የተመሠረበትን አሥረኛ ዓመት እያከበረ የሚገኘው ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄኔራል ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር፣ በኢንዱስትሪው አዲስ አደረጃጀትና የአገልግሎት መስክ በማስተዋወቅ የመድን ገበያውን የተቀላቀለበትን ወቅት በመዘከር ላይ ይገኛል፡፡ ከሌሎች የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በልዩነት እንዲታይ ያደረገውም የሕይወት መድን ሽፋን ብቻ በመስጠት ሥራ መጀመሩ ነው፡፡
በሕይወት መድን ሽፋን ከዓለም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከሚመደቡ ጥቂት አገሮች አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ፣ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ብቻውን ለአገልግሎት በማቅረብ የጀመረው ጉዞ አዋጭ እንደሚያደርገው በማመን ነበር፡፡ በሌሎች አገሮች አካሄድም የሕይወት ኢንሹራንስ ያለው አበርክቶ የላቀ ስለነበር፣ ኢትዮ ላይፍ ኩባንያም በሕይወት ኢንሹራንስ መስክ ለመሥራት በማሰብ ነበር፡፡
በተግባር ግን ለሕይወት ኢንሹራንስ አገልግሎት የነበረው ዝቅተኛ አመለካከትና አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ የነበረው ግንዛቤ ኢትዮ ላይፍ በፈለገው ልክ እንዳይጓዝ አደረገው፡፡ ይሁንና በቶሎ ትርፍ በማይገኝበት በሕይወት መድን ሽፋን መስክ አዳዲስ አገልግሎቶችን በመጀመር የሕይወት ኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲስፋፋና የሽፋን ደረጃውም እንዲሻሻል ኩባንያው አስተዋጽኦ ማበርከቱ አልቀረም፡፡ በዘርፉ ከፍተኛ ዓረቦን ካሰባሰቡ መድን ሰጪዎችም አንዱ ለመሆን ችሏል፡፡
በኢትዮጵያ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን በቶሎ አለመመደቡና ዝቅተኛ መሆኑ ኩባንያውን እንደፈለገ ሊያራምደው ስላላስቻለው አሠራሩን እንዲፈትሽ አስገድዶታል፡፡ የኩባንያው አመራሮች ውጥናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ እንደ ሌሎች የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጠቅላላ የኢንሹራንስ ሽፋን አገልግሎት ወደሚሰጥ ተቋም እንዲለወጥ ለማድረግ ተገደዋል፡፡ የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ እንደሻው የሚገልጹትም፣ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ኩባንያው ካሳለፋቸው ተግዳሮቶች አንዱ በሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ላይ ብቻ ተመርኩዞ መጓዝ ከባድ ሆኖበት እንደነበር ነው፡፡
በኩባንያው ምሥረታ ወቅት በተለይም በሕግ የተወሰነውን አነስተኛ የካፒታል መጠን፣ ሥራውን በተደራጀ አግባብ በማስኬድ የሚችልበት በቂ ፋይናንስ ማሟላት የኩባንያው ፈተና ሆኖ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡ በሌላ በኩል ኩባንያው ሲመረሠት የሕይወት ነክ ወይም የረዥም ጊዜ የመድን ዘርፍ ሥራ ላይ ብቻ ለመሳተፍ አቅዶ ቢሆንም፣ በሒደት ለዚህ ውሳኔ ታሳቢ የነበሩትን እንደገና በመመርመርና በአጠቃላይ የመድን ሥራ ላይ በመሰማራት ከነሐሴ 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡
ኢትዮ ላይፍ ኢንሹራንስ ኩባንያ ጠቅላላ የኢንሹራንስ ሽፋን ወደሚሰጥ ኩባንያ ራሱን ሲያሳድግ፣ ስያሜውንም ‹‹ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄኔራል ኢንሹራንስ አ.ማ.›› በማድረግና ካፒታሉን በማሳደግ ሥራ መጀመሩ ኩባንያው የተሻለ ጉዞ እንዲኖረው አስችሎታል፡፡
የኩባንያውን የአሥር ዓመታት ጉዞ በተመለከተም መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት፣ በአራት ሚሊዮን ብር ካፒታል መነሳቱን ነው፡፡ በጉዞው የመጀመርያዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ ትርፍ ማስመዝገብ ተስኖት እንደነበርም የኩባንያው የኃላ ታሪክ ያሳያል፡፡
ኩባንያውን ከመነሻው እስካሁን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩት አቶ ሽመልስ ገድለ ጊዮርጊስ እንደሚገልጹት፣ አራት ሚሊዮን ብር ካፒታል ይዞ የተቋቋመውን ኩባንያቸውን እንዲመሩ ኃላፊነት ሲረከቡ የሰው ኃይሉም እሳቸውን ጨምሮ አራት ባለሙያዎች ብቻ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ ከ100 ካሬ ሜትር የማይበልጥ ስፋት በነበረው ቢሮ፣ በሁለት ጠረጴዛዎችና ጥቂት ወንበሮች ሥራ እንደጀመረ ያስታወሱት አቶ ሽመልስ፣ ኩባንያው ይህ ነው የሚለው ቋሚ ንብረትም አልነበረውም፡፡ በጅምሩ ጊዜ የሥራ ፈቃድ ቶሎ ካለማግኘቱ ጋር በተያያዘ በዝግ ሒሳብ የተጠራቀመ ካፒታሉን ማንቀሳቀስ ባለመቻሉም ኩባንያው ከጅምሩ ፈተና እንደገጠመው ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ መሆኑ ለአስተዳደርና ጠቅላላ ወጪዎች የሚውል የገንዘብ እጥረት እንዲከሰት ከማድረጉም በላይ ደንበኞችን ለመሳብም ፈታኝ ሆኖበት ነበር፡፡
‹‹ኩባንያው ባለው የካፒታል አቅም፣ የሰው ኃይል ብቃት፣ በደንበኞች አገልግሎት ጥራት ራሱን አስተዋውቆ ቀልብ ለመሳብ በቂ ጊዜ የሚጠይቅ ነበር፤›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ኩባንያው በሕይወትና ጤና መድን ላይ ብቻ አተኩሮ ወደ ሥራ መግባቱም ውጤታማ እንደማያደርገው ከሽያጭ ወኪሎችና ከመድን አዋዋዮች ጭምር የሚነሳ የገበያ ጥርጣሬ ስለነበር፣ ከጅምሩ ተቀባይነቱ አመርቂ አልነበረም ብለዋል፡፡ በገበያው የነበረው የዋጋ ውድድርም ኩባንያው ኢንዱስትሪውን በተቀላቀለበት ወቅት ይበልጥ እንደከረረ የሚያስታውሱት አቶ ሽመልስ፣ በወቅቱ በአገሪቱ የነበረው የዋጋ ግሽበት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረትና መሰል ችግሮች በተለይ ለጀማሪ የኢንሹራንስ ኩባንያ ተስማሚ ስላልነበሩ የመጀመርያዎቹን ሦስት ዓመታት በፈተና ለማሳለፍ እንዳስገደዱት ይናገራሉ፡፡ በተለይም የኩባንያው መነሻ ካፒታል ዝቅተኛው ወለል ላይ ስለነበር፣ ቢዝነሱም በታቀደው መሠረት ሊሳለጥ ባለመቻሉ በገቢና ወጪ ሒሳቦች መካከል የነበረው አለመጣጣም የጎላ ነበር ብለዋል፡፡ ይህም ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ትርፍ እንዳይመዘገብ አንዱ ምክንያት በመሆኑ፣ ኩባንያው አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ወቅት ነበር፡፡ ይሁንና የባለአክሲዮኖች ትዕግሥትና የተሻለ ሥራ ለመሥራት የተደረገው ርብርብ ውጤቱን እንደቀየረው ገልጸዋል፡፡
የሠራተኞች ሞራልና በወቅቱ የነበረው የዳይሬክተሮች ቦርድ ወደ ሥራ ለመግባት የነበረው ተነሳሽነትና ቆራጥነት ኩባንያው የተጋረጠበትን ፈተና እያለፈ አሥረኛ ዓመቱ ላይ እንዲደርስ አስችሎታል ተብሏል፡፡ በርካታ ጉዳዮች በእነዚህ ዓመታት ውስጥ መቀየራቸውን የሚያወሱት ሥራ አስፈጻሚው፣ በሦስት ባለሙያዎች የተጀመረው ጉዞ፣ በአሁኑ ወቅት 186 ሠራተኞችን የሚያስተዳደርበት ደረጃ ላይ እንዳደረሰው አንዱ የጥንካሬው መገለጫው ነው፡፡ ጠቅላላ የመድን ዘርፍ ሥራ ከተስፋፋበት ጊዜ ጀምሮ የቅርንጫፍ ቢሮዎቹን ወደ 22 ማድረሱም ሌላው ስኬቱ ነው ይላሉ፡፡
የኩባንያው ካፒታልም ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረው አራት ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ወደ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ከፍ ማለቱም ሌላው እንደ ስኬት የሚታይ ነው፡፡ ‹‹የኩባንያው ኢንቨስትመንት ተሳትፎና ሀብትም ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በዚሁ መሠረት ኩባንያችን በተለያዩ አክሲዮኖች ውስጥና በንብረት ላይ ከ104 ሚሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ አለው፤›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ለዋና መሥሪያ ቤት የሚሆን ሕንፃም በመግዛት የሕንፃ ባለቤት መሆን ችሏል ብለዋል፡፡ የተጣራ የሀብት መጠንም 146 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ እ.ኤ.አ. በተጠናቀቀው ጁን 30 ቀን 2019 የኩባንያው ጠቅላላ ዓመታዊ የዓረቦን መጠን ከ162.0 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ የአቶ ሽመልስ ገለጻ ያስረዳል፡፡ በርካታ ተቋማዊና ግለሰብ ደንበኞች ማፍራትና ውጤታማ የሆነ ሥራ በመሠራቱ ኩባንያቸው ባለፉት ተከታታይ ዓመታት አበረታች ሊባል የሚችል ትርፍ እንዳስመዘገበ የሚገልጹ የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች፣ ቀጣዩ ጉዟቸውም ጥሩ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያስችል ነው ይላሉ፡፡