Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትተጠያቂነት ሳይኖረው የዘለቀው የተጨዋቾችና አሠልጣኞች ዝውውርና ንግዳዊው እንቅስቃሴ

ተጠያቂነት ሳይኖረው የዘለቀው የተጨዋቾችና አሠልጣኞች ዝውውርና ንግዳዊው እንቅስቃሴ

ቀን:

የ2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከወትሮው በተለየ በአጨቃጫቂ ሁኔታ፣ በተደጋጋሚ መቆራረጥ እንዲሁም በአሰልቺ የውድድር መርሐ ግብር ተጠናቋል፡፡ የዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ ስፖርታዊ ባላንጣነት ይልቅ ‹‹ብሔር ተኮር›› መጠቃቃቶችና ግጭቶችን አስተናግዶ አልፏል፡፡ በሊጉ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ምክንያት በተለይ የአዲስ አበባ ክለቦች የተለየ አቋም እንዲይዙ አድርጓል፡፡

አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ሳያከናውን የውድድር ዓመቱ መርሐ ግብር ተጠናቋል ቢባልም፣ የክለቡ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ እንዴት ሊሆን ነው? የሚለውና ሌሎች ከስፖርት መርህና ባህል ባፈነገጠ መልኩ ሲሰጡ የነበሩ ውሳኔዎች፣ ፌዴሬሽኑ ከፊት ለፊቱ የተደቀኑበት ጥያቄዎችን ሳይፈታና የሊጉን ቀጣይ አካሄድ እንዴት እንደሚሆን ሳይወስን የ2012 ዓ.ም. የዝውውር መስኮትን  መክፈቱ አነጋጋሪ አድርጎታል፡፡

ከአሠራር ጋር ተያይዞ በሊጉ ውስጥ የተፈጠሩ አለመግባባቶች በቅጡ ሳይቋጩና ቀጣይ አቅጣጫ ሳይቀመጥ የዝውውር መስኮት መከፈቱ በዘርፉ ያለውን ለስፖርቱ ሳይሆን፣ ለትርፍ ቅድሚያ በሰጡ ግለሰቦች እየተመራ ጠያቂም ሆነ ተጠያቂ ሳይኖረው ግምታዊ ሆኖ እንዲቀጥል ተፈልጓል የሚሉም አልታጡም፡፡

ለዚህም እንደ መከራከሪያ የሚቀርበው፣ ዝውውር የሚባለው “ሒደት” በምን እንደሚተዳደር ኃላፊነት ወስዶ የሚመራው እንዲሁም በተጨዋቾች፣ አሠልጣኞችና ወኪሎች መካከል ያለው የጥቅም ግንኙነት በውል (በግልጽ) ባልተለየበት ሁኔታ የዝውውር መስኮቱ መከፈት፣ ከንግድና ትርፍ ጋር እንጂ ከእግር ኳሱ ዕድገትም ሆነ አስተዋጽኦ ጋር የሚያገናኘው ነጥብ የለም በማለት የሚተቹ በርካቶች ሲሆኑ፣ ጉዳዩ የሚመራበትና የሚተዳደርበት አካሄድ ማበጀት ቀዳሚ ሊሆን እንደሚገባው ይመክራሉ፡፡

ክለቦች ለ2012 ዓ.ም. የውድድር ዓመት የሚያስፈልጋቸውን ተጨዋቾችና አሠልጣኞች ማዘዋወር ይችሉ ዘንድ የዝውውር መስኮት ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ መከፈቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ የመስኮቱ መከፈት ተከትሎ ክለቦች በቃል ደረጃ ያነጋገሯቸውን ተጨዋቾች በማስፈረም ላይ ይገኛሉ፡፡ አካሄዱ ላይ ጥያቄ ያላቸው የአዲስ አበባ ክለቦች አመራሮች ሆኑ ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ቀጣዩ የሊግ አካሄድ በምን መልኩ እንደሚከናወን ተነጋግሮ አንድ የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲቀመጥ ቀድሞ ከመሥራት ይልቅ የነበሩና የሚታወቁ ተጨዋቾች በተለመደው አግባብ ለማዘዋወር የሚደረገው ሩጫ ትርጉም እንደሌለው ጭምር ያስረዳሉ፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ዘንድሮ ሳይጠናቀቅ ተጠናቋል ተብሎ በሚነገርለት ፕሪሚየር ሊጉ፣ አንድ ቡድን ከሜዳው ውጪ ማሸነፍ ቀርቶ ነጥብ ተጋርቶ መመለስ  አዳጋች ያደረገው ንብረትም ሆነ የሰው ሕይወት እንደ ቀላል ነገር በአልባሌ ቦታ ጉዳት ሲደርስበት ቆይቷል፡፡ በዚህም አንዳንድ የክልል ክለቦች ከአዲስ አበባ ውጪ ከከተማቸው ወደ ሌላ የክልል ከተማ ሄደው መጫወት አደገኛነቱን በመግለጽ ፎርፌ በመስጠት ጉዞዋቸውን ሲሰርዙ ቆይተዋል፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ ፋሲል ከተማ በቀጣዩ የውድድር ዓመት ወደ መቐለ ተንቀሳቅሶ እንደማይጫወት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በይፋ ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ምክንያቱ ፋይናንስ ይሁን እንጂ ጅማ አባ ጅፋርና ሌሎችም ክለቦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በፕሪሚየር ሊግ የሚታዩት ችግሮች፣ በተዋረድ ባሉት ሊጎች ከዚያም በታች በሚገኙት ዲቪዚዮኖች እንደሚታዩ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የዝውውር መስኮቱን ይፋ ማድረጉ እንደተጠበቀ፣ ክለቦችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ከነበረው ችግር አኳያ፣ ሊጎቹ እንዴት ይቀጥሉ ለሚለው ቅድሚያ ሊሰጠው በተገባ ነበር በማለት በተጨዋቾች ዝውውር ላይ የተጠመዱ ክለቦች አካሄድን ይተቻሉ፡፡

የአዲስ አበባዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና አሁን ላይ ላለፉት ሁለት አሠርታት በዘለቀው የፕሪሚየር ሊጉ የውድድር ሥርዓት እንደማይቀጥሉ፣ ከዚህ ይልቅ ውድድሩ በየክልሉ ሆኖ እንዲቀጥል ፍላጎታቸው ስለመሆኑ ጭምር በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል የየቡድኖቻቸውን የቀጣይ ዓመት አሠልጣኞች ሳያሳወቁ፣ በተጨዋቾች ዝውውር ላይ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ክለቦች መኖራቸውና ይህም እግር ኳሱን ሽፋን በማድረግ ንግዳዊ እንቅስቃሴ መኖሩን አመላካች እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

ብዙዎቹ ክለቦች በወሬ ደረጃ ካልሆነ በአሁኑ ወቅት ዋና አሠልጣኝ የሌላቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያን በመወከል ለአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚጫወተው ፋሲል ከተማ አሠልጣኙ ‹‹በቤተሰብ ችግር›› ምክንያት ክለቡን መልቀቁ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ምናልባትም የአሠልጣኙ ቀጣይ ማረፊያ እንደሚሆን የሚጠበቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡ የፋሲል ከተማ ቀጣዩ አሠልጣኝ ማን እንደሚሆን እስካሁን አልታወቀም፡፡

ሌላው አርባ ምንጭ ከተማ ሲሆን፣ የክለቡ አሠልጣኝ የነበሩት አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም በአሁኑ ወቅት ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገውን ሰበታ ከተማን ለማሠልጠን መስማማታቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡ አሠልጣኙ ከፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ትራንስ ኢትዮጵያ፣ ሐረር ቢራ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም አሁን ላይ የለቀቁት አርባ ምንጭ ከተማ ክለቦች በማሠልጠን ይታወቃሉ፡፡ 

የባህር ዳር ከተማ ክለብም በተመሳሳይ አሠልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን (ማንጎ) አሰናብቶ በምትካቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሠልጣኝ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ለመቅጠር በማነጋገር ላይ መሆኑ ይነገራል፣ ሌሎችም በተመሳሳይ መንገድ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል በእነዚህና በሌሎች ችግሮች ተተብትቦ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሐምሌ 25 እና 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በውድድር ዓመቱ አከናውኛለሁ ያለውን ዕቅድ ገምግሟል፡፡ እንደ ሪፖርተር ምንጮች ከሆነ፣ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ጀምሮ ሁሉም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በተሰጣቸው የኃላፊነት ልክና የሥራ ድርሻ ምን እንዳከናወኑ የሚያሳይ ሪፖርት እንዲያቀርቡ በማድረግ መገማገማቸው ታውቋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በውድድር ዓመቱ ከውሳኔ አሰጣጥ ጀምሮ በከፍተኛ ልዩነት ውስጥ ሆነው ሥራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸው፣ ከነዚህም ልዩነቶቹ መካከል ኢትዮጵያ ቡና ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ሊያከናውኑት የነበረው ጨዋታ እንዲቋረጥ የተደረገበት አግባብ አንደኛው ሲሆን፣ የቅዱስ ጊዮርጊስና የወልዋሎ አዲግራት ጨዋታ ሒደት ሁለተኛው የልዩነቱ መንስዔ ነው፡፡

በዚህም ፕሬዚዳንቱና ምክትላቸው በአንድ በኩል፣ የተቀሩት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደግሞ በሌላ በኩል በመሆን ውሳኔዎች ሲተላለፉ መቆየታቸውን ተከትሎ፣ ይህ ግምገማ እንዲደረግ ምክንያት እንደሆነ የሚናገሩት ምንጮች፣ በሁለቱ ቀን ግምገማም፣ ከውሳኔ ጋር ተያይዞ ልዩነቶቹ ለምን ሊፈጠሩ እንደቻሉ፣ በፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል ኢብራሂም የሚመራው የሊግ ኮሚቴ፣ በአቶ ሰውነት ቢሻው የሚመራው የቴክኒክና ልማት ኮሚቴ፣ በአቶ ዮሴፍ ተስፋዬ የሚመራው የዳኞች ኮሚቴ፣ በአቶ አበበ ገላጋይ የሚመራው የማርኬቲንግ ኮሚቴ፣ እንዲሁም ሌሎችም እንደየ ኃላፊነታቸው በውድድር ዓመቱ ያከናወኑዋቸውን ሥራዎች በሪፖርት መልክ እንዲያቀርቡና ማብራሪያ እንዲሰጡ፣ ፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራም እንደዚሁ እንደ ተቋም መሪነታቸው በግምገማው ተካተው ሥራቸውን እንዲያቀርቡ መደረጉ ታውቋል፡፡

የግምገማው ዋና ዓላማም አመራሩ በቀጣይ በአንድ መንፈስ የብሔራዊ ተቋሙን የዕለት ዕለት ሥራዎች ለማከናወንና እንዳለፉት ጊዜያት ተመሳሳይ የአመራር ልዩነቶች እንዳይፈጠሩ ለማድረግ እንደሆነም ተነግሯል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...