Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሸሪዓ ሕግ አግባብ የሚመሠረተው ‹‹ዛድ ባንክ›› በአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ሥራ ይጀምራል ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ አዲስ የባንክ አገልግሎት ለማስጀመር አራት ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች (በምሥረታ ላይ ያሉ) አክሲዮኖችን መሸጥ ስለመጀመራቸው አስታውቀዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ማግኘታቸውን ካሳወቁና በምሥረታ ላይ ከሚገኙ አራት ወለድ አልባ ባንኮች መካከል አንዱ ዛድ የተሰኘው ባንክ ነው፡፡ ዛድ ባንክ ወለድ አልባ የባንክ ሥራ ለመጀመር የሚያስፈልገውን ካፒታል ለማሰባሰብና የአክሲዮን ሽያጭ ለማካሄድ ሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ እንዳገኘ የባንኩ አደራጆች ገልጸዋል፡፡

የዛድ ባንክ አደራጆች ሐሙስ ሐምሌ፣ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ሥራ ለማስጀመር የሚቻልበትን ካፒታል በጥቂት ወራት ውስጥ በሚከናወነው አክሲዮን ሽያጭ አሰባስበው በጥር 2012 ዓ.ም. ወደ ሥራ ለመግባት ማቀዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

የዛድ ባንክ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅና የአደራጅ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሙኒር ሁሴን እንደገለጹት፣ በመጀመርያው ዓመት አንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል በማሰባሰብ ወደ ሥራ እንገባለን፡፡ የባንኩ የሦስት ዓመታት ውጥን ካፒታሉን ወደ አራት ቢሊዮን ብር ማድረስ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የሸሪዓ ሕግን ተከትሎ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ባንክ የሚሰጥ ተቋም መመሥረት የዓመታት ሕልማቸው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሙኒር፣ ባንኩ ከኢትዮጵያ ባሻገር በሌሎች አገሮች የሚገኙ የሸሪዓና የባንክ አማካሪዎችን በመያዝ ተጠሪነቱ ለባንኩ ቦርድ አመራር እንደሚሆን የተገለጸ የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ በማቋቋም ከሸሪዓው ሥርዓት አንፃር ቁጥጥርና ክትትል የሚደረግበት አካሄድ ይዘረጋል ብለዋል፡፡

‹‹በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ ባደረግነው ጥናት፣ ኢስላማዊ መርህን የተከተለ የተቀማጭ ገንዘብ፣ የፋይናንስ፣ የኢንቨስትመንትና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን አረጋግጠናል፤›› ያሉት አቶ ሙኒር፣ በእስላማዊ መርህ መሠረት የባንክ አገልግሎት የዘረጉ በርካታ አገሮች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ አኳያ ሲታይ ግን መደበኛው የባንክ አገልግሎት በአብዛኛው ወለድ ላይ የተሠረተ በመሆኑ፣ ከወለድ ጋር የተገናኘ ማንኛውንም የባንክ አገልግሎት ለማይፈልግ የኅብረተሰብ ክፍል አማራጭ የባንክ አገልግሎት ማቅረብ ሳይቻል ረዥም ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መሰጠት ተጀምሯል፡፡

ባንኮች ከወለድ ነፃ አገልግሎት እንዲያቀርቡ የሚፈቅደው የብሔራዊ ባንክ አዋጅ መውጣቱን ተከትሎ፣ በመመርያ የወለድ ነፃ የመስኮት አገልግሎት ተፈቅዶ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ከሰኔ ወር ወዲህ ሙሉ በሙሉ ወለድ አልባ የባንክ ሥራዎችን ማከናወን የሚፈቅደው መመርያ በመውጣቱ፣ ወልድ አልባ ባንኮች እንዲቋቋሙ መንገዱን ከፍቷል፡፡ ዛድ ባንክም ይህንኑ ተከትሎ የአክሲዮን ሽያጭ እንደጀመረ አስታውቋል፡፡ ‹‹እስላሚክ ባንክ ለማኅበረሰቡ ጎጂና ኢሞራላዊ ለሆኑ፣ እንዲሁም በሸሪዓው ለተከለከሉ ንግዶች ድጋፍ ስለማያደርግ፣ አብሮም ስለማይሠራ ለኅብረተሰቡ አስፈላጊና ጠቃሚ ኢንቨስትመንቶች እንዲበረታቱ አስተዋጽኦ ያደርጋል፤›› ያሉት አቶ ሙኒር፣ አገራዊ ፋይዳውን በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡      ኢስላሚክ ባንኪንግ ወይም ወለድ አልባ የገንዘብ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ማቋቋም ከተፈቀደ ወዲህ ዛድን ጨምሮ አራት ባንኮች (በምሥረታ ላይ ያሉ) ወደ አክሲዮን ሽያጭ የገቡት በተመሳሳይ ጊዜ በአንድ ላይ መሆኑ ግን ሒደቱን አነጋጋሪ አድርጎታል፡፡ ለዛድ ባንክ አደራጆች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል ወለድ አልባ ባንኮችን ለመመሥረት ሁሉም አደራጆች በአንድ ጊዜ መነሳታቸውና የአክሲዮን ሽያጭ መጀመራቸው አደጋ የለውም ወይ? የሚለው ቀዳሚው ነበር፡፡ በተጨማሪም ወለድ አልባ ባንክ በማደራጀት ላይ ያሉትና ሌሎችም በእንዲህ ያለው ተናጠላዊ ግን ደግሞ ተመሳሳይ ዘርፍ ላይ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በማድረግ በፈለጉት ጊዜ ተፈላጊውን ካፒታል አሰባስበው ወደ ሥራ ለመግባት አይቸግራቸውም ወይ? የሚል ጥያቄም ቀርቧል፡፡

ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው ዝቅተኛው የተከፈለ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር እንዲሆን ከተደነገገ በኋላ አንድም ባንክ ሊመሠረት አልቻለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ 500 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ ከባድ በመሆኑ ነው፡፡ ዛድ ባንክ ይህንን ሥጋት እንዴት እንደሚወጣው ምላሽ የሰጡት አቶ ሙኒር፣ ይህ ሥጋት እንደማይሆን አስታውቀዋል፡፡

በምሥረታ ላይ የሚገኙት ኢስላማዊ ባንኮችን መበራከት በተመለከተም፣ ‹‹የት ላይ ቆመን ነው ይህንን የምለው?›› በማለት፣ የባንክ ተደራሽነት እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ባንኮቹ በዝተዋል በሚለው ጥያቄ እንደማይስማሙ ገልጸዋል፡፡ በባንክ የማይጠቀም ኅብረተሰብ ክፍል በጣም ብዙ በመሆኑና የገበያ ፍላጎትም ከፍተኛ በመሆኑ፣ ተበራክተው የመጡት ወለድ አልባ ባንኮች ችግር አይፈጥሩም ብለዋል፡፡

‹‹ወለድ መቀበልም ሆነ መጠየቅ ክልክል በመሆኑ፣ ወደ ባንክ የማይመጣ፣ ከባንክ የማይበደር፣ በባንክ የማያስቀምጥ የኅብረተሰብ ክፍል በጣም ብዙ ከመሆኑ አንፃር በቁጥር በርከት ብለው ቢመጡ ችግር የለውም፤›› ይላሉ፡፡ አያይዘውም በአንድ አገር ውስጥ ይህንን ያህል ወለድ አልባ ባንክ ብቻ ያስፈልጋል የሚል ቀመር እንደሌለ የሚናገሩት አቶ ሙኒር፣ በተወሰኑ አገሮች ውስጥ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ግን ደግሞ ትልልቅ አቅም ያላቸው ባንኮች እንዳሉ ዋቢ ያደርጋሉ፡፡ አነስተኛ አቅም ያላቸው ባንኮች ኖሯቸው ቁጥራቸው ግን በርካታ የሆኑባቸው አገሮች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ‹‹ዋናው ነገር ተደራሽ መሆናቸው ነው፡፡ ባደረግነው ጥናት የእኛ አገር የባንክ ተደራሽነት ዝቅተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ተደራሽነቱን በማስፋት መብዛታቸው ከገበያው ፍላጎት ጋር የሚያያዝ ነው፤›› ብለዋል፡፡  

በአገሪቱ እየመጡ ያሉትን ባንኮች ጉዳይ እንዳጠኑ የገለጹት አቶ ሙኒር፣ እየመጡ ካሉት ባንኮች ጋር ሊኖር የሚችለው ውድድር ብቻም ሳይሆን፣ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም በባንክ መስክ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለውን ነገር በመገመት እያዩት እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ክፍት ሲደረግ፣ የውጭ ባንኮች ሊመጡ ስለሚችሉ ውስጣዊና ውጫዊ ሥጋቶችን የሚመልስ ስትራቴጂ ነድፈን እየተንቀሳቀስን ነው፤›› በማለት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡        

ከወለድ አልባ ባንኮች ጋር በተያያዘ የሚጠቀሰው ሌላው ችግር በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚታየው የሰው ኃይል እጥረት ነው፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ ወለድ አልባ ባንኮች ተበራክተው መምጣታቸው ሥጋት ሊሆን እንደሚችል ይነገራል፡፡ ይህንን ሥጋት አቶ ሙኒርም ይጋሩታል፡፡ በምሥረታ ላይ ለሚገኙት የተቀሩት ባንኮችም ፈተና እንደሚሆንባቸው አቶ ሙኒር ይስማማሉ፡፡ በኢስላሚክ ባንኪን የሠለጠነ በቂ ባለሙያ ባለመኖሩ ለሚከፈቱት ባንኮች ሁሉ የሚበቃ ባለሙያ ላይኖር እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ክፍተቱን በማየት ከወዲሁ ዝግጅት እንደተጀመረ፣ በባለሙያ እጥረት ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት ለመቅረፍም የተለያዩ አማራጮችን በመዘርጋት ዝግጅት ስለተደረገ ዛድ ባንክ ሥራ በሚጀምርበት ወቅት ችግር እንዳይገጥመው በተለያዩ  የሰው ኃይል ልማት ከወዲሁ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ የወለድ አልባ አገልግሎት መጀመር አዲስ በመሆኑ በርካታ ጥያቄዎች መሰንዘራቸው አይቀሬ ነው፡፡  በመሆኑም ምላሽ የሚሰጡ ዕቅዶች መነደፋቸውን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ይህን መሰል ባንክ መመሥረት ለምን አስፈለገ ከሚለው ጀምሮ በርካታ ጥያቄዎች ይሰነዘራሉ፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅትም ይኼው ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ መደበኛው የባንክ አገልግሎት ከወለድ አልባ ባንክ መለየት አለበት ያሉት አቶ ሙኒር፣ ‹‹ወለድ አልባ ባንክ አዲስ ነው፡፡ ስለዚህ ወለድን መጠቀም የማይፈልገው ኅብረተሰብ ለረዥም ጊዜ ባንክ ላይ ኢንቨስት ለማድረግና የባንክ ባለቤት ለመሆን ቢፈለግም ሳይሆንለት የቆየበት ዋናው ምክንያት መደበኛው ባንክ በወለድ ስለሚሠራ ነው፡፡ የእኛ ግብ ይህን የኅብረተሰብ ክፍል መድረስ ስለሆነ ከፍተኛ አቅም አለ ብለን እናምናለን፤›› ይላሉ፡፡ ይህ በመሆኑም ባንኩን ወደ ሥራ ለማስገባት ያስፈልጋል የተባለውን ካፒታል በአጭር ጊዜ አሰባስበን ወደ ሥራ እንደሚገባ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ባለ ሒደታቸው ተጠቃሽ የሚባል ተግዳሮት እንዳላጋጠማቸው የሚገልጹት አደራጆቹ፣ ዘርፉ አሁን ላለንበት ደረጃ እንዲደረስ የብሔራዊ ባንክ ትልቅ ሚና እንደነበረው አስታውሰዋል፡፡ አቶ ሙኒር ብሔራዊ ባንክ ቢሮክራሲ የሌለበት ቅን አገልግሎት እንዳገኙበትና እንዲያውም ለሌሎችም ተቋማት በምሳሌ የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ወይም እስላማዊ መርሆዎችን ተከትሎ የሚሠራ ባንክ ከባንክ ሥራው ባሻገር ሃይማኖታዊ ተግባሩ ይጎላል የሚለው ምልከታን የሚያንፀባርቁ አሉ፡፡ በዛድ ባንክ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይህንኑ የሚያመላክት ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ ‹‹ዛድ ባንክ ኢትዮጵያዊ ባንክ ልንለው እንችላለን፤›› ያሉት አቶ ሙኒር፣ አደራጆቹም ሆኑ ከዚህ በኋላ መሥራች ሆነው የሚመጡት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ ነው፡፡ አቶ ዛይድ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ይህንን ግንዛቤ ያመጣው እኛም እንዲደራጅ ይኼ ነገር እንዳለ ተረድተናል፡፡ ይኼ ግንዛቤ የመጣው በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስላልተሠራ ነው፡፡ በሁሉም ባለድርሻ በኩል ይህንን ግልጽ የማድረግ ነገር ቢሠራ ይኼ ነገር ወደዚህ ደረጃ አይደርስም ነበር የሚል እምነት አላቸው፡፡

‹‹ኢስላሚክ ባንክ፣ ባንክ ነው፡፡ ሌላ ምንም ማለት አይደለም፤›› ያሉት አቶ ሙኒር፣ የባንክ አገልግሎት ነው የሚሰጠው በማለት ሃይማኖትና ተግባሩ ይጎላል የሚለው አመለካከት ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የሁለት አገሮች ባንኮችን ጠቅሰዋል፡፡ ኩዌት ሐውስ ፋይናንስ የተባለ ማሊዥያ ውስጥ የሚገኝ ኢስላሚክ ባንክ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት የባንኩ አስቀማጮች ሙስሊም ያልሆኑ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ኢስላሚክ ባንክ ኦፍ ብሪቴንም ውስጥ ወደ 90 በመቶዎቹ ሙስሊም ያልሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህ የባንክ አገልግሎት የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡ ይህንን ለማስጠበቅም ሁሉም በግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ላይ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ እስላማዊ ባንኪንግ የተለየ የሚያደርገው የሚጠቀምባቸው መርሆዎች ከእስላማዊው የሸሪዓ መርሆዎች የሚፈቅዳቸው ቢዝነሶችን ነው፡፡ የሚሰጠው ግን የባንክ አገልግሎት ስለመሆኑ አስረድተው፣ በመደበኛውና በእስላሚክ ባንኪንግ መካከል ያለውንና ልዩነት አብራርተዋል፡፡ በተለይ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ያሏቸውንም ገልጸዋል፡፡

እስላሚክ ባንክ የትኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያስተናግድ ስለመሆኑ የጠቀሱት አቶ ሙኒር፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውና አማራጭነቱ የጎላ ስለመሆኑ አክለዋል፡፡

ስለዚህ ይህንን ግንዛቤ ካሳደርን ሰዎች በዚህ ባንክ በመጠቀም የሚያሳድጉት ቢዝነሳቸውን እንጂ ሌላ ነገር እንደሌላው በማስረዳት፣ በዚህ ደግሞ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ይሆናል ብለዋል፡፡

ዛድ ባንክ አንድ ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለመሸጥ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዝቅተኛ ደረጃ የሚሸጠው አክሲዮን 30 ሺሕ ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዕለቱ መግለጫ መገንዘብ እንደተቻለው እስካሁን 11 ባንኮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ነው፡፡

እነዚህ ባንኮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ወደ 40 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ተቀማጭ ገንዘብ ያሰባሰቡ ሲሆን፣ ወደ ስድስት ቢሊዮን ብር የሚገመት ከወለድ ነፃ በሆነ ኢንቨስትመንት ላይ ውሏል፡፡ ይህ ግን እጅግ አነስተኛ የሚባል በመሆኑ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶች መከፈት በዚህ ረገድ ኢንቨስት የሚደረገውን የገንዘብ መጠን ያሳድጋል፡፡ የባንክ ተደራሽነትም ይጨምራል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች