Friday, June 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲስ አበባ ከምታስተናግደው የሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም የምታገኘው ተጠቃሚነት እንደሚጨምር ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአፍሪካ እስካሁን ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆቴል ኢንቨስትመንት ተመዝግቦበታል

በሞሮኮ ካዛብላንካ ከተማ እ.ኤ.አ. በ2011 የተጀመረውና ለስምንት ዙር የተካሄደው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም፣ በአዲስ አበባም ለሁለት ጊዜ በተከታታይ ተካሂዶ ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎም ከዚህ ቀደም ፎረሙን  ያስተናገዱ ከተሞች ከኢንቨስትመንትና ከተሳታፊዎች ያገኙትን ተጠቃሚነት ያስጠናው የፎረሙ አዘጋጅ የእንግሊዙ ኩባንያ ቤንች ኤቨንትስ፣ አዲስ አበባ ለሦስተኛ ጊዜ ስታስተናግድ በታዳሚዎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ እንዲሁም ከታክስ ገቢ በጠቅላላው ከ3.7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደምታገኝ ሲጠበቅ፣ ከኢንቨስትመንት ስምምነቶችም በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገቢ እንደሚጠበቅ አስታውቋል፡፡

 ቤንች ኤቨንትስ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2014 እና በ2015 ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረሙን አስተናግዳለች፡፡ ይህ በመሆኑም በርካታ የሆቴል ፕሮጀክት ስምምነቶች ተፈርመዋል፡፡ ይሁንና በዚያን ወቅት ከነበረው የተሳታፊዎች ቁጥርና በወቅቱ በተለይም እ.ኤ.አ. በ2014 ከተወጣው ወጪ አኳያ በመጪው መስከረም ወር ለአራት ቀናት በአዲስ አበባ በሚካሄደው ፎረም ላይ የአሥር በመቶ ጭማሪ ቢኖር፣ ቀጥታ ከተሳታፊዎችና ከፎረሙ ከተማዋ የምታገኘው ገቢ 1.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሆን ሲገመት፣ በተዘዋዋሪ መንገድ ሊገኝ የሚችለው ገቢ እስከ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ተገምቷል፡፡ ከፎረሙ መዘጋጀት ጋር በተያያዘ ከታክስ ሊገኝ የሚችለው ገቢም 250 ሺሕ ዶላር እንደሚሆን በመታሰቡ በጠቅላላው ከፎረሙ ሊገኝ የሚችለው ገቢ ከ3.75 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ይህንን ጥናት ያጠናው ፊውቸርኒር አማካሪዎች የተሰኘ ገለልተኛና ዓለም አቀፍ ተቋም እንደሆነ ቤንች ኤቨንትስ ጠቅሶ፣ የጥናቱ መነሻም ከዚህ ቀደም በታዳሚዎች ላይ በተደረገ ጥናት የተገኘ ውጤት ስለመሆኑም መግለጫው ያትታል፡፡ በመሆኑም ታዳሚዎች በቆይታቸው ወቅት ለሆቴል፣ ለትራንስፖርት፣ ለጉብኝት፣ በፎረሙ ለመሳተፍ የሚከፍሉትንና ሌሎችም ወጪዎች ታክለው የአዲስ አበባ ገቢ ከላይ በተጠቀሰው አኃዝ ሲገለጽ፣ ፎረሙ መካሄድ ከጀመረበት ከስምንት ዓመታት ወዲህ አስተናጋጅ አገሮች በጠቅላላው ከ21 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት እንደቻሉም ተጠቁሟል፡፡

ዋናውና ትልቁ ተጠቃሚነት ግን በሆቴል ፕሮጀክቶች አማካይነት የሚመጣው ገቢና ከስምምነቶቹ የሚመነጨው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡ በመሆኑም ከ6,000 በላይ የሥራ ዕድል ያስገኙና ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት የሆቴል ፕሮጀክት ስምምነቶች ፎረሙን ባስናገዱት አገሮች ውስጥ መመዝገቡን ቤንች ኤቨንትስ ያወጣው መግለጫ ያሳያል፡፡

ከመነሻው ማለትም እ.ኤ.አ. በ2011 የሞሮኮ ዋና ከተማ ካዛብላንካ ያስተናገደችው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም፣ በዓመቱና በተከታዩ በኬንያ፣ ናይሮቢ ተስተናግዷል፡፡ አዲስ አበባ ከኖይሮቢ በመረከብ ሁለት ጊዜ አከታትላ ስታስተናግድ፣ የቶጎዋ ሎሜ እ.ኤ.አ. በ2016 የተካሄደውን ፎረም አስተናግዳለች፡፡ የሩዋንዳዋ ኪጋሊ ሁለት ጊዜ አከታትላ ስታስተናግድ፣ እ.ኤ.አ. በ2016 ሁለት ጊዜ ፎረሙ በመካሄዱ ኪጋሊና ሎሜ ተጋርተውት ያለፈ ክስተት ሆኗል፡፡ ዓምና በድጋሚ ለሦስተኛ ጊዜ ናይሮቢ በማስተናገድ ቀዳሚዋ ከተማ ሆናለች፡፡ አዲስ አበባም በመጪው ዓመት ከመስከረም 11 እስከ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚካሄደው ይህ የሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም፣ ከዚህ ቀደም ቢበዛ ለሁለት ቀናት መካሄዱ ሲታወስ ዘንድሮ ቀናቱን ማበራከቱም ለየት እንደሚያደርገው ይታያል፡፡

ይህ ፎረም በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ከአዘጋጆቹ ጋር በመነጋገርና የኢንቨስትመንት ስምምነቶችም እንዲመጡ በማማከር ጭምር በመሳተፍ አገር በቀሉ ካሊብራ ሆስፒታሊቲ የሆቴል አማካሪዎችና የቢዝነስ ኩባንያ መሥራቾች ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ ከመሥራቾቹ አንዱ የሆኑትና የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነዋይ ብርሃኑ እንደሚገልጹት፣ በመጪው መስከረም የሚካሄደውን ፎረም አብሮ ለማሰናዳት ካሊብራ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የዘንድሮው ዝግጅት አዳዲስ ይዘቶች እንደሚኖሩት አስታውቀው፣ ፎረሙ ላይ ሽልማት ሊበረከትላቸው የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ሊኖሩ እንደሚችሉና የፎረሙ ዝግጅትም በመንግሥት ከወዲሁ ድጋፍ እየተደረገለት እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ወሳኙን ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ ነዋይ፣ ኩባንያቸው ከ20 ያላነሱ የሆቴል ፕሮጀክቶች እንዲፈረሙ ማስቻሉንና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመወከል በድርድር ሒደቶችም መሳታፉን አስታውሰዋል፡፡

በአፍሪካ የሆቴል ኢንቨስትመንት እያደገ እንደመጣ ሲገለጽ፣ ኢትዮጵያም በግብፅ የበላይነት በሚመራው በዚህ ተስፋፊ ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከሚታባቸው አሥር ዋና ዋና አገሮች አራተኛ በመሆን ትመደባለች፡፡ ግብፅ ከ15 ሺሕ በላይ ክፍሎች ያሏቸውን 51 አዳዲስ ሆቴሎች እየገነባች ትገኛለች፡፡ ከናይጄሪያና ከሞሮኮ በመከተል አራተኛዋ ኢትዮጵያም ባለፈው ዓመት ብቻ 31 አዳዲስ ሆቴሎችን ለመገንባት ስምምነት ፈርማለች፡፡ ከአብዛኞቹ ስምምቶች ጀርባም ካሊብራ ሆስፒታሊቲ አማካሪዎች እንደሚገኝበት ታውቋል፡፡ ከሆቴል ኢንቨስትመንት በተጨማሪም የሆቴሎች ዓውደ ርዕይም በኢትዮጵያ እግሩን መትከል ጀምሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች