Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንገዶች ባለሥልጣን ከራሱ የጀመሩ የለውጥ ግንባታዎች ጀምሯል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለ91 መንገዶች ከ150 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦለታል

በተለያዩ መጠሪያዎች እንደ አዲስ ሲዋቅርና ሲደራጅ ከ67 ዓመታት በላይ የዘለቀው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ በመንገድ አውታር ዝርጋታ ሥራ ትልቁን የኃላፊነት ሚና በመጫወት ለዓመታት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡

ከፍተኛ በጀት ከሚመደብላቸው መንግሥታዊ ተቋማት ትልቁን ድርሻ በመያዝ ይጠቀሳል፡፡ ይህ መሥሪያ ቤት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዋና መሥሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ጀምሮ ሰፋፊ የመዋቅር ለውጦችን እየተገበረ ይገኛል፡፡ የሥራ ከባቢን ምቹ በማድረግና ዘመናዊ አሠራር በመተግበር ውጤታማነታቸው ከሚነገርላቸው መሥሪያ ቤቶች አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ለውጡ ከመሥሪያ ቤቱ ዋናው መግቢያ በር ጀምሮ ይታያል፡፡ የቀድሞ ገጽታው በአያሌው ተቀይሯል፡፡ በነባሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ በታነጸው አዲሱ ሕንፃና በቀድሞው ሕንፃ መካከል የሚገኘው የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ ዓይነ ግቡ በሆነ ዲዛይን ተውቦ በአበባና በአረንጓዴ ተክሎች ተከቧል፡፡

ቢሮዎችን ለሥራና ለሠራተኛ እንዲሁም ለባለጉዳይና ለእንግዳ ምቹና ተስማሚ ሆነው ተደራጅተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ከአንድ ዓመት ተኩል ወዲህ የተከናወነ ነው፡፡ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) እንደሚገልጹት፣ ይህ ሁሉ የሚደረገው ምቹ የሥራ ቦታ ለመፍጠርና የሥራ ተነሳሽነትን ለማሳደግ ነው፡፡ የሥራ ከባቢን ምቹና ፅዱ ማድረግ ትልቅ ፍልስፍና እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በአንድ ዓመት ውስጥ የተቋሙን ነባር ገጽታ በመቀየር ለሠራተኞች ምቹ በማድረግ  የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል በማሰብ እንደሆነ ያክላሉ፡፡

ሠራተኞች ደስተኛ ካልሆኑ ደንበኞችን በሚገባ ለማስተናገድ ይቸገራሉ፡፡ ደረጃውን ባልጠበቀ የሥራ ቦታ ያውም በአነስተኛ ደመወዝ፣ ጫና በሚበዛበት የሥራ ደርሻ ውስጥ ሆነው እንዲያስተናግዱ ማድረግ ተገቢ ባለመሆኑ ተቋሙ ከደመወዝ ውጭ ያለውን ማንኛውንም አሠራሩን በተቻለ አቅም እያስተካከለ ይገኛል፡፡

የሥራ ቦታውን ለደንበኛውም ቢሆን ዓይነ ግቡ ለማድረግ መሠራቱን የሚያሳይ ሲሆን፣ ከባቢውን ምቹ ለማድረግ የተሠራው ሥራ ጎልቶ የሚታይ በመሆኑ ሠራተኞች ቢሮ እያደሩ መሥራት እንዲችሉ ጭምር ታስቦ የተደረገ ነው ተብሏል፡፡

እንዲህ ባለው ድባብ የመሥሪያ ቤቱን ዕይታና ገጽታ መለወጥ የቻለውና በዚሁ መስክ ተጨማሪ ሥራ እያከናወነ የሚገኘው መንገዶች ባለሥልጣን፣ በዋና ዋና ክንውኖቹ ላይ የሰጠው መግለጫ አገሪቱ አሁንም ለመንገድ ሥራ ከፍተኛ በጀት መመደቧን የሚያመላክት ነው፡፡ በርካታ ተግዳሮቶች የተደገኑበት ስለመሆኑም የሚያመላክት ነው፡፡ ይኸውም በ2011 በጀት ዓመት ባለሥልጣኑ ለማከናወን ያቀዳቸውን ተግባራት በዕቅዱ ልክ አለማከናወኑ አንዱ ነው፡፡

የ2011 ዓ.ም. አፈጻጸምን በማስመልከት ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት ማብራሪያ፣ በመንገዶች ግንባታና ከባድ ጥገና 3,558 ኪሎ ሜትር ለመሥራት ታቅዶ ማከናወን የተቻለው 2,215 ኪሎ ሜትር ነበር፡፡ አፈጻጸሙም 62 በመቶ ነው፡፡ አፈጻጸሙ የቀነሰው በውጫዊና ውስጣዊ ተፅዕኖች እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ከሌላው ጊዜ በተለየ በርካታ ፕሮጀክቶች በደካማ አፈጻጸም ሳቢያ መቋረጣቸውን በዋቢነት ጠቅሰዋል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ለመጪው ዓመት ሥራም እንቅፋት ነው፡፡

የ11 ፕሮጀክቶች የጨረታ ሒደት መጓተት፣ ወሰን የማስክበር ሥራን በቶሎ ማጠናቀቅ ባለመቻሉ ተፅዕኖ መፈጠሩን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ውጫዊ ተፅዕኖች ቢኖሩም አፈጻጸሙ ከ2010 ዓ.ም. አንፃር ሲታይ፣ ዘንድሮ በተወሰነ ደረጃ ከፍ ማለቱ አልቀረም፡፡ የመንገድ ግንባታና ጥገና አፈጻጸሙ ከዕድገትና ትራንስፎርሜሸኑ ዕቅድ አንፃር ሲታይም፣ በአራት ዓመታት ውስጥ የተከናወነው ሥራ መልካም እንደሚባል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በአምስት ዓመታት ውስጥ እንደሚከናወን የታቀደው ከባድ የጥገና ሥራ 16,740 ኪሎ ሜትር ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም 12,337 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ታቅዶ እስካሁን 11,445 ኪሎ ሜትር ወይም 93 በመቶ ተከናውኗል፡፡

በ2011 ዓ.ም. የ45 ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ ውሎች እንደተፈረሙ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ ውስጥ የግማሹ ዋና ሥራ ተጀምሯል፡፡ ለቀሪዎቹም አስፈላጊ የግንባታ ቁሳቁሶችን በማጓጓዝና በካምፕ ግንባታ ሥራዎች ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም ከግንባታ ሥራ ጋር በተያያዘ ፈታኝ ሆኖብናል ያሉት የግንባታ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ቶሎ ሥራ መጀመር አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም. ከተፈረሙት 45 ፕሮጀክቶች ውስጥ ግማሽ ያህሉ ብቻ ወደ ሥራ መግባታቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ቀሪዎቹ አልተጀመሩም፡፡ ለ2011 በጀት ዓመት ከመንግሥት የተመደበው 28 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ ገንዘብ ሥራ ላይ እንደዋለም ጠቅሰዋል፡፡

 የባለሥልጣኑን የ2012 ዕቅድ በተመለከተ ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው፣ ከ150 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው 91 ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ይጀመራል፡፡ በ2012 ዓ.ም. መንግሥት ለመንገዶች ባለሥልጣን ሲመድብ ከነበረው በላይ በጀት እንደለደለ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በአጠቃላይ በ2012 ዓ.ም. ለ91 ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚወጣው ጨረታ ትልቅ ገበያ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ በአንፃሩ  ለዚህን ያህል ኢንቨስትመንት ገበያውን ማግኘት ከባድ እንደሚሆንም ተወስቷል፡፡ 69  ፕሮጀክቶች ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ በበጀት ዓመቱ ይሠራሉ ከተባሉት ፕሮጀክቶች ውስጥ ከአዳማ እስከ አዋሽ የሚዘረጋው የመጀመርያው 60 ኪሎ ሜትር መንገድ በአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ የሚገነባ ነው፡፡ 16 ነባር ፕሮጀክቶችም ጨረታቸው በመጪዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ ይፈረማሉ ተብሏል፡፡

በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከአዳማ አዋሽ ግማሽ ጀምሮ እስከ ድሬዳዋ፣ በመንግሥትና በግሉ ሴክተር የጋራ ትብብር ለመሥራት የአዋጭነት ጥናት ይከናወናል፡፡ የፕሮጀክቱ አዋጭነት ከታየ በኋም ይተገበራል ተብሏል፡፡ ሌሎች በአዲስ አበባ በሁሉም መስመሮች የፍጥነት መንገድ ለመገንባት የሚያስችል የመጀመርያ ደረጃ ጥናት በዚህ በጀት ዓመት ይካሄዳል፡፡

 ከአዲስ አበባ ጫንጮ፣ ከአዲስ አበባ ጅማ፣ ከአዲስ አበባ ፍቼና ከአዲስ አበባ ደብረ ብርሃን የሚያገናኙ የፍጥነት መንገዶች ለግንባታ ታቅደዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ይሠራሉ ከተባሉት ሥራዎች መካከል አሰብ ኮሪደር ይጠቀሳል፡፡ ከኤርትራ ጋር የሚገናኙ ሁለት ድልድዮችን የመሥራት ሐሳብ እንዳለ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ትልቁ እንደሆነ የሚጠቀሰውና ችግር ውስጥ እንደገባ የሚነገርለት ፕሮጀክት በባህር ዳር ከተማ የሚገነባው የዓባይ ድልድይ ነው፡፡ የድልድዩ ሥራ በበጀት ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ ተካቷል፡፡

ድልድዩ ችግር ላይ የወደቀ ሲሆን፣ የድልድዩን ግንባታ ለማስጀመር ብዙ ጊዜ እንደወሰደ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ከጥቂት ወራት በፊት የግንባታ ውል የተፈረመ በመሆኑ በዚህ በጀት ዓመት ሥራውን ይጀምራል፡፡ በተለይ ዲዛይን የተሠራው ይህንን ድልድይ ለመገንባት ከ1.43 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ሲሆን፣ ግንባታውም ሲሲሲ የተባለው የቻይና ኩባንያ የሚገነባው ነው፡፡ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ይሠራሉ የተባሉት 91 ፕሮጀክቶች ከ150 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የፕሮጀክቶቹ ሥራ መጀመር ከ150 ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሏል፡፡ ሆኖም ይህንን ጥቅል ኢንቨስትመንት ለመከወን ባለሥልጣኑ እያጋጠሙት ያሉት ውጫዊ ችግሮች ሊቀረፉለት መቻል እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አፅዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በሦስት ዓመት የተፈቀደ ግንባታ ስድስትና ስምንት ዓመታት እየፈጀ ኢኮኖሚው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት አይቻልም ያሉት አቶ ሀብታሙ፣ ስለዚህ ወሰን ማስከበር ሥራ ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊሠሩ ይገባል፡፡ እንደ ዘርፉ እንደ አገር ብዙ ለውጥ የሚፈልጉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ እኛ ጋር የሚወጣው ተቋራጭ የመጨረሻውን የመንግሥትን ክራይቴሪያ የሚያመሏ ተቋራጭ ነው፡፡ ስለዚህ ፈቃድ አሰጣጡ ላይ ለውጥ እንዲደረግ የሚሻ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ኮንስትራክሽን ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ አቅም ያለው መሆኑንም በማስታወስ ሥራው እንዳይስተጓጎል ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍልና ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሠሩ ይገባል ተብሏል፡፡ በዚህ ዓመት በ2012 ዓ.ም. 38.2 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ ይህ ካለፈው ዓመት 37 በመቶ ጭማሪ ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህ በጀት በባለሥልጣኑ ታሪክ ከፍተኛ የሚባለው እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት መግለጫ ባለሥልጣኑ የመዋቅር ማስተካከያ ማድረጉን የተመለከተው ዓብይ ጉዳይ ይገኝበታል፡፡ መዋቅሩ በአገሪቱ የመንገድ ዘርፍ ላይ ያለው ከፍተኛ የሥራ ጫና የሕዝቡ ፍላጎት ተቋሙን የተሻለ ለማድረግ የሥራ ጫናውን ለማመጣጠንና ቀጣይ ፍላጎቱን ለማየት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መዋቅር ላይ ለውጥ ተደርጓል፡፡ ይህም ችግሮች የነበሩባቸው ተብለው የሚታሰቡ ዘርፎችን በተሻለ አገልግሎት ሊሰጥ በሚችል ደረጃ የመዋቅራዊ ማስተካከያ ተሠርቷል፡፡ 

ባለሥልጣኑ በጣም ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እንደሌሉት የጠቀሱት ኢንጂነሩ፣ ተወዳዳሪ ከፋዮች ስላልሆን ሠራተኞች ይለቃሉ ብለዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ግን ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ወጣቶች እየሠለጠኑ ነው፡፡ እነዚህን ወጣቶች ማብቃት ከተቻለ ክፍተቱን ማጥበብ ይችላል ተብሎ ታስቧል፡፡

ባለሥልጣኑ አሉብኝ ያላቸውን ተጨማሪ ተግዳሮቶች ሲገለጹም የረዥም ጊዜ ፍኖተ ካርታ ላይ አንዳንድ ችግሮች ነበሩ፡፡ ‹‹አለን ግን መፅደቅ አለበት፡፡ ተቋሙ አሁን የራሱ የሆኑ ችግሮች አሉበት፡፡ የውጫዊ ሁኔታው ብዙ ጫና እየፈጠረ ነው፡፡ ከፍተኛ የሥራ ጫና ያለበት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ ላይ የተሻለ ለመፈጸም ከፍተኛ ችግር እያጋጠመ ስለመሆኑ በማስረዳትም፣ ፕሮጀክት አፈጻጸም መዳከምና የወሰን ማስከበር ጋር ያለው ጉዳይ ፈተና እየሆነ ስለመምጣቱ ዋና ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ፡፡

ለግንባታ የሚሆን ግብዓት ማግኘትና ግብዓቶችን ከቦታ ቦታ ማጓጓዝ ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡ በተወሰነ መንገድ የአማካሪዎችና የኮንትራክተሮች የሥነ ምግባር ችግር፣ የብቃትና የልምድ ችግር ስለመታየቱ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ የበጀት እጥረትም መኖሩን ተናግረዋል፡፡ በተለይ በወሰን ማስከበር ዙሪያ ያለው ችግር ጊዜ ከመውሰድ አልፎ ከፍተኛ ወጪ እየጠየቀ መሆኑን አሳሳቢ እንዳደረገው ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ ይህንንም በምሳሌ ለመጥቀስ በ2011 ዓ.ም. ባለሥልጣኑ ከተመደበለት 28 ቢሊዮን ብር ውስጥ አራት ቢሊዮን ብር ለካሳ የተከፈለ ነው፡፡ የካሳ ክፍያ እያደረገ ነው፡፡ አሁን ላይ የተጋነነ ካሳ ክፍያ ይቀርባል፡፡ ይህ አካሄድ አደጋ ያለው መሆኑ ተገልጿል፡፡ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየናሩ መምጣታቸው ደግሞ ወደፊት የግንባታ ዋጋ የበለጠ እየጨመረ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አንዳንዶች የሚፈጽሙት ተግባርም ፈተናም ነው፡፡ የግንባታ ሥራዎች በአግባቡ እንዳይካሄዱ የሚያደርጉ ወገኖች አሉ፡፡ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ችግር ቢኖር መንገድ ተንከባክቦ እንዲያልቅ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡

አንዳንድ ቦታ አንድ ሰው የግንባታ ሥራ ሲያስተጓጉል ሁሉ እናያለን ያሉት ዳይሬክተሩ፣ እንዲህ ያለው ሁኔታ መንገዱን በተፈለገው ጊዜ ገንብቶ ለማጠናቀቅ እንቅፋት ስለመሆኑ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ የመንገድ ግንባታዎች ብዙ ችግሮች ያሉባቸው ሲሆን፣ እንዲህ ያለው ሰው ሠራሽ ተግባር ጠቃሚ ያለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ፈታኝ የሆኑ ችግሮች ቢኖሩም፣ መንግሥት አሁንም ለዚህ ዘርፍ ከፍተኛ በጀት በጅቶ ተጨማሪ መንገዶችን ለመገንባት ዝግጅት ላይ ነው፡፡

ለአስረጅነትም ባለፉት 21 ዓመታት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለንግድ ሥራ ውሏል ብለዋል፡፡ የግንባታ ሥራዎች እንዴት እንደነበሩ ለማስታወስም እስከ 2018 ድረስ 48 በመቶ የሚሆነው አጠቃላይ ኢንቨስት የተደረገው ገንዘብ በአገር ውስጥ ተቋራጮች የተሠራ ነው፡፡ ይህም የአገር ውስጥ ተቋራጮች ተሳትፎ ወደ 50 በመሆኑ ነው፡፡ ይህ በብዙ የአፍሪካ አገሮች ያልተለመደ ነው፡፡ የራሱ የሆኑ ብዙ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም፣ እንዲሁም ገና ተለማማጅ ነው፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያሳያል፡፡

በአማካሪዎች ረገድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው በአገር ውስጥ አማካሪዎች የተሠራ ነው፡፡ ባለፉት 21 ዓመታት ከተሠሩት ዲዛይኖች 62 በመቶ በአገር ውስጥ አማካሪዎች ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተሠሩ መንገዶች የፋይናንስ ምንጭ መንግሥት ነው፡፡ 83 በመቶ የሚሆነው መንግሥት ፋይናንስ የተደረገ ነው፡፡ 17 በመቶው ብቻ ነው በብድርና በዕርዳታ ፋይናንስ የተደረገው፡፡ መንግሥት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያደረገበት ስለመሆኑ ያመለክታል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች