ድርጅቱ የ14 ቢሊዮን ብር ዕዳውን ከሚሰጠው አገልግሎት እንደሚከፍል ይጠበቃል
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በክፍያ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን የአዲስ አዳማ የክፍያ መንገድን ማስተዳደር ከጀመረ አምስት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም 31 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን በማስተናገድ እስካሁን 965 ሚሊዮን ብር ገቢ አሰባስቧል፡፡
50 ኪሎ ሜትር ለሚረዝመው የአዲስ አዳማ የክፍያ መንገድ ተከታይ የሆነው አዲሱን የድሬዳዋ ደዋሌ የክፍያ መንገድ በመረከብ፣ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ከሰኔ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በመንገዱ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን በማስከፈል አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ሲጂሲ በተባለው የቻይና ሥራ ተቋራጭ የተገነባው የድሬዳዋ ደዋሌ መንገድ 223 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውና ከ5.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የጠየቀ ነው፡፡ አንድ ተቋራጭ ብቻውን 223 ኪሎ ሜትር የገነባው ረዥሙ የመንገድ ፕሮጀክት እንደሆነ የሚጠቀሰው ይህ የክፍያ መንገድ፣ በሰባት ሜትር የመንገድ ስፋት የተገነባ ነው፡፡ መንገዱ ለጂቡቲ ወደብ የትራፊክ እንቅስቃሴ ዓይነተኛ ሚና ያለው ሲሆን፣ የወጪና ገቢ ዕቃዎች የሚስተናገዱበት ነው፡፡ መንገዱ ሦስት የክፍያ ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን፣ 12 መግቢያና 12 መውጫ በሮች አሉት፡፡
እንደ አዲስ አዳማ የክፍያ መንገድ ሁሉ የድሬዳዋ ደዋሌ የክፍያ መንገድ የራሱ ዋጋ ተመን የወጣለት ሲሆን፣ የአገልግሎቱ ክፍያ ግን ከአዲስ አዳማ በተለየ ነው፡፡ ከኢንተርፕራይዙ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የድሬዳዋ ደዋሌ መንገድ የዋጋ ተመን የተሽከርካሪዎችን መጠን በአራት በመከፋፈል ዋጋ ተሰልቶለት የሚሠራበት ነው፡፡
የኢንተርፕራይዙ የኮሙዩኒኬሽንና ማርኬቲንግ ቡድን መሪ ወ/ሮ ዘሀራ መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት አነስተኛ ለሆኑ ተሽከርካሪዎች 100 ብር፣ ሁለተኛ ደረጃ 150 ብር፣ ትላልቅ ተብለው ለተለዩትና በሦስተኛ ደረጃ ለተሰጣቸው ተሳቢ ያላቸው የጭነት ተሽከርካሪዎች ደግሞ 200 ብር የዋጋ ተመን ወጥቷል፡፡ በዚህ መንገድ ለመገልገል ከፍተኛ ዋጋ ተመን የወጣላቸው ተሳቢ ያላቸውና ከፍተኛ በሚል ለተለዩት ተሽከርካሪዎች ነው፡፡
እነዚህ ተሽከርካሪዎች ከድሬዳዋ ደዋሌ ድረስ ባለው መንገድ ሲጠቀሙ መክፈል የሚጠበቅባቸው 250 ብር ነው፡፡ ሆኖም የድሬዳዋ ደዋሌ የፍጥነት መንገድን ለመጠቀም የተተመነው ዋጋ አከፋፈል ግን ከአዲስ አዳማ የክፍያ መንገድ የአከፋፈል ዘዴ የተለየ አሠራር የሚተገበርበት እንደሆነ ከወ/ሮ ዘሀራ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ማንኛውም ተሽከርካሪ ከድሬዳዋ መግቢያ ወይም የክፍያ ጣቢያ ላይ ለተሽከርካሪው ከተመነው ዋጋ 50 በመቶውን ይከፍላል፡፡ ቀሪውን ክፍያ ግን ደዋሌ እስኪደርስ ድረስ ባሉት ሁለት የክፍያ ጣቢያዎች ሲደርስ የሚከፈል ነው፡፡
ይህ የተደረገው ያለምክንያት እንዳልሆነ ያብራሩት ወ/ሮ ዘሀራ፣ መንገዱ በአጥር ያልታጠረና ወጥ በመሆኑ አንድ ከድሬዳዋ የተነሳ ተሽከርካሪ ቀጣዮቹ ሁለት የክፍያ ጣቢያዎች ሳይደርስ ተገንጥሎ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መሄድ የሚችል በመሆኑ ነው፡፡
ደዋሌ ሳይደርስ ተገንጥሎ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚጓዝ ከሆነ ለድሬዳዋ ደዋሌ ከተተመነው ዋጋ ግማሹን ክፍያ ብቻ በመክፈል እንዲጠቀም ያስችላል፡፡
ሆኖም ጉዞው ከድሬዳዋ በኋላ በቀሪዎቹ ሁለት የክፍያ ጣቢያዎች አልፎ የሚሄድ ከሆነ ቀሪውን 25 በመቶ ሁለተኛው የክፍያ ጣቢያ ላይ እንዲከፈል ይደረጋል፡፡ ከሁለተኛው የክፍያ ጣቢያ ይህም አልፎ ሦስተኛው የክፍያ ጣቢያ ላይ ሲደርስ ደግሞ ቀሪውን 25 በመቶ እንዲከፈል የሚደረግበት አሠራር ነው፡፡
ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው የድሬዳዋ ደዋሌ መንገድ በክፍያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ የኢንተርፕራይዙን ገቢ በማሳደጉ ረገድ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ የሚኖረው መሆኑ ነው፡፡
ከሰኔ መጀመርያ ጀምሮ ሥራ የጀመረው ይህ መንገድ በቀን 860 ተሽከርካሪዎችን እያስተናገደ ሲሆን፣ በ2012 ዓ.ም. በቀን በመንገዱ የሚስተናገዱ ተሽከርካሪዎች ቁጥር አንድ ሺሕ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡ በዚህም ከድሬዳዋ ደዋሌ መንገድ ብቻ በቀን 200 ሺሕ ብር ገቢ ለማግኘት ስለመታቀዱ ወ/ሮ ዘሀራ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሥሌት ብቻ ለአገሪቱ ሁለተኛው የክፍያ መንገድ ከሆነው ከድሬዳዋ ደዋሌ ብቻ በዓመት ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት እንደታሰበ ያመለክታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢንተርፕራይዙ በ2011 ዓ.ም. ከአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ 275.5 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሰበሰበ የሚገልጸው የኢንተርፕራይዙ መረጃ ከተገኘው 275.5 ሚሊዮን ብር ውስጥ 264 ሚሊዮን ብሩ የተገኘው በበጀት ዓመቱ መንገዱን ከተጠቀሙ ከ8.48 ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች ተስተናግደው ነው፡፡ ቀሪው 11.2 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከማስታወቂያና ከሌሎች ልዩ ልዩ አገልግሎቶች የተገኘ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ የበጀት ዓመቱ ገቢ ከዓምናው ጋር በንፅፅር ሲታይ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ በ2010 ዓ.ም. ኢንተርፕራይዙ ያገኘው ጠቅላላ ገቢ 244 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ከኢንተርፕራይዙ የተገኘው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በ2012 በጀት ዓመት በአዲስ አዳማ የክፍያ መንገድ በቀን ከ25 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎችን፣ በዓመት 2.26 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን ለማስተናገድ ያቀደ ሲሆን፣ ከዚህ የትራፊክ ፍሰትም በዓመት ከ324.4 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሚሰበስብ ግምቱን አስቀምጧል፡፡
በተመሳሳይ በ2012 ዓ.ም. ከድሬዳዋ ደዋሌ የክፍያ መንገድ በቀን 1,200 ተሽከርካሪዎችን በማስተናገድ ከ220 ሺሕ ብር ገቢ እንደሚገኝ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ይህም በዓመታዊ ሥሌት ሲታሰብ፣ 438,000 ተሽከርካሪዎችን በማስተናገድ ከ80.8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ከድሬ ደዋሌ ክፍያ መንገድ እንደሚገኝ ታቅዷል፡፡ በጥቅሉ ከሁለቱ የክፍያ መንገዶች ከ405.2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡ ከመረጃው አንፃር ሲታይ፣ በ2012 ዓ.ም. ይገኛል ተብሎ የታቀደው ገቢ በ2011 ዓ.ም. ከተገኘው ከ129.7 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ይኖረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የአዲስ አዳማን የፍጥነት መንገድ አገልግሎት ሲያስጀምር በ2007 ዓ.ም. በአማካይ ዕለታዊ ገቢው 331,494 ብር ነበር፡፡ በቀን በአማካይ ያስተናግድ የነበረውም 12 ሺሕ ተሽከርካሪዎችን ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ከ23 እስከ 24 ሺሕ ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ከአኃዛዊ መረጃዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ በአጠቃላይ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ መፍጀቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ባለፈው ወር መጠናቀቁ ተገልጾ አገልግሎት የጀመረው የድሬዳዋ ደዋሌ የክፍያ መንገድ ደግሞ 5.2 ቢሊዮን ብር ያህል ፈጅቷል፡፡
የሁለቱም የክፍያ መንገዶች የግንባታ ወጪ 85 በመቶው ከቻይና ኢምፖርት ኤስፖርት ባንክ በብድር የተገኘ ሲሆን፣ 15 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሸፈነ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የአዲስ አዳማ የክፍያ መንገድ በአሁኑ ወቅት 600 ሠራተኞች አሉት፡፡ የድሬዳዋ ደዋሌ መንገድ ደግሞ ለ200 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የገለጹት ወ/ሮ ዘሀራ የኢንተርፕራይዙን ሠራተኞች ቁጥር ከ800 በላይ ያደርሰዋል፡፡ የዚህ መንገድ ሥራ መጀመር ደግሞ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ይሰጣል፡፡ ለአብነት ያነሱም ከዚህ ቀደም ከድሬዳዋ ደዋሌ ለመድረስ አሥር ሰዓታትን የሚፈጅ ሲሆን፣ አሁን ከአራት እስከ አምስት ሰዓታት ብቻ የሚፈጅ መሆኑ ነው፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት የክፍያ መንገዶች ያወጣውን ወጪ ለመመለስ የሚችለው በሁለት አሥርት ዓመታት መሆኑን ነው፡፡
የአዲስ አዳማ የክፍያ መንገድ አገልግሎት ከጀመረበት ጊዜ እስካሁን በአምስት ዓመት ውስጥ ያስገኘው ገቢ 965 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ለግንባታው ከወጣው ወጪ አንፃር እስካሁን ያስገኘው ገቢ ሲታይ ከአሥር በመቶ ያነሰ ነው፡፡
ይህም የግንባታ ወጪን ለመመለስ ከ20 ዓመታት በላይ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ የድሬዳዋ ደዋሌም መንገድም ለ17 ዓመታት እንዲያገለግል የተገነባ ሲሆን፣ ክፍያውን ለመመለስ ወደ 20 ዓመታት ሊጠይቅ ይችላል፡፡
ይሁን እንጂ የክፍያ መንገዶቹ በየዓመቱ ሊያስገኙት የሚችሉት ገቢ እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ ምናልባት ወጪያቸውን ለመመለስ የሚወስደው ጊዜ በተወሰነ ደረጃ ዝቅ የሚልበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ይገመታል፡፡ ዋና ነገር ግን መንገዶቹ የሚሰጡት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆን ነው፡፡
የክፍያ መንገዶች ከሚሰጡት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር ወጪያቸውን በአጭር ጊዜ ለመመለስ ባይችሉም፣ አስፈላጊነታቸው የታመነበት በመሆኑ ተጨማሪ የፍጥነት መንዶችን በመገንባት ወደ ሥራ የማስገባቱ ሥራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አሁን በግንባታ ላይ የሚገኘው የሞጆ ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡
ከሁለቱ የክፍያ የፍጥነት መንገዶች በተጨማሪ ሌሎች ሦስት መንገዶች፣ በግሉና በመንግሥት አጋርነት ሥርዓት ሊገነቡ እንደሚችሉ መንግሥት ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ከአዳማ ጀምሮ እስከ ድሬዳዋ ባለው መስመር በሦስት ፕሮጀክቶች ተከፋፍለው የሚተገበሩ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ማስታወቁን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ከአዳማ አዋሽ፣ ከአዋሽ ሚኤሶ፣ ከሚኤሶ ድሬዳዋ ባለው መስመር ለሚገነቡት የፍጥነት መንገዶች እስከ 1.1 ቢሊዮን ዶላር መመደቡን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ተሾመ ታፈሰ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡