Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለመልካሙ ጥርጊያ ጥሩ ማሳረጊያ ይበጅለት

የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን የሚመለከቱ ሕግጋት እየተፍታቱና እየተሻሻሉ ይገኛሉ፡፡ አላፈናፍንና አላሠራ በማለታቸው ይተቹ የነበሩ አንቀጾች ተለውጠዋል፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ሕጎች አዳዲስ አገልግሎቶችን ለማስጀመር ጭምር የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ተደርጎባቸዋል፡፡

በፋይናንስ ዘርፉ እንዳይሳተፉ ክልከላዎች የተደረጉባቸው ዜጎች ዳግም ተሳታፊ የሚሆኑበትን ዕድል የሚሰጥ ድንጋጌም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ተሰጥቶበት ሥራ ላይ እንዲውል ይሁንታ አግኝቷል፡፡ ሰሞኑን ውሳኔ አግኝተው ወደ ተግባር እንደሚሸጋገሩ ከሚጠበቁት ውስጥ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሳተፉ የሚፈቅደው የባንክ ንግድ ሥራ ሕግ ማሻሻያ አንዱ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ ለአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት በመስኮት ብቻ መገደቡ ቀርቶ ራሱን የቻለ ባንክ ማቋቋም እንደሚቻል ውሳኔ ማግኘቱም በፋይናንስ ዘርፉ የታየ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ በኢንዱስትሪው ውስጥ አዳዲስ አሠራሮችን ከመፍጠር አኳያና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከማስገኘትም አንፃር በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በቀላሉ አይታይም፡፡

ከሰሞኑም ግልጽነትና ተጠያቂነትን ከማስፈን አንፃር የግል ባንኮች ላይ የተደነገገውና ዓመታዊ አፈጻጸማቸውን ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ግዴታ፣ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማትም ይህንኑ እንዲተገብሩ በሕግ መደንገጉ በፋይናንስ መስኩ ከተደረጉ ዓይነተኛ ለውጦች ውስጥ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡

ይህ ውሳኔ የግልና የመንግሥት ተቋማት በእኩል መወዳደሪያ ሜዳ መሠለፍ የሚችሉበትን አሠራር ከማስፈን ባለፈ፣ በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቋማትን የመንግሥትና የግል ስለሆኑ ብቻ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ገድቦ የሚያይ ሕግ ሲተገበርበት የነበረውን አካሄድ የመቀየሩ መልካም ጅምር ለዘርፉ ተዋንያን በተለይም ለግል ባንኮች ትልቅ እፎይታን የሚያመጣ ነው፡፡ ሆኖም ገና መሻሻል የሚገባቸው ሕግጋት እንዳሉ መታወስ አለበት፡፡ በዚሁ መነሻነት የፋይናንስ ተቋማት ላይ ብቻ ተለይተው የወጡ ሕግጋትን ሁሉንም እንዲመለከት በማድረግ በነካ እጅ አንዱን ከሌላው የሚለዩ አሠራሮችና ሕግጋቶች ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባ መጠቆሙ ግን ግድ ነው፡፡ ምክንያቱም የውድድር ሜዳው ጤነኛ እንዲሆን ከተፈለገ የመወዳደሪያ ሜዳውን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ዙሪያ እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎች ይበል የሚያሰኙ ሲሆን፣ ሌሎችም ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ማሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ማሻሻያ የተደረገባቸውን ሕግጋትንም በአግባቡ ተፈጻሚ ማድረግና ፍትሐዊ ቁጥጥሩን ማስፈን ሊሳት የማይገባው ጉዳይ ነው፡፡ በቅርቡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እያደረጉ ያሉ ባንኮችን ጉዳይ ነጥለን ብንመለከት እንኳ፣ የጠቀሜታቸውን ያህል ጉዳት እንዳያመጡ መከላከል የሚቻልበትን አሠራር ለመፍጠር ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ ከወዲሁ መዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡

የመቆጣጠሪያ ሥልቱን በተገባ መንገድ ማስኬድ የሚችልበት አቅምና ዕውቀቱ እንዳለውም እርግጠኛ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በዘርፉ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን ማሰባሰብ ይገባል፡፡ መደበኛ ባንኮችን እንደሚቆጣጠር ሁሉ ከወለድ ነፃ ባንኮችም ግልጽ የሆነ ድንጋጌዎችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልገው በመረዳት የተባሉት ባንኮች ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ዝግጅቱን በግልጽ በማሳወቅ የፋይናንስ እንቅስቃሴው በሕጋዊ መንገድ እንዲራመድ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ሊመጡ ከሚችሉ ያልታዩና ያልተጠበቁ ችግሮችም መከላከል የሚቻልባቸውን አካሄዶች መንደፍ ያስፈልጋል፡፡

በአንፃሩ በሕጋዊ መንገድ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውንና ወደ ባንክ የሚመጣውን ገንዘብ እንዲበራከት ለማድረግ፣ እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ለማበራከት ወለድ አልባ ባንክ መጀመሩ ጠቃሚ ነው ከተባለ፣ እነዚህ አዳዲስ ባንኮች ጠንካራና ተዓማኒነት ያለው ሥርዓት መገንባት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በእምነታቸው ምክንያት የባንክ ተጠቃሚ መሆን ያልቻሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደ መደበኛው የገንዘብ ሥርዓት በማስገባት ረገድ ወለድ አልባ ባንክ የሚጫወተውን አወንታዊ አስተዋጽኦ መገመት አይከብድም፡፡ ሆኖም ለዘመናት ሳይፈቀድ የቆየውን የነበረውን ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ለማጀመር የሚያስችል የመንግሥት ይሁንታ ከተሰማበት ጊዜ ወዲህ ባንክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ የጀመሩ ስምንት ቡድኖች እንዳሉ ታውቋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም አራቱ የአክሲዮን ሽያጭ ጀምረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለውን ባንክ ለማቋቋም የተሰናዳ አንድ ብቻ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን አሁን በአጭር ጊዜ ሌሎችም ለተመሳሳይ ሥራ ለመሰማራት ጥድፊያ ያለበት ሩጫ ግን በአንክሮ መታየት አለበት፡፡ አንድ ወይም ሁለት ጠንካራ ባንክ ቢፈጥሩ ይመረጣል የሚለው አመለካከት ሰሚ ሊያገኝ ይገባል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያሉት መደበኛ ባንኮች ተዋህደው ጠንካራ ይሁኑ እየተባለ በወለድ አልባ ውጭ ስለዚህ እነዚህ ባንኮች ምሥረታ ላይ ናቸውና ጉዳዩን ማጤን ይርባቸዋል፡፡ በተበጣጠሰ ካፒታል ትልቅ ሥራ መሥራት እንደሚችል ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠልም ቢሆን ፈተና ሊሆን እንደሚችል ተገንዝበው፣ ሰብሰብ ብለው ጠንከር ያለ ካፒታል ኖሯቸው ቢሠሩ ይመረጣል፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉም ተበታትነው ሥራ ከመጀመራቸው በፊት የሚፈጸም ሲሆን ከቀጥታ ሊያድን እንደሚችል መታሰብ አለበት፡፡

ይህ ማለት በቁጥርም በርከት ብለው ጠንካራ የሚያስብላቸው ካፒታል ከያዙ ምንም ችግር አይኖረውም፡፡ ሆኖም እስካሁን የነበሩ ልምዶች ይህንን የሚያሳዩ በመሆኑ የነገ ጉዟቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ከወዲሁ ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል፡፡ ጠንከር ያሉ ጥቂት ባንኮች የመኖሩ ጉዳይ ትልቅ ጠቀሜታ ይሰጣል፡፡ መጪውንም ውድድር ለመቋቋም ይቻላል፡፡

ሌላው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዚህ ዘርፍ ውስጥ እንዲገቡ ሲፈቀድ ግን አሁን ባሉት የፋይናንስ ጠቋማት ውስጥ ባለድርሻ ለሚያደርጋቸው አሠራር ላይ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡

የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑት በዚህ ረገድ ቢጓዙ መሆኑ መታሰብ ይኖርበታል፡፡ አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም ከተፈለገ የተሻለውን አማራጭ ሰከን ብሎ ማሰብ ጠቃሚ ነው፡፡ ምክንያም ዳያስፖራው ራሱን የቻለ ባንክ እንዲኖረው መመኘት መልካም ቢሆንም፣ የበለጠ ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው አሁን ባሉት ባንኮች ውስጥ የራሳቸውን ድርሻ መውሰድ ቢሆን ጠንካራ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንዲገነቡ በማድረግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ እነርሱም ኢንቨስት ባደረጉት ልክ ትርፋቸውን ሊያገኙ ይችላሉና አሁን የተገኙትን ዕድሎች በአግባቡ እንዲጠቀሙ የተሻለውን አማራጭ እንዲወስዱ ከወዲሁ በታሰቡት ይመረጣል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት