የአገሪቱ ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በሚያሳይበት ወቅትም የኢትዮጵያ ባንኮች ከተለመደው የላቀ በማትረፍ ከዓመት ዓመት በመጓዝ ላይ ይገኛሉ፡፡ የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸውም በየጊዜው እያደገ እንደመጣ ከሚያወጡት የፋይናንስ ሪፖርታቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እየተዳከመ መምጣቱ እየተጠቀሰ፣ የዋጋ ንረትም ባለሁለት አኃዝ ሆኖ ዓመቱን ቢያሳልፍም የባንኮች አጠቃላይ አፈጻጸም ግን ከሌላው የንግድ ዘርፍ የተለየ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል፡፡ ባንኮች የኢኮኖሚው መንገዳገድ ሳይነካቸው፣ ትርፋቸውን ሳይሸርፈው መዝለቃቸው ግን አነጋጋሪ እንደሆነ የሚጠቁሙ አሉ፡፡
የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ዘርፍ በአሳሳቢ ማሽቆልቆል ውስጥ በመሆኑ፣ ዘርፉ የሚያስገኘው ገቢም እየተዳከመ በመምጣቱ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ዝቅተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ በአንፃሩ አገሪቱ ከውጭ ለምታስመጣው መጠነ ሸፊ ሸቀጦችና የካፒታል ዕቃዎች የምታውለውን ገንዘብ ሊያስገኝ ባለመቻሉ፣ ከብድርና ዕርዳታ፣ ከውጭ ሐዋላ፣ ከውጭ ኢንቨስትመንትና ከመሳሰሉት ምንጮች የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ለገቢ ዕቃዊዎች ግዥ እንዲውል ምክንያት ሆኗል፡፡ የተዛባ የንግድ ሚዛን ብቻም ሳይሆን፣ የአገሪቱን የውጭ ዕዳ መጠን እየተበራከተ እንዲመጣም ሰበብ ሆኗል፡፡
በመሆኑም የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ዕጦት ፈታኝ በሆነበት ወቅት የባንኮች የትርፍ ዕድገት ከቀደሙት ዓመታት በላይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የሚዋዥቀው ኢኮኖሚ ሳይነካቸው በከፍተኛ አትራፊነታቸው ተጉዘው፣ በተሸኘው የ2011 ዓ.ም. በተቀማጭ ገንዘብ መጠን፣ ለብድር ያዋሉት ገንዘብ፣ ወጪና ገቢያቸው ተቀናንሶ ያስመዘገቡት ትርፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በተለይ የ16ቱ የግል ባንኮች የ2011 ሒሳብ ዓመት ግርድፍ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በጥቅል ያተረፉት ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት በአምስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ዕድገት አሳይቷል፡፡ እንዲህ ያለው አፈጻጸም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክም እንደተመዘገበ ታይቷል፡፡ ከግል ባንኮች አፈጻጸም አንፃር 16ቱ ባንኮች ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት በጥቅሉ 14.8 ቢሊዮን ብር አትርፈዋል፡፡ ባንኮቹ በ2010 ዓ.ም. በጥቅል ያስመዘገቡት ትርፍ 10.48 ቢሊዮን በመሆኑ ትርፋቸው ከፍተኛ በሚባል ደረጃ አድጓል ማለት ይቻላል፡፡
የሒሳብ ሪፖርታቸው እንደሚያሳየው፣ የግል ባንኮቹ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት በተናጠል ያስመዘገቡት ትርፍ ከ250 ሚሊዮን ብር እስከ 3.3 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከሦስት ባንኮች በቀር የተቀሩት የግል ባንኮች በተናጠል ከታክስና ተቀናሾች በፊት ያስመዘገቡት አማካይ ትርፍ ከ600 ሚሊዮን በላይ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ከአንድ ቢሊዮን ብር ጀምሮ እስከ 3.3 ቢሊዮን ብር ያተረፉ ባንኮች ብዛት አምስት ሲሆኑ፣ የአገሪቱ ባንኮች ከትርፍ አንፃር ከውጤታማነት በላይ የሆነ ግስጋሴ እያሳዩ እንደሚገኙ ያመላክታል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ ወጋገን ባንክ ብቻ ከቀደመው ዓመት የትርፍ መጠኑ በ19 በመቶ ቅናሽ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ሌሎቹ ባንኮች ግን ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ያገኙት ትርፍ ዕድገት ከ15 እስከ 106 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ በ2011 የሒሳብ ዓመት የትርፍ ዕድገቱን 106 በመቶ ማድረስ የቻለው ደቡብ ግሎባል ባንክ ሲሆን፣ ዓባይ ባንክ 86 በመቶ፣ ዘመን ባንክም በ82 በመቶ ትርፋቸውን አሳድገዋል፡፡ 16ቱ ባንኮች ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ያተረፉት የትርፍ በመጠን በአማካይ 40 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑ ከፍተኛ የትርፍ ዕድገት እንደሆነ አመላካች እንደሆነ የሚጠቅሱ አሉ፡፡
እንደ ዓመታዊ ትርፋቸው ሁሉ የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸውም ወደ 60 በመቶ ዕድገት የታየበት ስለመሆኑ ከዚሁ ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት መገንዘብ ይቻላል፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ፣ እስከ ሒሳብ ዓመቱ ማጠናቀቂያ ድረስ የ16ቱም የግል ባንኮች ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ ከ359.4 ቢሊዮን ብር ደርሶ ነበር፡፡ ይህ አኃዝ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ81.7 ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ እንዳሳየ ያመለክታል፡፡ በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ 277.6 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ የግል ባንኮችን የብድር አሰጣጥ በተመለከተም፣ እስከ ሰኔ 2011 ዓ.ም. መጨረሻ የባንኮቹ ብድር ክምችት 259.2 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታይቷል፡፡ ይህም ከዓምናው የሒሳብ ዓመት አንፃር የ42 በመቶ ዕድገት ያሳየበት ሲሆን፣ የለቀቁትና የፈቀዱት የብድር መጠን ከ76.4 ቢሊዮን ብር በላይ ነበር፡፡
የአገሪቱ ኢኮኖሚ ተቀዛቅዞ ባንኮች እንዲህ ባለው ደረጃ ማትረፋቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ የአገሪቱ ባንኮች አጣብቂኝ ውስጥ ባለ ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲህ ባለ ደረጃ ማትረፋቸው ጥሩ ቢሆንም፣ እያገኙ ያሉት ትርፍ ቀጣይነት ያለው ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ እንደሚያሳስባቸው የሚገልጹ የኢኮኖሚና የባንክ ባለሙያዎች አሉ፡፡
በባንክ ኢንዱስትሪው ከ20 ዓመታት በላይ ያገለገሉ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የባንክ ባለሙያ እንደገለጹት፣ ‹‹ባንኮች ከሌሎች የንግድ ዘርፎች ተለይተው እየተመነደጉ የመሄዳቸው ነገር እንደ ቢዝነስ መልካም ነገር ነው፡፡›› ይሁን እንጂ ትርፋቸው ከየትኛው የባንክ አገልግሎት ተገኘ? የሚለው ሲታይ ሁሉም ባንኮች ይበልጥ ትርፍ ወደሚገኝበት የገቢ ንግድ ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው፣ ይህ አካሄዳቸው ሊያዛልቅ እንደማይችል አስተያየት ሰጪው ያምናሉ፡፡
በ2011 ዓ.ም. ባንኮች ያስመዘገቡትን ትርፍ በተመለከተ ግርድፍ መረጃውን ያጣቀሱት እኚህ ባለሙያ፣ የአገሪቱ ባንኮች የሰጡት የብድር መጠን ከፍ ማለቱን በዚህም ጭምር ትርፋቸው ማደጉን ጠቅሰዋል፡፡ የባለሙያው ግርታ ግን ባንኮች ኢኮኖሚው ተቀዛቀዘ በሚባልበት ወቅትም የሰጡት የብድር መጠን ከሚጠበቀው በላይ ዕድገት ማሳየቱ ላይ ነው፡፡ ቢሆንም ብድሩን የሰጡት ለየትኛው ዘርፍ ነው ሲባል፣ ዳጎስ ያለ የአገልግሎት ክፍያ የሚጠየቅበት ዘርፍ ላይ የመሆኑ ጉዳይ አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ለመጥቀም ብሎም ባንኮችን ቀጣይነት ያለው ትርፍ የሚያገኙበት ዘርፍ ላይ አለመሆኑ ሥጋታቸው ነው፡፡
የትርፍ ዕድገቱ ዘላቂ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ እንደሚያነጋግር አስተያየት የሰጡ ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያ በበኩላቸው፣ ባንኮች ያሳዩት አፈጻጸም ጤነኛ ነው ወይ? የሚለውን ለመግለጽ የግድ ባንኮቹ ትርፍ ያገኙበትን ዘርፍ መለየቱ ግድ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ባንኮቹ ብዙ ትርፍ የሚገኝበት የገቢ ንግድ ላይ ብቻ በማተኮራቸው ትርፋቸውን እንዳናረው ይገልጻሉ፡፡ አንዳንድ ባንኮች ለወጪ ንግድ ያዋሉት ብድር ከፍተኛ ሲሆን፣ የብድሩ መመለስ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ያለውን ጥቂት የውጭ ምንዛሪ ለገቢ ንግድና ተያያዥ ሥራዎች በማዋል ከፍተኛ የአገልግሎት ዋጋ እየጠየቁ ትርፋቸውን የሚያሳድጉ ከሆነ ግን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ዘርፍ ተዘንግቷል ማለት ነው ብለዋል፡፡
የባንክ ባለሙያውም ሆኑ የኢኮኖሚ ባለሙያው የሚስማሙበት ነጥብ በተለይ ባንኮች ትርፍ እያገኙበት ያለው ዘርፍ የወጪ ንግዱ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን ነው፡፡ ኢኮኖሚው በተቀዛቀዘበት ሁኔታ ውስጥም ባንኮቹ የሰጡት ብድር ማደጉ እንዴት ሊሆን ቻለ? የሚለውን ጥያቄ ሊያስነሳ እንደሚችል የጠቆሙት ባለሙያዎቹ፣ ለየትኛው ዘርፍ ብድር ሰጡ? በኢኮኖሚው የትኛው ዘርፍ ነው የተሻሻለውና ለዕድገቱ አስተዋጽኦ ያደረገው? ሲባልም በአመዛኙ ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዘው መስክ እንደሆነ የሚጠቁም ሐሳብም ሰንዝረዋል፡፡
‹‹መኪና ልግዛ ብትል እንደፈለክ ታገኛለህ፡፡ ጫማና ልብስ ለመግዛትም አትቸገርም፡፡ በአንፃሩ ግን ለአንድ ፋብሪካ ጥሬ ዕቃ መግዛት ግን አትችልም፤›› በማለት በምሳሌነት ያነሱት የባንክ ባለሙያው፣ ይህ የሚያሳየው የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ለየትኛው ዘርፍ እንደዋለ እንደሚያሳይ ይገልጻሉ፡፡
በእንዲህ ዓይነቱ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምና አሰጣጥ ላይ የሚጠየቀው የአገልግሎት ክፍያ ከፍተኛ በመሆኑ፣ የአንዳንድ ባንኮችን ትርፍ ሊያሳድገው እንደቻለ ባለሙያዎቹ ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በተለይ ለዳያስፖራው በተፈቀደው የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ እያደገ የመጣው የገቢ ንግድ፣ ለባንኮቹ ትርፍ ዕድገት ትልቅ ሚና አለው ይላሉ፡፡ ባንኮቹም ቢሆኑ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡና ኢኮኖሚውን እንደገና እንዲያንሰራራ ከሚያደርጉት ዘርፎች ይልቅ፣ የውጭ ምንዛሪውን የሚያመጣው ደንበኛ ፍላጎት ብድር ወደ መስጠቱ ሊያደሉ ይችላሉ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተቀዛቅዟል ተብሎ ባንኮቹ ግን በትርፍ ተንበሽብሸዋል ሲባል ግር ሊል ይችላል፤›› ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ባንኮቹ የሰጡት ብድር መጠን ግን ዕድገቱን ያሳያል፡፡ በሌላው በኩል ደግሞ ኢኮኖሚው ማነቆ ውስጥ ገብቶ እየተንገዳገደ ነው የሚልም አለ፡፡ ስለዚህ ይኼ እንዳይፈነዳ የባንኮቹ የብድር ጥራት በየዘርፉ ሊታይ ይገባዋል ብለዋል፡፡
በተለይ ከወጪ ንግድ ጋር የተያያዙ ብድሮች ጤናማነታቸው መታየት እንዳለበትም ባለሙያዎቹ ያሳስባሉ፡፡ ለባንኮቹ ትርፍ ዕድገት ምክንያት የሆነው ሌላው ጉዳይ የብድር ወለድ ምጣኔያቸው መጨመር ነው፡፡ ስለዚህ የትርፍ አካሄዳቸውና እየመጡበት ያለው መንገድ ግን ቀጣይነት ያለው መሆኑ በደንብ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ በተለይ የብድሮቻቸው ጥራት መታየት አለበት፡፡
አንዳንዱ ብድር በማራዘም ማሻሻያ በማድረግ አገኘሁ የሚለው ትርፍ ሄዶ ሄዶ ለባንኩም ጉዳት እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡ ለምሳሌ ከጥቂት ወራት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኢኮኖሚው በመጎዳቱ ምክንያት ብድሩን የሚከፍሉበትን ጊዜ አራዝሞላቸዋል ተብሏል፡፡ ግን ሁሉንም ነገር ወስደን እዚያ ውስጥ የምንከተው ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ባንኮች እያገኙ ያሉት ትርፍ ጥሩ ቢሆንም፣ ዘላቂነቱንም በሚያረጋግጥ ሥራዎች ላይ ማተኮር ግድ ይላቸዋል ብለዋል፡፡