ ተጠቃሚውን ይሸኛል፡፡
በቁጠባ ሒሳብ ደብተር መስተናገድ ያልቻሉ ደንበኞች፣ እስከ ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በባንኩ በተፈጠረው ችግር ሳቢያ በወረፋ በተጨናነቁ ቅርንጫፎቹ ውስጥ ለረዥም ሰዓታት ለመጠበቅ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ የግብር ክፍያ ለመፈጸም በማሰብ ሲፒኦ ማሠራት የቸገራቸው አንድ ነጋዴ፣ ዓርብና ቅዳሜ በሁለት ቅርንጫፎች ሲፒኦ ለማሠራት ያደረጉት ሙከራ ድካም ብቻ እንዳተረፈላቸው ገልጸዋል፡፡ በባንኩ ችግር ሳቢያ ሲፒኦ ባለመሥራታቸው በገቢዎች ሚኒስቴር መቀጫ እንዳይጣልባቸው የሠጉት የባንኩ ደንበኛ፣ ለተከታታይ ቀናት የዘለቀውን ይህንን ችግር ገቢዎች ከግንዛቤ ማስገባት አለበት ብለዋል፡፡
ገንዘብ በተፈለገው ጊዜ ማንቀሳቀስ አለመቻል ብቻም ሳይሆን፣ በንግድ ባንክ በኩል ደመወዝ የሚቀበሉ የመንግሥትና የግል ሠራተኞችም ለሳምንት በዘለቀው የባንኩ አገልግሎት መስተጓጎል የወር ደመወዛቸው ወደ ባንኩ ስለመድረሱ ማረጋገጥ ተስኗቸው ሰንብተዋል፡፡ መሥሪያ ቤቶቻቸው ደመወዛቸውን ገቢ ስለማድረጋቸው ያረጋገጡም ወደ ባንክ ሄደው የሠሩበትን ገንዘብ ለማውጣት ሲቸገሩ ታይተዋል፡፡
የኔትወርክ ችግር በተደጋጋሚ በንግድ ባንክ ውስጥ የሚፈጠር ቢሆንም፣ የሰሞኑ ግን የተለየ እንደነበር የባንኩ ተገልጋዮች ተናግረው፣ ባንኩ ስላጋጠመው ችግር ለደንበኞች ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠት እንደነበር በመግለጽ ቅሬታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የኔትወርክ ችግሩንም ሆነ የሲስተም መጥፋቱን ያመጣው ባንኩ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በገባው ውል መሠረት የውኃና የመብራት ፍጆታ ክፍያዎችን ማስተናገድ መጀመሩ ያስከተለው መጨናነቅ ስለመሆኑ የሚገልጹ አልታጡም፡፡
ስጉዳዩ ከንግድ ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቅሰው፣ በኔትወርክ ላይ የተፈጠረ ጫና ያስከተለው ችግር እንደሆነና ችግሩ እንደተከሰተም ቅዳሜና እሑድ በተደረገ ርብርብ ኔትወርኩ ወደ ነበረበት መደበኛ የአገልግሎት አሰጣጥ ተመልሷል፡፡ ችግሩን ያባባሰው በባንኩ የአገልግሎት ኔትወርክ ላይ የተፈጠረው ጫና ሲሆን፣ በዚያም ላይ በርካታ መሥሪያ ቤቶች በባንኩ አማካይነት የሠራተኞች ደመወዝ የሚከፍሉበት ወቅት በመሆኑ መጨናነቅ እንደተፈጠረ ባንኩ አስታውቋል፡፡
ችግሩ ጊዜያዊ እንደሆነና በአሁኑ ወቅትም ሙሉ ለሙሉ መፈታቱን ባንኩ ገልጾ፣ ሰኞና ማክሰኞ የታዩት መጨናነቆች በዕረፍቱ ቀናት አገልግሎት ያላገኙ ደንበኞች ወደየቅርንጫፎቹ በአንድ ጊዜ በመሄዳቸው የተፈጠረ ጫና እንጂ ችግሩ መቀረፉን ባንኩ ይናገራል፡፡ ከ1,450 በላይ ቅርንጫፎቹ ባሻገር የሞባይል፣ የኢንተርኔትና የኤቲኤም ማሽኖቹ በአግባቡ እየሠሩ በመሆናቸው ደንበኞች ወደ ቅርንጫፍ ከመምጣት በእነዚህ እንዲጠቀሙም ባንኩ ጠይቋል፡፡ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት ከ22 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይታመናል፡፡