Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የከተማ አስተዳደሩ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ የሚወጣባቸው ፕሮጀክቶችን ለውጭ ኮንትራክተሮች ሰጠ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገር በቀል ኮንትራክተሮች ቅሬታ አሰምተዋል

በምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥልጣን በተረከበ አንደኛ ዓመት ማግሥት፣ በከተማው ገጽታ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣሉ የተባሉ ስድስት ፕሮጀክቶችን ለውጭ ኩባንያዎች ሰጠ፡፡ ሐሙስ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ምክትል ከንቲባው በተገኙበት የከተማ አስተዳደሩ ባለሥልጣናት፣ 10.7 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚደረግባቸውን ፕሮጀክቶች ከአምስት የውጭ ኩባንያዎች ጋር በመፈራረም አስረክበዋል፡፡

የመጀመርያው ፕሮጀክት ፒያሳ ማዘጋጃ ቤት ፊት ለፊት በሚድሮክ ተይዞ በነበረውና ለዓመታት ያለ ግንባታ ታጥሮ በመቆየቱ ምክንያት በተነጠቀው፣ 30,300 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባው ዓድዋ ፓርክ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘውና ወደ የትኛውም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚደረግ ጉዞ የሚጀመርበት ይህ ቦታ፣ ‹‹ሁሉም ከዚህ ይጀምራል!›› የተባለውን ፕሮጀክት የቻይናው ጂያንግሱ ሊትድ በ4.6 ቢሊዮን ብር ለመገንባት ውል ገብቷል፡፡

ሁለተኛው ፕሮጀክት አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ የሚገነባው ቤተ መጻሕፍት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በ19 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባ ሲሆን፣ 30 ሺሕ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል ቤተ መጻሕፍት ይሆናል ተብሏል፡፡

ይህን ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ውስጥ የሚታወቀው የጣሊያን ጂኦም ሉጂ ቫርኔሮ ኩባንያ ለመገንባት የተረከበ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ቫርኔሮ በሸራተን ማስፋፊያ ላይ የታቀደው የወንዝ ዳር ልማት በ2.5 ቢሊዮን ብር እንዲገነባ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን ፕሮጀክት በቻይና ኩባንያ እንዲሠራ በመፈለጉ ሥራው ከቫርኔሮ መነጠቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሦስተኛው ፕሮጀክት ከቦሌ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ በ22 ማዞሪያ አድርጎ እንግሊዝ ኤምባሲ ድረስ የሚገነባው መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ በአሁኑ ወቅት በመገንባት ላይ ያለው አደይ አበባ ስታዲየም ሥራ ሲጀምር፣ ሊፈጠር የሚችለውን የትራፊክ መጨናነቅ ከወዲሁ ለመቅረፍ ታስቦ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ 3.133 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን 330 ሚሊዮን ብር ወጪ ይደረግበታል ተብሏል፡፡ ለግንባታው የተስማማው ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባውን የቀለበት መንገድ የገነባው የቻይናው ሲአርቢሲ ነው፡፡ ሲአርቢሲ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት ስሙን በመቀየር አይኤፍኤች ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ተብሏል፡፡ ይህ የመንገድ ፕሮጀክት የሚነካቸውን ቤቶች በቅርቡ ማፍረስ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አራተኛው ፕሮጀክት አዳምስ ፓቪሊዮን አካባቢ ከሚገኘው ፑሽኪን አደባባይ እስከ ጎተራ ማሳለጫ ድረስ የሚገነባው ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከታሰበና ዲዛይኑ ከተሠራ ሦስት ዓመት ያለፈው ሲሆን፣ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ያለበት ነው፡፡ መንገዱ 2.3 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ ከ30 እስከ 45 ሜትር ስፋት አለው፡፡ ይህንን ሥራ የቻይናው ግዙፍ ኩባንያ ሲሲሲሲ ተረክቦታል፡፡

አምስተኛው ፕሮጀክት ከአራት ኪሎ ወደ ካዛንቺስ በሚወስደው መንገድ ከሒልተን አዲስ አበባ ከፍ ብሎ በሚገኘው አሥር ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ፣ አንድ ሺሕ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ መያዝ የሚችል ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ሕንፃ ነው፡፡ ይህንን ፕሮጀክት የቻይናው ጂያንግሱ ሊትድ ለመገንባት ተረክቧል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ቤተ መንግሥቱን ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ ሲታሰብ፣ ሊፈጠር የሚችለውን የፓርኪንግ ችግር ለመቅረፍ ሲባል የታሰበ ፕሮጀክት ነው ተብሏል፡፡

ስድስተኛው ፕሮጀክት ከተገነባ 46 ዓመታትን ያስቆጠረውና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በቂ ዕድሳት ያልተደረገለትን ማዘጋጃ ቤት ማደስ የሚያስችል ነው፡፡

ይህ ሥራ ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያ አሌክ ፊት አውት ተሰጥቷል፡፡ በአምስት የውጭ አገር ኩባንያዎች የሚገነቡት እነዚህ ስድስት ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 10.7 ቢሊዮን ብር ይወጣባቸዋል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ከንቲባው እነዚህ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ሳይሆን ከተያዘላቸው ቀነ ገደብ ባነሰ ጊዜ ይጠናቀቃሉ ብለዋል፡፡

‹‹በፕሮጀክት ጅማሮ ላይ መናገር ትንሽ ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር መናገር ጥሩ ስለሆነ፡፡ ነገር ግን እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ሥራ እንደሚጀምሩ ነው፤›› ሲሉ ምክትል ከንቲባው በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

በከፍተኛ የፋይናንስ ብቻ ሳይሆን የሥራ ዕጦት ላይ የሚገኙ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ለፕሮጀክቶቹ መልካም አመለካከት ቢኖራቸውም፣ ሥራው ለውጭ ኩባንያዎች ብቻ መሰጠቱ ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል፡፡

ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል የአመሐ ስሜ ኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤት የሆኑት አቶ አመሐ ስሜ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት አገር በቀሉ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛል፡፡

መንግሥት ባለፈውም ሆነ በዚህ ዓመት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እንደማይጀምር፣ ይልቁኑም የተጀመሩትን ለማጠናቀቅ እንደሚሠራ መግለጹን አቶ አመሐ ያስታውሳሉ፡፡

ከዚህ ባሻገርም እጃቸው ላይ ሥራ የነበራቸውም ኮንትራክተሮች ባለፉት ዓመታት በነበሩ የተለያዩ የዋጋ ጭማሪዎች፣ የውጭ ምንዛሪ ከብር ጋር የነበረው ልዩነት መስፋትና እጥረት፣ በተዋዋሉት ዋጋ ሥራ አጠናቀው ማስረከብ ያልቻሉ ኮንትራክተሮችም በርካታ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለማድረግ የታሰበው ውይይት እስካሁን ባለመካሄዱ፣ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቀዋል ይላሉ፡፡

‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለውጭ ድርጅቶች ብቻ ሥራ መስጠቱ በአገር ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን አቅም ያቀጭጨዋል፡፡ ቢያንስ ከውጭ ድርጅቶች ጋር የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን በማቀናጀት ወይም በሰብ ኮንትራት ሥራ የሚገኙበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት፤›› በማለት የገለጹት አቶ አመሐ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች