Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአዲስ አበባና የድሬዳዋ ምክር ቤቶች ምርጫ ከ15 ዓመታት ቆይታ በኋላ ከአጠቃላይ ምርጫ...

የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ምክር ቤቶች ምርጫ ከ15 ዓመታት ቆይታ በኋላ ከአጠቃላይ ምርጫ ጋር እንዲካሄድ ተወሰነ

ቀን:

በድኅረ ምርጫ 97 ተከስቶ በነበረው ውዝግብ ምክንያት በተለየ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ሲከናወኑ፣ የነበሩት የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች ምክር ቤቶች ምርጫዎችና የአካባቢ ምርጫዎች፣ ከመጪው ዓመት ጀምሮ የኢትዮጵያ ምርጫ በቦርድ በሚያዘጋጀው ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ከ15 ዓመታት ቆይታ በኋላ እንዲከናወኑ ተወሰነ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው የአራተ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተ አስቸኳይ ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምክር ቤቱ በላከው ደብዳቤ መሠረት እንደተዘጋጀ የተነገረለትን የውሳኔ ሐሳብ አፈ ጉባዔው አቶ ታገሰ ጫፎ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

በስብሰባው ወቅት እንደተገለጸው በፌዴራል መንግሥት ሥር ሆነው በየራሳቸው ቻርተር የሚተዳደሩት የሁለቱ ከተሞች ምክር ቤቶችም ሆኑ የአካባቢ ምርጫዎችን በብቃት ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው፣ በቦርዱ በሚዘጋጀው ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲካሄድ መወሰኑ ተጠቁሟል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አቶ ታገሰ ለምክር ቤቱ፣ ‹‹የአገራችንን የዴሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ለማጠናከር የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የሕግ ማዕቀፍ፣ የአመራሮች አመራረጥ፣ ዘመናዊ አሠራር መዘርጋት፣ እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ አሠራርና መድረክ እንዲፈጠርላቸው ማድረግ በሪፎርሙ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት ካለው የጊዜ ማነስ አንፃር የምርጫ አስፈጻሚዎችን መመልመል፣ ማደራጀት፣ ሥልጠና መስጠትና ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎችን በክልል አጠናቆ ማስፈጸምና ምርጫውን በተቀመጠው ጊዜ ማካሄድ እንደማይቻል ቦርዱ ለምክር ቤቱ ያቀረበ መሆኑን በመግለጽ፣ የቦርዱን ውሳኔ ከግንዛቤ በማስገባት ምክር ቤቱ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ እንዲያፀድቀው ምክር ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

በመደበኛ መርሐ ገብሩ መሠረት የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደር የምክር ቤቶች አባላት ምርጫ  2010 ዓ.ም. መካሄድ ነበረበት፡፡

ሆኖም ምርጫ ቦርድ በወቅቱ ምርጫዎችን ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ የለም በማለቱ፣  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫው ወደ 2011 ዓ.ም. እንዲራዘም ወስኖ ነበር፡፡

ነገር ግን ዘንድሮም ምርጫውን ለማካሄድ የተያዘው ዕቅድ መተግበር አልተቻለም፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ሐምሌ 4 ቀን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ፣ የሁለቱን ከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤት ምርጫን በተቀመጠው ጊዜ ማለትም ዘንድሮም ማካሄድ አይቻልም ማለቱን በቀረበው የውሳኔ ሐሳቡ ተጠቅሷል።

ምክር ቤቱም አፈ ጉባዔው በጠየቁት መሠረት የውሳኔ ሐሳቡን ሁለት አባላት ከሰጡት ድጋፍ አስተያየት ውጪ ያለ ምንም ክርክርም ሆነ የማብራሪያ ጥያቄ፣ ያለ ምንም ተቃውሞም ሆነ ድምፀ ተዓቅቦ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

ነገር ግን የውሳኔ ሐሳቡ ከፀደቀ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ የምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ፣ ምርጫውን በተመለከተ የይራዘምልኝ ጥያቄ ሳይሆን የቀረበው ምርጫውን ለመካሄድ የማያስችሉ ጉዳዮችን ጠቅሶ ምክር ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ብቻ መጠየቁን ጠቁሟል፡፡

በመሆኑም መንግሥት የሰጠውን መግለጫ እንዲያስተካክል ወይም ማረሚያ እንዲያወጣ ጠይቋል፡፡

“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካለበት ከፍተኛ የሥራ ጫና፣ ከአቅም ውስነንነትና ከሪፎርም ሥራ መደራረብ የተነሳ በዚህመት መደረግ የነበረበትን የአካባቢ ምርጫና የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ ምክር ቤቶች ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጽሑፍ የገለጸ ቢሆንም፣ ምርጫዎቹ ከሚቀጥለው አገራዊ ምርጫዎች ጋር እንዲካሄዱ ምክረ ሐሳብ ያቀረበውም ሆነ ውሳኔ ያሳለፈው የተወካዮች ምክር ቤት ነው፤” ሲል በቦርድ ሰብሳቢዋ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ተፈርሞ የወጣው የቦርዱ መግለጫ ጠቅሷል፡፡

“በመሆኑም ቦርዱ የአካባቢ ምርጫም ሆነ የሁለቱ ከተማ ምክር ቤቶች ምርጫ ከአጠቃላይ ምርጫ ጋር መካሄድ አለባቸው የሚል የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል የሚለው የሚዲያዎች ሪፖርት ማስተካከያ እንዲደረግበት እንጠይቃለን፤” ሲል ቦርዱ አክሏል፡፡

ነገር ግን ሪፖርተር ወደ ማተሚያ ቤት እስከገባበት እስከ ዓርብ ምሽት ድረስ የቦርዱን ጥያቄ በተመለከተ ከመንግሥት ወይም ከምክር ቤቱ የተሰጠ ምላሽ አልተሰማም፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ መጪው አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ በጊዜው ሰሌዳ መሠረት ስለመካሄዱ እያነጋገረ ነው፡፡ ከዚሁ ጥያቄ ጋር በተገናኘ ኢሕአዴግ የሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ በጊዜው እንዲካሄድ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የድርጅቱ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትርብይ አህመድ (ዶ/ር) ሐሙስ ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄ በሰጡጥ ምላሽ፣ በ2012 .ም. የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ የኢሕአዴግ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰነድ በማዘጋጀት ምርጫው በወቅቱ መደረግና አለመደረጉ ያለውን ጥቅምና ጉዳት በዝርዝር እንደተወያየበት ገልጸዋል።

ከውይይቱም ባለፈ በተግባርም ከዚህ በፊት ከነበሩ ምርጫዎች የተሻለ ምርጫ ለማድረግ በጀት፣ የሕግ ማዕቀፍና የተቋም አደረጃጀት ማሻሻያ መፍጠር እንደተቻለም አመልክተዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...