Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ወለድ አልባ ባንክ ሊቋቋም ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወልድ አልባ የመድን ኩባንያም ይመሠረታል ተብሏል   

ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን በስፋት ለማስጀመር እየተንቀሳቀሱና በምሥረታ ላይ ከሚገኙት አንዱ የሆነው ሒጅራ ባንክ፣ የአክሲዮን ሽያጭ በይፋ መጀመሩን አስታወቀ፡፡ በኢትዮጵያ ቀዳሚው እንደሚሆን የሚጠበቀውን ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ (ታካፉል) ኩባንያ እንደሚመሠርት ገልጿል፡፡

የሒጅራ ባንክ አደራጆች እሑድ ሐምሌ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በጎልፍ ክለብ ይፋ እንዳደረጉት፣ ለሁለት ዓመታት ሲያደርጉት የሰነበቱትን ዝግጅት አጠናቀው ወደ አክሲዮን ሽያጭ ገብተዋል፡፡ የባንኩ አክሲዮን ሽያጭም ከሐምሌ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በዘጠኝ ባንኮች በኩል በተከፈተ ዝግ ሒሳብ የሒጅራ ባንክ አክሲዮን ሽያጭ እንደተጀመረ ታውቋል፡፡

በአደራጆቹ መሠረት ለሽያጭ የተዘጋጁት አንድ ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አንድ ሚሊዮን አክሲዮኖች ናቸው፡፡ ባንኩ በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ሲያሰባስብ ወደ ሥራ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡ የአንድ አክሲዮን ዋጋ አንድ ሺሕ ብር ሲሆን፣ አክሲዮን መግዛት የሚፈልግ ሰው መግዛት የሚችለው ዝቅተኛ አክሲዮኖች ብዛት 30 ነው፡፡ በመሆኑም የሒጅራ ባንክ ባለአክሲዮን ለመሆን በትንሹ 30 ሺሕ ብር ዋጋ ያላቸውን 30 አክሲዮኖች መግዛት ይጠበቅበታል፡፡ በተጨማሪም አንድ ባለአክሲዮን እስከ 20 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች መግዛት እንደሚፈቀድለት ታውቋል፡፡ ከ200 ሺሕ ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች የሚገዙ ባለአክሲዮኖችም እንደ መሥራች አባላት ይታያሉ፡፡

ከ200 ሺሕ ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች የሚገዙ ባለድርሻዎች መሥራች ስለሚሆኑ፣ ባንኩ ማትረፍ ከጀመረበት ዓመት ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ከባንኩ 15 በመቶ ትርፍ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻ መሠረት የሚከፋፈሉ ሲሆን፣ የተቀረውን ትርፍም ከሌሎች ባለአክሲዮኖች ጋር ይጋራሉ፡፡

የሒጅራ ባንክ መሥራች ኮሚቴ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አህባቡ አብደላ በኢትዮጵያ ጠንካራና እየተስፋፋ የመጣ ወለድ አልባ አማራጭ የፋይናንስ ተቋማትን በተለይም ባንኮች የሚሰጡትን አገልግሎት የመጠቀም ፍላጎት እንዳለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ አስታውሰው፣ በዚህም ዘርፍ ብዙኃኑ የኅብረተሰብ ክፍል በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በሰፊው እንዲሳተፍ ለማስቻል ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ሚና ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ዘርፉ በመንግሥት ተቋማት እያገኘ ያለው ድጋፍና ዕገዛ በዚሁ ከቀጠለ፣ ዘለቄታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ብሎም፣ ከሰሃራ በታች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛነቱ የሚነገርለትን የፋይናንስ ተቋማትን ተደራሽነት አሁን ከሚገኝበት 35 በመቶ በ2020 ዓ.ም. ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ የተያዘውን አገራዊ ዕቅድ ለማሳካት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡

ሒጅራ ባንክ ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት እንደሚኖረው የሚገልጹት አደራጆቹ፣ አካታችና ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓትን በማስፈን ከፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት ተራርቆ የሚገኘው አብዛኛው ሕዝብ በኢኮኖሚው ውስጥ ንቁ ተዋናይ እንዲሆን ይህን መሰሉ የፋይናንስ አገልግሎት ዕገዛ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡ የመንግሥት ትኩረት ያረፈባቸውን ዘርፎች በማጤን በተለይ በግብርና፣ በእንስሳት ሀብት፣ በቱሪዝም መስክ፣ እንዲሁም የአረንጓዴ ልማት ይዘት ባላቸው ዘርፎች ላይ በመደራጀት ላይ የሚገኘው ባንክ ጉልህ ተሳትፎ እንደሚኖረው የገለጹት ቦርድ ሰብሳቢው፣ በአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪም አማራጭ የገንዘብ አገልግሎት አቅራቢ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡   

አደራጆቹ ላለፉት ሁለት ዓመታት አካታች የፋይናንስ ሥርዓት ተገቢነት ባለው መልኩ ተግባራዊ እንዲሆንና፣ በአገር ደረጃ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲፈጥር የተለያዩ ጥናቶችን፣ ተከታታይነት ያላቸውን ሥልጠናዎችና ሕዝባዊ ውይይት መድረኮችን ሲያከናውኑ ስለመቆየታቸው ተገልጿል፡፡ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ሥርዓትን በማበልፀግ ለዘመናት በአገራችን ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ባለው ውስን ተሳትፎ የሚታወቀውን ሰፊ የኅብረተሰብ ክፍል በአገሪቱ ዕድገት ላይ አዎንታዊ ሚናና ድርሻ እንዲኖረው ለማስቻል በርካታ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ የአቶ አህባቡ ንግግር ያመለክታል፡፡

ዘርፉን የተመለከቱ ትምህርትና ሥልጠናዎችን፣ እንዲሁም የልምድ ልውውጥ መድረኮችን በራስ ተነሳሽነት ሲያዘጋጁ የቆዩ አደራጆች ከአገር ውጭ በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጉዞዎችን በማድረግ በአገራችን የሚገኙ ባንኮችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ የወለድ ነፃ የፋይናንስ ሥርዓት ተቋማትና ኤክስፐርቶች ጋር በማገናኘት ለዘርፉ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ቆይተዋልም ተብሏል፡፡

በምሥረታ ላይ የሚገኘው የሒጅራ ባንክ አደራጆች እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ፣ በኢኮኖሚው መስክ ጉልህ አሻራ ለማኖር መንግሥት የጀመረው ሥር ነቀል ለውጥን የሚያግዝ አካታች የፋይናንስ ሥርዓትን በማስፋፋትና ተደራሽ በማድረግ የፋይናንስ ዘርፉ ላይ የሚታየውን የአገልግሎትና የተደራሽነት ክፍተት ለማጥበብ ወደፊትም ቀስ በቀስ ለማስወገድ ወለድ አልባው አገልግሎት ወሳኝ ሚናውን እንደሚጫወት እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሒጅራ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከማቅረብ ባሻገር፣ ከባንኩ ጋር መሳ ለመሳ የሚሠራና ‹‹ተካፉል›› የተባለ የኢንሹራንስ ኩባንያ ለማቋቋም መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ይህ የመድን ኩባንያ ከመደበኛው የኢንሹራንስ አገልግሎት ለየት የሚሉ ግልጋሎቶች የሚቀርቡበት ሲሆን፣ በአብዛኛውም ከወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት መርሆዎች ጋር ተመሳሳይነት ያለው እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡

ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ራሱን ችሎ እንደ መደበኛ ባንክ መቋቋም የሚችልበትን አዎንታዊ ምላሽ ከመንግሥት በቅርቡ ማግኘቱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ባንኮች በመስኮት የወለድ አልባ አገልግሎትን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በሚከተሉት እምነት ሳቢያ በመደበኛው የባንክ አገልግሎት መጠቀም ያላስቻላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የባንክ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችለው የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት መጀመር ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

የወለድ አልባ አገልግሎት ራሱን ችሎ መስጠት ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ፣ ባንኮች በርካታ ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመጣ አስችሏል፡፡ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የጀመሩ ባንኮችም እስካሁን 30 ቢሊዮን ብር ገደማ በቁጠባ ለማስቀመጥ አስችሏል፡፡ ወለድ አልባ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች መቋቋማቸው ከባንክ ውጪ የሚንቀሳቀሰው ሰፊ ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመጣ፣ በእምነታቸው ምክንያት ገንዘባቸውን በባንክ ለማስቀመጥ የተቸገሩ ዜጎችም በሚፈልጉት የንግድና የኢንቨስትመንት መንገድ እንዲገለገሉበት እንደሚያስችል ይታመናል፡፡

እንዲህ ያሉ ባንኮች የባንክ ኢንዱስትሪውን መቀላቀላቸው ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳው የገለጹት የሒጅራ ባንክ አደራጆች ቦርድ ሰብሳቢ፣ መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ የሰጠውን ትኩረትና ተግባራዊ ምላሽ በማጤን ከሁሉም የአገራችን ክፍል በተውጣጡና በማኅበራዊ ተሳትፏቸው በሕዝብ ዘንድ መታመንን ባተረፉ ዜጎች አነሳሽነትና መሥራችነት እየተቋቋመ የሚገኝ ባንክ ነው፡፡ ከመሥራቾቹ መካከል የፋይናንስ፣ የኢንቨስትመንትንና የቢዝነስ አማካሪዎች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ በዘርፉ በአገር ውስጥና በውጭ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ምሁራን የተካተቱበት መሆኑ ተወስቷል፡፡

ሒጅራ ባንክ የተሟላ አካታች የፋይናንስ ሥርዓትን ዕውን መሆን በከፍተኛ ጉጉት ለሚጠብቀው የኅብረተሰብ ክፍል አክሲዮን መሸጥ የሚያስችለውን ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ ካገኘ አንድ ወር ያለፈው ቢሆንም፣ በዘርፉ የሚስተዋለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለማረምና የትግበራ ሒደቱን በአግባቡ ለማሳየት በተለያዩ ክልሎች በመዟዟር ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ሲያካሂድ ቆይቷል ተብሏል፡፡

በአደራጆቹ ዕቅድ መሠረት ባንኩን ለመመሥረት የሚያስችላቸውን የ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል በስድስት ወራት ውስጥ አሰባስበው ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ባንኩን ሥራ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡ በተያዘው ዕቅድ መሠረት ባንኩን መመሥረት ከተቻለ፣ በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው ዝቅተኛው ካፒታል ቀድሞ ከነበረው 100 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር ካሳደገ ወዲህ የሚቋቋም የመጀመርያው ባንክ እንሚሆን ይጠበቃል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከሰባት ዓመታት በፊት የባንክ መቋቋሚያ ዝቅተኛውን ካፒታል ወደ 500 ሚሊዮን ብር ሲያሳድግ፣ ለመቋቋም በዝግጅት ላይ የነበሩና አክሲዮን ሲሸጡ የነበሩ አክሲዮን ኩባንያዎች የግማሽ ቢሊዮን ብር የተከፈለ አክሲዮን ማሰባሰብ እንደሚያዳግታቸው በማስታወቅ እንቅስቃሴያቸውን እንዳቋረጡ ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮችን ለማቋቋም የሚንቀሳቀሱ አምስት ባንኮች በዚሁ መመርያ መሠረት፣ 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በማሰባሰብ ወደ ሥራ ለመግባት ዳር ዳር እያሉ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሌላ ነፃ የሚል መጠሪያ ያለው ባንክም በተመሳሳይ አክሲዮን እየሸጠ ነው፡፡ ሒጅራ ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ ስለመጀመሩ ይፋ ባደረገበት ፕሮግራም ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የኡለሞች ምክር ቤት ሰብሳቢ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስና ሌሎችም ታዋቂ ሰዎች ታድመው ነበር፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች