Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከታሰበው ግማሽ መንገድ የቀረው የወጪ ንግድ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም እየተዳከመ መምጣቱ ሲነገር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዕቅዱ ልክ ሊተገበር አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ ለወትሮው ሲያስገኝ ከነበረውም ያነሰ ገቢ እያስመዘገበ መጥቷል፡፡ ዘንድሮም በ2.67 ቢሊዮን ዶላር የተገደበ ውጤት ዓመቱን ደምድሟል፡፡

እንዳለፉት ተከታታይ ዓመታት ሁሉ የዘንድሮ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከቀደመው ዓመት ዝቅ ማለቱን ሊያቆም አልቻለም፡፡ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ ወጪ ንግዱ በ2011 ዓ.ም. ከዕቅዱ ማሳካት የቻለው 62 በመቶውን ብቻ ነው፡፡ ይህም በዓመቱ እንደሚገኝ ከታቀደው የ4.32 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ሊገኝ የቻለው ግን ከላይ የተጠቀሰው የ2.67 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ብቻ ነው፡፡ ከዓምናው አኳያ በንጽጽር ሲቀመጥም በ170 ሚሊዮን ዶላር አንሶ ተገኝቷል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አኳያ ይገኛል የተባለው ከተገኘው ገቢ ጋር ይነፃፀር ከተባለ፣ ልዩነቱ እጅግ የሰፋ ሆኖ ይገኛል፡፡ በአምስቱ ዓመት የዕቅድ ዘመን ሒደት በ2011 ዓ.ም. የአገሪቱ የወጪ ንግድ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛል ተብሎ ነበር፡፡ በ2012 መጨረሻም አሥር ቢሊዮን ዶላር ሊገኝ እንደሚችል ታቅዶ ነበር፡፡ በዚህ ዓመት መጨረሻ ከተገኘው የ2.67 ቢሊዮን ዶላር አንፃር ይህ የተለጠጠ ዕቅድ ሲመዘን፣ ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ጉድለት አስመዝግቧል፡፡

 የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅዱ እንዲህ ያሉ ሰማይና ምድር የተራራቁ እውነታዎች እየፈተኑት እንደማይሳካ በመረጋገጡ በዕቅዱ የተቀመጡ ግቦች ዳግም ተከልሰዋል፡፡ ይህም ተደርጎ፣ ከጀምሩ የተቀመጡ ግቦች ወደ ታች ተቀንሰውም እንደታሰበው ማሳካት አልተቻለም፡፡ ከሰባት ቢሊዮን ወደ አራት ቢሊዮን ዝቅ የተደረገው የወጪ ንግድ ገቢ በግማሹ ተከናውኗል፡፡ የወጪ ንግዱ ከሚያገኘው ማበረታቻ አንፃር አፈጻጸሙ ቁልቁል ለመውረዱ የተለያዩ ምክንያቶች ሲቀርቡና ሲተነተኑ ቆይተዋል፡፡ ለዘንድሮው ደካማ ውጤት ከመንግሥት የሚቀርቡ ምክንያቶች ግን ከቀደሙት ጊዜያት የተለዩ አይደሉም፡፡   

የዘንድሮውን የወጪ አፈጻጸም በማስመልከት መረጃና ማብራሪያ የሰጡት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ፣ ከወጪ ንግዱ ዘርፍ 70 በመቶ ድርሻ ከሚይዘው የግብርና ዘርፍ ውስጥ በተለይ ቡና፣ ቅባት እህሎች በተለይም ሰሊጥና የጥራጥሬ ምርቶች በብዛትም በጥራትም እንደሚጠበቀው አልተስፋፉም፡፡ የግብርና ምርቶችን የወጪ ንግድ ከዕቅድ አኳያ ማሳካት ያልተቻለበት ዋነኛ ምክንያት ብለው አቶ ወንዱ የሚናገሩት፣ ምርትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ሥራዎች ስላልተሠሩ ነው፡፡ አምራቾችን በቀጥታ ከላኪዎች ጋር የሚያገናኝ አሠራር አለመኖሩ፣ በየጊዜው የዓለም ገበያ ዋጋ መዋዠቁ ትልቅ ጫና ፈጥሯል፡፡

መንግሥት ለወጪ ንግዱ አፈጻጸም መዳከም ባደረገው ግምገማ ደረሰበት የተባለው ችግር ይህ ብቻ እንዳልሆነ ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ ከላኪዎች አኳያ የነበሩ ችግሮችንም አንስተዋል፡፡ ላኪዎች ከገዥዎች ጋር የገቡትን የወጪ ንግድ ስምምነት አክብረው አለመላክ በዋኛነት ተጠቅሷል፡፡ ምርት ሆነ ብሎ ከግብይት ውጭ በማቆየት ዋጋ እስኪጨምር የመጠበቅ ችግርም ተከስቷል፡፡ በተባለው ጊዜ ምርት አለማቅረብ በሰፊው ታይቷል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን፣ አንዳንድ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን የገዙበትንና የሚሸጡበትን ዋጋና የግብይት መረጃ ሆነ ብለው አዛብተው ሲያቀርቡ፣ ከዋጋ በታች ሲሸጡ ተደርሶባቸዋል፡፡ እንደ አቶ ወንድሙ ገለጻ፣ ከአገር ውስጥ ገበያ በውድ እየገዙ ወደ ውጭ ሲልኩ ደግሞ ዋጋውን ቀንሰው እንደሸጡ የሚያሳይ የሒሳብ ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡

ላኪዎች በሚያቀርቡት መረጃ መሠረት የገዙበትና የሸጡበት ዋጋ የሚመዘገብ በመሆኑ፣ ሒደቱ ላይ አሻጥር እንደሚታይ አቶ ወንድሙ ገልጸዋል፡፡ ይህ አካሄድ ከመሸጫ ዋጋ በታች ወይም ‹‹አንደር ኢንቮይስ›› በማድረግ የሚሠራበት ተግባር በመሆኑ የወጪ ንግዱን ጎድቶታል ብለዋል፡፡ እንዲህ ባለው አሠራር የሚያገኙትን ትርፍ የውጭ ምንዛሪ ወደ ጥቁር ገበያ እየወሰዱ በመመንዘር ራሳቸውን ጠቅመው መንግሥትን የሚያከስሩ፣ ባንኮች የሰጧቸው ብድሮችም በቶሎ እንዳይመለስላቸው የሚያደርጉ የንግድ መዛባትን ያስከተሉ ነጋዴዎች ታይተዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ አብዛኞቹ ላኪዎች አስመጪ በመሆን ጭምር ስለሚሠሩ፣ ሆነ ብለው የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሲሉ ከስረው እየሸጡ የሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ በሚያስመጡት ዕቃ ዋጋ ላይ የከሰሩትንም ያወጡትንም ትርፋቸውንና ሌሎች ወጪዎቻቸውን በማከል በውድ ዋጋ በመሸጥ ለዋጋ ግሽበትም ምክንያት እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሕገወጥ ተግባር ወጪ ንግዱን ምን ያህል እንደጎዳው አቶ ወንድሙ እንዲህ በማብራራት የነጋዴዎቹን አድራጎት ‹‹እኩይ›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡

ለወጪ ንግዱ አፈጻጸም ማነቆዎች ከሆኑት አንዱ አምራች ኢንዱስትሪዎች የገጠማቸው የግብዓት እጥረትም ተጠቅሷል፡፡ በዚህ ዘርፍም የጥራት ችግር  ተንሰራፍቶ ይታያል፡፡ ጥሬ ዕቃ የሚያስገቡ አምራቾች የሚገዟቸው ግብዓቶች የጥራት ደረጃ መለያየት ችግር አምጥቷል፡፡ በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ የታየው ሌላው ችግር ባለሀብቶቹ የወጪ ንግድን ሥነ ምግባር አለመጠበቅ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የገቡ ኩባንያዎችም ምርቶቻቸውን ለወጪ ንግድ ብቻ ማቅረብ አለመቻል፣ አንዳንዶቹም ከውል ውጪ ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረባቸውም የወጪ ንግዱን በዕቅዱ አግባብ እንዳይራመድ አስገድደውታል ይላሉ፡፡ በፋብሪካ ውጤቶችም ሆነ በግብርና ምርቶች ላይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የተንሰራፋው የፖለቲካ አለመረጋጋትነ የሰላም መጥፋትም ለወጪ ንግዱ ማነቆ እንደነበር አቶ ወንድሙ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የወጪ ንግድ አፈጻጸም በታቀደው ልክ ላለመሆኑ ሰርክ የሚነሳው የኮንትሮ ባንድና የሕገወጥ ንግድ ዘንድሮም በምክንያትነት ቀርቧል፡፡ በተለይ የማዕድን ዘርፉ የወጪ ንግድ በምሳሌነት ቀርቧል፡፡ በዓመቱ ዘርፉ ያስመዘገበው የስምንት በመቶ ውጤት ብቻ ነው፡፡ በአገሪቱ ከሰፈነው አለመረጋጋት አኳያ፣ የማዕድን ውጤቶች እንደ ልብ አለመመረታቸው፣ የተመረቱትም በበቂ መጠን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ባለመቅረባቸው፣ ከዘርፉ የታሰበው ገቢ አልተገኘም፡፡ የማዕድን ምርት ወደ ጎረቤት አገሮች በሕገወጥ መንገድ በገፍ እየወጣ ይሸጣል፡፡ በጥቁር ገበያ የደራ ንግድ ጦፏል፡፡

በጥቅሉ የወጪ ንግዱ አፈጻጸም መዳከሙ ታይቶም በቶሎ መላ ሊበጅለት አልቻለም፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ግን እነዚህን ችግሮች እንዴት ሊፈታ እንደሚችል በሚገባ ማቀዱን ከመናገር አልተቆጠበም፡፡ እንደ አቶ ወንድሙ ገለጻ፣ በ2012 በጀት ዓመት እንደሚገኝ የታቀደውን የ4.69 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማሳካት የተለያዩ ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡ መፍትሔ የተባለውም አጠቃላይ የንግዱን ዘርፍ ሪፎርም ማድረግ ነው፡፡

በሪፎርሙ መሠረት የእያንዳንዱን ላኪ ስምምነት መቆጣጠር አንደኛው መንገድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል የሚገበያዩ ምርቶችም ከምርት ገበያው ውጭ እንደይሸጡ፣ ምርቶች ለውጭ ገበያ ሲቀርቡም ምርት ገበያው ፈቃድ መስጠት እንደሚኖርበትና ለጉምሩክ ይለፍ መጻፍ እንዳለበት ሪፎርሙ ይጠይቃል፡፡ ማረጋገጫ ከምርት ገበያው ያልተጻፈላቸው ምርቶች መንቀሳቀስ እንዳይችሉ በማድረግ የመቆጣጠር ሥራ ይሠራል ተብሏል፡፡

በመፍትሔነት ከተጠቀሱት ውስጥ ሌላኛው፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የላኪዎችን ፈቃድ ትክክለኛነት የሚያረጋግጥበት አዲስ አሠራር መዘርጋቱ ነው፡፡ ይህን ሥራ በቅርቡ እንደሚጀምር ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ የላኪዎች ፈቃድም በየጊዜው ኦዲት ይደረጋል ተብሏል፡፡ ለወጪ ንግዱ የሚሰጠው ማበረታቻ ሳይጓደል፣ የቁጥጥር ሥራው ግን ጥብቅ እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡

የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከልም በፊት ከነበረው በተለየ አኳኋን የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በቅንጅት እንደሚሠሩ ተገልጿል፡፡ ‹‹የእኛን ምርት ጎረቤት አገሮች የራሳቸው ምርት አስመስለው በስማቸው መሸጥ የለባቸውም፤›› ያሉት አቶ ወንድሙ፣ በመንግሥት ውሳኔ ስለተሰጠበት ይህን ለመከላከል በቅንጅት ይሠራበታል በማለት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር የተሻለ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ለማግኘት ርብርብ እንደሚደረግ አክለዋል፡፡ ከግብርና ምርቶች አኳያም ለአርሶ አደሩ መንግሥት ባስቀመጠው ስትራቴጂ መሠረት ምርቱን በጥራትና በብዛት የሚያሳድግባቸው ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ የግብይት ሰንሰለትን ማሳጣር ሌላው የመፍትሔ ዕርምጃ ነው፡፡

የወጪ ንግዱ ላይ የሚሳተፉት ባለሀብቶች እንዲበዙ በማድረግ የተሻለ ለመሥራት ስለመታቀዱ ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፣ መንግሥት ለላኪዎች ከሚያደርገው ድጋፍ ጎን በፊት ከነበረው በተለየ ኦዲት መደረግ ስለሚጀምር በጥናት የተደገፈ ዕርምጃ ይተገበራል ብለዋል፡፡ የላኪዎችን ፈቃድ ኦዲት ለማድረግ የታቀደው ደግሞ ትክክለኛውን ላኪ ትክክለኛ  ካልሆነ የሚለይበት ምክንያት ለመደገፍ ብቻ ሳይሆን ዕርምጃ ለመውሰድ ነው፡፡

አምራች ኢንዱስትሪው አንድ ቢሊዮን ዶላር እንዲያስገኝ ይጠበቃል፡፡ ይህም ከጠቅላላው የወጪ ንግድ ገቢ 27 በመቶውን የሚወክል ሲሆን፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንደ ልብ ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻች፣ የአገር ውስጥ ባለሀብት በኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገባ በማድረግ ጭምር ምርት እንዲበራከት በማድረግ የታቀደውን የወጪ ንግድ ገቢ ለማሳካት መንግሥት ማቀዱ ተብራርቷል፡፡

ንግድ ሚኒስቴር ለወጪ ንግዱ መዳከም እንደ ምክንያት ያቀረባቸውና የመፍትሔ ሐሳቦች ያላቸውን ውጥኖች እንዴት እንደሚያሳካቸው ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ላኪዎች ግን የተለየ ሐሳብ አላቸው፡፡ በተለይ ላኪዎችን ለመቆጣጠር ተብሎ የወጣው አሠራር ብልሹ ላኪዎችን በተወሰነ ደረጃ ለማስቆም ቢያስችለው እንኳ፣ የወጪ ንግዱን የጎዳው ዋናው ችግር ግን ወሳኝ የሆኑ የግብርና ምርቶች በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ብቻ ይገበያዩ መባላቸው ነው፡፡

የምርት ገበያው አሠራር የወጪ ንግዱን ምን ያህል እንደጠቀመና እንደጎዳው መንግሥት በሚገባ ማጥናት እንዳለበት ያሳሰቡት እኚሁ ላኪ፣ በነፃ ገበያ መርህ ከምርት ገበያው ውጭ ግብይት እንዲኖር መፈቀድ አለበት ብለዋል፡፡ በምርት ገበያ ብቻ ተገበያዩ የሚለው አሠራር መላክ የሚገባን ምርት እንዳይላክ አድርጓል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሊታዩ ይገባል ብለዋል፡፡ ችግሩ ይህ ብቻ ባይሆንም ለምሳሌ ለግብርና ምርቶች የውጭ ምንዛሪ ግብይት መዳከምና ለኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት አንዱ ምክንያት አጠቃላይ የግብይት ሒደቱ በመሆኑ፣ መንግሥት ግብይቱን በነፃ ገበያ ሥርዓት ማካሄድ በግድ በምርት ገበያው ብቻ ይሁን የሚለውን በመተው በአማራጭ በግብይት ቢደረግ ነገሮች ሊለወጡ ይችላል ይላሉ፡፡

በ2012 ዓ.ም. ከወጪ ንግዱ መንግሥት ለማግኘት በዕቅድ የያዘው መረጃ እንደሚያሳየው 4.69 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 3.32 ቢሊዮን ዶላር ወይም 70.8 በመቶ የሚሆነውን ከግብርና ምርቶች፣ 1.02 ቢሊዮን ዶላር ወይም 21.7 በመቶ ከማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ 265.8 ሚሊዮን ዶላር ከማዕድን ዘርፍና 83.6 ሚሊዮን ዶላር ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭና ከሌሎች ምርቶች እንደሚገኝ ታቅዷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች