Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣበትን የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ እንዲታደጉ ተጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጣልቃ ገብተው እንዳስተካከሉት ሁሉ፣ ትልቅ ተስፋ ቢጣልበትም በአሁኑ ወቅት እየመከነ የሚገኘውን ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካንም እንዲታደጉ ተጠየቀ፡፡

ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት በመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክት ግንባታዎች ውስጥ ለረዥም ጊዜ የሠሩትና በአሁኑ ወቅት መንግሥታዊውን የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ላይ የሚገኙት አቶ ሳሙኤል ሃላላ ናቸው፡፡  

አቶ ሳሙኤል ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ተፈጥረው የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ መልካም ዕርምጃዎችን ወስደዋል፡፡

‹‹ጊዜው ቢዘገይም የህዳሴ ፕሮጀክት ዕውን በሚሆንበት ደረጃ አስተካክለውታል፤›› በማለት የገለጹት አቶ ሳሙኤል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክትንም በተመሳሳይ መንገድ ጣልቃ ገብተው እንዲያስተካክሉ›› ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

አቶ ሳሙኤል ጨምረው እንደገለጹት፣ በያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክት ላይ በተሟላ ቴክኖሎጂና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ጥናት ተካሂዶ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ፣ ይህ ካልሆነ ግን ከፍተኛ የአገር ሀብት የፈሰሰበት ፕሮጀክት ባክኖ ይቀራል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ በ600 ኪሎ ሜትር ርቀት በኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦራ ዞን ያዩ ወረዳ የተጀመረው የኮል ፎስፌት ማዳበሪያ ኮምፕሌክስ ፕሮጀክት ከጅምሩ አወዛጋቢ ነበር፡፡

የውዝግቡ ምክንያት ሦስት ቁም ነገሮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ እነሱም የአካባቢ ተፅዕኖ፣ ከፍተኛ ደን ተመንጥሮ በቁፋሮ የሚወጣው የድንጋይ ከሰል ጥራት አነስተኛ መሆንና የፋብሪካው ግንባታ በዘርፉ ምንም ዓይነት ልምድ ለሌለው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን  (ሜቴክ) ሥራው በትዕዛዝ መሰጠቱ ናቸው፡፡

ፕሮጀክቱ ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር በተቋቋመው ኮል ፎስፌት ማዳበሪያ ኮምፕሌክስ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አማካይነት የተለያዩ የጂኦሎጂና የአዋጭነት ዝርዝር ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡

በፌዴራል መንግሥት በተሰጠው አመራር መሠረት የፋብሪካ ግንባታዎች በሜቴክ እንዲከናወን ተወስኖ፣ ውሉ በፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲና በሜቴክ መካከል ተፈርሟል፡፡

መጀመርያ በተካሄደው ጥናት የታሰበው 300 ሺሕ ቶን ዩርያ፣ 30 ሺሕ ቶን ሜታኖል፣ 90 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ማምረትና ማመንጨት ቢሆንም፣ ሜቴክ በድጋሚ ባካሄደው ጥናት ፕሮጀክቱ እጅግ ተለጥጧል፡፡

በዚህ መሠረት አምስት እያንዳንዳቸው በዓመት 300 ሺሕ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች፣ ሦስቱ እያንዳንዳቸው በዓመት 250 ሺሕ ቶን ዳፕ ማዳበሪያ  የሚያመርቱ ፋብሪካዎችና ሌሎች ተያያዥ ፋብሪካዎች ግንባታ ተጨምሮ ታቅዷል፡፡

በወቅቱ የተነሳው አለመግባባት ፕሮጀክቱ የሚካሄድበት ቦታ፣ በኢትዮጵያ ምናልባትም የተፈጥሮ ደን ያለበት በመሆኑ ደኑን አጥፍቶ ይህን ፕሮጀክት ማካሄድ አግባብ አይደለም የሚል ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ደኑ ተመንጥሮ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ጥራት የሌለው በመሆኑ፣ የታሰበውን ምርት በዝቅተኛ ወጪ ማምረት አያስችልም የሚል ይገኝበታል፡፡ ከዚህ በዘለለም ሜቴክ ምንም ዓይነት ልምድ የሌለው በመሆኑ፣ አገሪቱን ብዙ ሀብት ያሳጣታል የሚል መከራከሪያ ቀርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን መከራከሪያዎች በሙሉ ቦታ አልተሰጣቸውም፡፡

ይህ ፕሮጀክት በእስካሁኑ ሒደት 11 ቢሊዮን ብር የወጣበት ሲሆን፣ ሥራውን ለማጠናቀቅ 20 ቢሊዮን ብር በድጋሚ ተጠይቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሥራው የቆመ ሲሆን፣ በጅምር የቀረውን ይኼ ፕሮጀክት ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ይዘውታል፡፡

ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበት ይህ ፕሮጀክት በችግሮች የተሞላ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጣልቃ ገብተው እንዲታደጉት ተጠይቋል፡፡

አቶ ሳሙኤል እንደሚሉት፣ እነዚህ ግንባታዎች ትልቅ ልምድ የሚጠይቁ ቢሆንም ሜቴክ በድፍረት ገብቶባቸዋል፡፡

‹‹ልምድ ከቀሰምክ በኋላ መሥራት የምትችላቸው ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ይህ ፕሮጀክት የተራቀቀ፣ ልምድና ዕውቀት የሚጠይቅ ነው፤›› ሲሉ ሥራው ከኮርፖሬሽኑ አቅም በላይ እንደሆነ አቶ ሳሙኤል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ፣ ይህንን ሰፊ ተቋም ካልሠራሁት በማለት፣ ለዚያውም ዲዛይኑን እየሠራሁ እገነባለሁ በማለት ሥራውን ወስዷል፡፡

‹‹ኮርፖሬሽኑ የተረከበው ሥራ እጅግ በጣም ከፍተኛ ክህሎት ያለው ተቋም የሚወስደውን ሥራ ነው፡፡ ልምድ ሳይኖረው ዲዛይን ከሥር ከሥር እየሠራሁ እገነባለሁ በማለት ተረከበ፤›› በማለት ሁኔታውን የሚገልጹት አቶ ሳሙኤል፣ ‹‹ማን ይጠይቀናል ካልተባለ በስተቀር ፕሮጀክቱ ችግር ውስጥ እንደሚገባ ጥርጥር የለውም ነበር፤›› ሲሉ አቶ ሳሙኤል አስረድተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች