Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያን እግር ኳስ ማቅ ያለበሰው የካፍ ውሳኔ

የኢትዮጵያን እግር ኳስ ማቅ ያለበሰው የካፍ ውሳኔ

ቀን:

በከፍተኛ በጀት ታንፀው ለአገልግሎት የዋሉት የኢትዮጵያ “ዘመናዊ ስታዲየሞች” ተገቢውን ዝቅተኛውን መሥፈርት አላሟሉም ተብለው ኢንተርናሽናል ውድድሮች እንዳይካሄድባቸው ታገዱ፡፡ ዕግዱን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው ደብዳቤ ያሳወቀው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ሲሆን፣ ምክንያቱም የሐዋሳ፣ የባህር ዳር፣ የመቐለና የድሬዳዋ ስታዲየሞችን ጨምሮ አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየም ለኢንተርናሽናል ጨዋታ ብቁ አይደሉም በሚል እንደሆነ ታውቋል፡፡

ስታዲየሞቹ ከዚህ ቀደም በተደረገባቸው ግምገማ አኅጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ያላሟሏቸው መሠረታዊ ይዘቶችን በመገምገም ካፍ ማስጠንቀቂያም ምክርም ለሚመለከታቸው የአገሪቱ የስፖርት አመራሮች ሲያደርስ ስለመቆየቱ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እ.ኤ.አ. 2019 ዕግዱን ይፋ ባደረገበት ደብዳቤ አካቷል፡፡

ካፍ እ.ኤ.አ. በ2020 የሚያከናወነውን የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ ኢትዮጵያ እንደምታሰተናግድ ዕድሉን ከሰጣት ዕለት ጀምሮ እያደረገች ያለውን ዝግጅት ምን እንደሚመስል በየጊዜው ሙያተኞችን በመላክ ሲገመግም መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በዚሁ መሠረትም ተቋሙ ከአንድ ዓመት በፊት ባስተላለፈው ውሳኔ የአስተናጋጅነቱን ዕድል ከኢትዮጵያ ነጥቆ ለካሜሩን መስጠቱ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

በአኅጉራዊ የእግር ኳስ ተቋም የተላለፈው ውሳኔ በተደጋጋሚ የቀረቡ  ማሳሰቢያዎችና ማስጠንቀቂያዎች ሰሚ ማጣታቸውን ተከትሎ የመጣ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወቅቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ስለዕገዳው እውነትነት ብቻ ሳይሆን፣ ውሳኔው ለአገሪቱ እግር ኳስ ትልቅ ጉዳት እንዳለው ያስረዳሉ፡፡

ካፍ የስታዲየሞቹ መታገድ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያሳወቀው ሐምሌ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለመንግሥታዊ አካሉ ስፖርት ኮሚሽን ያሳወቀው ሐምሌ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየም ሙሉ እድሳት ሳይደረግለት ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንደማይችል፣ በተጨማሪም ምንም እንኳ “ዘመናዊ” የሚለውን ስያሜ ቢይዙም ባለመጠናቀቃቸው ግን የመቐለ፣ የባህር ዳር፣ የሐዋሳና የድሬዳዋ ስታዲየሞች የካፍን ዝቅተኛ ስታንዳርድ ያላሟሉ በመሆናቸው በተመሳሳይ ማናቸውንም ኢንተርናሽናል ጨዋታ እንዳያጫውቱ መታገዳቸው አሳውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካሜሩን ለምታስተናግደው እ.ኤ.አ. 2020 የቻን ውድድርና እ.ኤ.አ. በ2021 ለሚከናወነው ዋናው የአፍሪካ ዋንጫ፣ እንዲሁም፣ እ.ኤ.አ. ለ2022 የዓለም ዋንጫ የምድብና የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ፕሮግራም ወጥቶለት ተጋጣሚ አገሮቹም ተለይተው ታውቀዋል፡፡ እንደ ካፍ ውሳኔ ከሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከእንግዲህ በሜዳው የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ተሰርዘው፣ በተመረጡ የጎረቤት አገሮች ሜዳዎች ዕጣ ፈንታውን አንደሚወስንም አስታውቋል፡፡

 ብሔራዊ ቡድኑ በሚቀጥለው ዓመት ለሚካሄደው ለቻን ዋንጫ የመጀመርያውን ማጣሪያ ከጂቡቲ አቻው ጋር ተጫውቶ ወደ ተከታዩ ዙር የሚያሳልፈውን ውጤት ይዟል፡፡ ከውጤቱ ባሻገር የብሔራዊ ቡድኑ ወቅታዊ አቋምም እንደ ስታዲየሞቹ ሁሉ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ የሁለቱን ብሔራዊ ቡድኖች የደርሶ መልስ ጨዋታ የተከታተሉ ሙያተኞች ከወዲሁ ሥጋታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡

‹‹በዕንቅርት ላይ. . .›› እንዲሉ በማንነት ፖለቲካ በመታመስ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደተባባሰ የውርደት አዘቅጥ እንዲገባ ምክንያት ከመሆኑም አልፎ፣ የዕግድ ውሳኔው በቀጣይ አኅጉራዊ ተሳትፎ የሚጠብቃቸው ሁለቱ መቐለ 70 እንደርታና ፋሲል ከተማ ክለቦች ኢንተርናሽናል ጨዋታዎቻቸውን የሚያደርጉት ካፍ ዕውቅና በሰጣቸው የጎረቤት አገሮች ስታዲየሞች በመሄድ ለመጫወት ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

ለዚህ ሁሉ መንስዔው ካፍ በየጊዜው ለሚሰጣቸው ማሳሰቢያዎች ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠት ብሎም ለሚቀርቡት ማስጠንቀቂያዎች የማሻሻያ ሥራዎች በ“ጆሮ ዳባ ልበስ” በመታለፋቸው እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይህንኑ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የፌዴሬሽኑ አመራሮችና ሌሎችም ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡

ይህ የካፍ ዕርምጃ ወትሮውም መርህ አልባ በሆኑ ማንነት ላይ ባተኮሩና በስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት ሲንገዳገድ የከረመውን እግር ኳስ ከድጡ ወደ ማጡ የከተተ፣ ማቅ ያለበሰ ስለመሆኑ የእግር ኳሱ አመራሮችና ሙያተኞች የሚገልጹት የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ዕግዱ የጊዜ ገደብ የሌለው፣ ለውጥና ማስተካከያዎች ቢደረጉና ካፍም ቢቀበላቸው ዕግዱን ወዲያውኑ ሊያነሳ የሚችልበት አግባብ ስለመኖሩ፣ አልያም ዕገዳውን አፅንቶ እስከ መቼ ሊቆይ እንደሚችል በዕገዳው ያስቀመጠው ጉዳይ አለመኖሩ ይበልጥ አሳሳቢ እንዳደረገውም እየተነገረ ይገኛል፡፡

በዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ ‹‹ውሳኔው ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ትልቅ ጉዳት ያስከትላል፣ ይሁንና ውሳኔውን ተከትሎ ከካፍ ሰዎች ጋር እየተገናኘን ነው፡፡ በመሆኑም ካፍ በተለይ በመቐለና በባህር ዳር ስታድየሞች ላይ ያለው አመለካከት የለዘበ መሆኑ፣ ይህንኑ ለመቐለ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች አሳውቄ የክልሉ መንግሥትም ተጨማሪ ፋይናንስ በመመደብ ስታዲየሙ ላይ ያልተሟሉ ግንባታዎችን እያከናወነ መሆኑን እንደሚገኝ፣ በፌዴሬሽኑ የካፍ የክለብ ላይሰንሲንግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ተድላ ዳኛቸው ቦታው ድረስ ሄደው ያረጋገጡ መሆኑንና ይህንኑ በፎቶና በቪዲዮ ጭምር ማስረጃ በማስደገፍ ለካፍ እንዲላክ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ ስታዲየምን በተመለከተ ግን የከተማ አስተዳደሩ ስታዲየሙን በማደስ ላይ በመሆኑ የግንባታ ዕቃዎች በዚያው የሚገኙ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ችግር እንደሌለው፣ ስታዲየሙ እሑድ ሐምሌ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያንና የጂቡቲ ብሔራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታቸውን ባደረጉበት ዕለት፣ የጨዋታው ኮሚሽነር ጨዋታው በዝግ እንዲሆን ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ያደረጋቸው ዋናው ምክንያትም ለስታዲየሙ ግንባታ በሚል በየቦታው የወዳደቁ ቁሳቁሶች ባለመነሳታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከዚህ ባለፈ የካፍ ውሳኔ ትክክለኛና ተገቢ እንደሆነ፣ ግንባታቸው ተጀምሮ ዓመታትን ያስቆጠሩት የክልል ስታዲየሞች እንዲጠናቀቁ በተለይም በካፍ ዕገዳ የተላለፈባቸው ስታዲየም ባለቤቶች ለትግራይ ወጣቶችና ስፖርት፣ ለአማራ ወጣቶችና ስፖርት፣ ለድሬዳዋ አስተዳደርና ለደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ከየክልሎቻቸው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመነጋገር የስታዲየሞቹ ግንባታ የሚጠናቀቅበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹና ጉዳዩን እንዲያውቁት የካፍን ውሳኔ በማያያዝ የተላከላቸው ስለመሆኑ ጭምር አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል፡፡

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...