አትሌቲክስ ከውጤት ጀምሮ በአደረጃጀት የተሻለ ቦታ ካላቸው ተቋማት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ የአበበ ቢቂላ ፈለግ በመከተል በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዛሬም በዓለም የውድድር መድረክ አንቱታን ያተረፈበት ብቸኛ መገለጫ ሆኖ ይገኛል፡፡ በአመራር ደረጃም ቢሆን አሁን ላይ ከራሱ አብራክ የተገኙ አትሌቶች የአንበሳውን ድርሻ ይዘው መገኘታቸው በሌሎች የስፖርት ተቋማት ጥያቄ እንዲነሳ ማድረጉ አልቀረም፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከፊት ለፊቱ ጠንካራ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተሳትፎዎች ይጠብቁታል፡፡ ከእነዚህ ተሳትፎዎች መካከል ዘንድሮ ለ12ኛ ጊዜ በሞሮኮ ራባት የሚከናወነው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎችና ከመስከረም 16 እስከ መስከረም 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በኳታር የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ለእዚህ ተሳትፎ የሚመጥኑ አትሌቶች ምርጫን በተመለከተም ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን በማስቀመጥ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ለወትሮ ይደመጥ የነበረውን ውዝግብ ማስቀረት መቻሉ እየተነገረ ይገኛል፡፡
በኦሊምፒክ የረዥም ርቀት ንግሥቷ ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ በአብሮነት የሚታወቀውን የቀድሞ አትሌቶች ኅብረት ወደ ነበረበት መመለስ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት እንዲለመድ በመሥራት ላይ መሆኑም ይነገርለታል፡፡ በመስከረም ወር አጋማሽ በኳታር ዶሃ ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚያዘጋጃቸው ብሔራዊ አትሌቶች 10,000 ሜትር በሁለቱም ጾታ፣ 3000 መሰናክል በሁለቱም ጾታ፣ በ1,500 ሜትር በሁለቱም ጾታ እና በ800 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ምርጫ አድርጎ ዝርዝራቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
የዕርምጃ ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ በማራቶንና በ5,000 ሜትር ገና በማጣራት ላይ መሆኑንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ከነሐሴ 13 እስከ 25 ቀን 2019 በሞሮኮ ራባት ለሚካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በአጠቃላይ 45 ሴቶችና 47 ወንዶችን መርጦ ዝግጅቱን እንደቀጠለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተሳትፎ የሜዳ ተግባራትን ጨምሮ አጭር ርቀት፣ መካከለኛና ረዥም ርቀት ሲሆን ሻምፒዮናው በአጠቃላይ 22 የውድድር ዓይነቶችን እንደሚሸፍን ይታወቃል፡፡