Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወለድ አልባው ዘምዘም ባንክ በመጪው መስከረም ሥራ ይጀምራል ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ወለድ አልባ ባንክ እንዲመሠረት ለማድረግ ቀዳሚ ሚና የነበረው ዘምዘም ባንክ አክሲዮን ማኅበር (በምሥረታ ላይ) በ2012 ዓ.ም. የመጀመርያው እንደሚሆን የሚታሰውበውንና ሙሉ በሙሉ ወለድ አልባ የሚሆውን ባንክ በአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ለመመሥረት የሚያስችለውን ዝግጅት እንዳጠናቀቀ አስታወቀ፡፡

ዘምዘም ባንክ ቅዳሜ፣ ሐምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው፣ ወለድ አልባውን ባንክ ለማስጀመር የሚያስፈልገውን ካፒታል በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኝና እስካሁንም ከሚፈልገው ካፒታል ከ70 በመቶ በላይ ማሟላቱን አስታውቋል፡፡

በባንኩ ምሥረታና በእስላማዊ የባንክ አገልግሎት ጠቀሜታና አዋጭነት ዙሪያ የባንኩ አደራጆች ከኅብተረሰቡ ክፍሎች ጋር ባካሄዱት ውይይት ወቅት እንዳሉት፣ ባንኩን ሥራ ለማስጀመር አስፈላጊውን ካፒታል በማሟላትና አገልግሎቱን በመጀመር ፋና ወጊ የሚሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የዘምዘም ባንክ አደራጅ ቦርድ ሊቀመንበር  ናስር ዲኖ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት ባንኩን ለማቋቋም በሕግ ከተቀመጠው የ500 ሚሊዮን ብር ዝቅተኛው የተከፈለ ካፒታል መጠን በላይ ማሰባሰብ በመቻሉ፣ በአዲሱ ዓመት መስከረም ወር ሥራ እንዲጀምር ለማድረግ ታቅዷል፡፡

በባንክ መስክ ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ ባንክ ለማቋቋም መንቀሳቀስ ከጀመረ የሰነበተው ዘምዘም ባንክ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከሰባት ዓመታት በፊት ወለድ አልባ አገልግሎት ባሉት ባንኮች አማካይነት አገልግሎት በመስኮት እንዲጀመር ቢፈቀድም፣ ራሱን የቻለ ወለድ አልባ ባንክ ማቋቋም ባለመፈቀዱ ዘምዘም ባንክ የሰበሰበውን የአክሲዮን ገንዘብ ላዋጡት ባለአክሲዮኖች ለመመለስ መገደዱ አይዘነጋም፡፡ ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እስላሚክ ባንክ እንዲቋቋም መንግሥታቸው ፈቃደኛ መሆኑን ካሳወቁ በኋላ፣ ወለድ አልባ ባንክ ለመመሥረት እንቅስቃሴዎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡

ዘምዘም ባንክ በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ለመሠማራት ሲያደርግ የቆየውን እንቅስቃሴ ዳግም ለማስጀመር በመጪው መስከረም ወር በክልሎች ዋና ዋና ከተሞች ቅርንጫፍ ለመክፈት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 60 ለማድረስ ማቀዱንም ናስር (ዶ/ር) ይፋ አድርገዋል፡፡

ዘምዘም ባንክ ከሰባት ዓመታት በፊት ባንኩን ለማቋቋም የሚያስፈልገው የተከፈለ ካፒታል መጠን 100 ሚሊዮን ብር ስለነበር በዚሁ መሠረት ከ137 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖችን በመሸጥ ባንኩን ለመሠረት የሚያስችለውን ካፒታል አሰባስቦ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተመለከተው ሕግ ባሉት ባንኮች ብቻ በመስኮት እንዲሰጥ የሚፈቅዱ መሆኑ ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ ባንክ ለመቋቋም ሳይችል መቅረቱ አይዘነጋም፡፡

በአሁኑ ወቅት ዘምዘምን ጨምሮ አራት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጁ ባንኮች ወደ አክሲዮን ሽያጭ ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ ዛድና ሒጅራ ባንኮች እስከ ቀጣዩ ዓመት አጋማሽ ድርስ ወደ ሥራ እንገባለን በማለት መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች