Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጭነት ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ የገደበው መመርያና ውጤቱ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጭነት ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለመወሰን ያወጣውን መመርያ ተግባር ላይ ማዋል ጀምሯል፡፡

በዚህ ውሳኔ መሠረት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ትልልቅ የሚባሉ ተሽከርካሪዎች በቀን እንቅስቃሴያቸው ተገድቧል፡፡ አስተዳደሩ ይህንን መመርያ ለማውጣት ከወሰነባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓታት የሚታየውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅና አደጋ ለመቀነስ ነው፡፡ የአካባቢ አየር ብክለት ለመቀነስ፣ ተሽከርካሪዎችም አገልግሎታቸውን በተቀላጠፈ ሁኔታና የሎጂስቲክስ ወጪን በመቀነስ ማከናወን እንዲችሉ ለማድረግ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት፣ ሥልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 64/2011 አንቀጽ 49(9) መሠረት የወጣው መመርያ፣ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የከተማዋን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ የጭነት ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀሻ ፈቃድ ቁጥጥር ሥርዓት እንደሚዘረጋ ተደንግጎ የሚገኝ በመሆኑ ይኼንን ለማስፈጸም ጭምር ነው፡፡ እንዲህ ያለውን መነሻ ይዞ ተግባራዊ የተደረገው መመርያ በከተማ ውስጥ ይታይ የነበረውን የትራፊክ እንቅስቃሴ ችግር የፈታ መሆኑ እየተነገረ ቢሆንም፣ በአንፃሩ በምሽት ብቻ ተገድበው እንዲንቀሳቀሱ የተወሰነባቸው የጭነት ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴዎችና ከእነሱ ሥራ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቢዝነሶች ችግር ውስጥ እየገቡ መሆኑን የዘርፉ ተዋንያን እየገለጹ ነው፣ አቤቱታቸውንም እያቀረቡ ነው፡፡ ወትሮ በቀን ሥራቸውን ያከናውኑ እንደነበር የሚናገሩ የጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች፣ አሁን በአዲሱ መመርያ እየተስተጓጎልን ነው እያሉ ነው፡፡

ከሁሉም በላይ ግን በዚህ መመርያ ምክንያት የወጪ ንግድ ምርቶችን ለማጓጓዝ ፈተና እንደገጠመ እየተነገረ ነው፡፡ በሥጋ፣ በአበባ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ የወጪ ንግድ  የተሰማሩ ኩባንያዎች የዚህ መመርያ አተገባበር በእጅጉ እንዳሳሰባቸው፣ በተናጠልና በማኅበሮቻቸው አማካይነት መመርያው ከተተገበረ ማግሥት ጀምሮ አቤቱታቸውን እያቀረቡ ነው፡፡ መመርያው በተተገበረ በመጀመርያው ቀን ሥጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ያደርጉት የነበረው ግስጋሴ አዲስ አበባ መግቢያ መንገዶች ላይ መገታቱ እንደታወቀ የተጀመረው እንቅስቃሴ እስካለፈው ዓርብ ሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የወጪ ንግድ ምርቶች የሚጓጓዙባቸው ተሽከርካሪዎች በዚህ መመርያ እንዲስተናገዱ መደረጉ አግባብ አይደለም፡፡ ይመለከታቸዋል ለተባሉ መሥሪያ ቤቶች በደብዳቤና በአካል ማስረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ብዙዎቹ ላኪዎች ይህ መመርያ በፍፁም የወጪ ንግድ ምርቶችን የሚያጓጉዙ ባለማቀዝቀዣ ተሽከርካሪዎች ላይ ይተገበራል ብለው ያልጠበቁት ስለነበር፣ በቀላሉ የሚበላሹትን ምርቶቻቸውን ለማስለቀቅ ይመለከታቸዋል የተባሉ ቢሮዎችን በማንኳኳት መፍትሔ ማፈላለጋቸውን አስረድተዋል፡፡

መፍትሔ በማፈላለጉ ረገድ የጎላ ድርሻ የነበረው የኢትዮጵያ ሥጋ ላኪዎች ማኅበር፣ ሥጋ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ለማስለቀቅና ይህ መመርያ ፈፅሞ ሊመለከታቸው እንደማይገባ ለማስረዳት ይመለከታቸዋል ላሏቸው መንግሥታዊ ተቋማት ማሳወቃቸውን ጠቁመዋል፡፡   

በመጀመርያዎቹ ሁለት ቀናት ለአቤቱታቸው በአግባቡ መልስ ለማግኘት የተቸገሩ ቢሆንም፣ ከሁለት ቀን በኋላ እንደ መፍትሔ የተቀመጠውም አቅጣጫ ጉዳዩን ያወሳሰበ እንደሆነ የሚያመለክት ሆኗል፡፡ እንደ መፍትሔ የተቀመጠው የወጪ ንግድ ምርት የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች በክፍያ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ መባሉ ነው፡፡ በክፍያ ለመንቀሳቀስም የወጣው መመርያ ግራ ያጋባ መሆኑን የዘርፉ ተዋናዮች ተናግረዋል፡፡ ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ከኤጀንሲው የወጣው የጭነት፣ የማሽነሪና መሰል ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴዎች በተመለከተ በሚል ሥጋ፣ አበባና ፍራፍሬ የሚጭኑ በክፍያ የሚስተናገዱበትን ሁኔታ የሚያመለክት ሌላ መመርያ ወይም ማስፈጸሚያ ነው፡፡ ይህ መመርያ ‹‹ከመመርያ ቁጥር 01/2011 ለከባድ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በክፍያ የሚንቀሳቀስ ፈቃድ የሚሰጠው በአንቀጽ 6 መሠረት የግድ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው፤›› ይላል፡፡ አያይዞም፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ በዚህ አግባብ የሚስተናገዱት ኤክስፖርት የሚደረጉና ሊበላሹ የሚችሉ (አበባ፣ ሥጋና ፍራፍሬ) ብቻ ሲሆኑ፣ ከዚህ ውጪ ያሉ እንቅስቃሴዎች በመመርያው በተፈቀዱ ጊዜያት ብቻ መከናወን ስለሚችሉ፣ የክፍያ ፈቃድ እንደማንሰጥ እያሳወቅን ከኤክስፖርት ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ የፈቃድ ጥያቄዎች ማሟላት አለባቸው፤›› በማለት መሥፈርቶችን ይገልጻል፡፡

ማሟላት አለበት ተብሎ በቅድሚያ የተጠቀሰው ዕቃ ኤክስፖርት የሚደረግና የሚበላሽ መሆኑን የሚገልጽ የድጋፍ ደብዳቤ የሚል ነው፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ፕሮግራምና በመመርያው የተዘረዘሩ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት የሚሉም ይገኙባቸዋል፡፡ ተሽከርካሪ ለማንቀሳቀስ ለሚጠየቅ ፈቃድ የአመልካች ወይም የተወካይ መታወቂያ፣ ማመልከቻ፣ ሊብሬ፣ የታደሰ ንግድ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከተፈቀደው ሰዓት ውጪ  ለመንቀሳቀስ ለጭነት ተሽከርካሪ የሚሰጥ የመንቀሳቀሻ ፈቃድ አገልግሎት ክፍያ ተመን ደግሞ፣ መደበኛ ፈቃድ ለማግኘት በቀን 500 ብር የአገልግሎት ክፍያ ይጠየቅበታል፡፡ ልዩ ፈቃድ ለማግኘት በቀን 1,000 ብር የአገልግሎት ክፍያ የሚያስከፍል ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሚደረግ እንቅስቃሴ የሚያስቀጣ ነው፡፡ ቅጣቱ እንደ ጥፋቱ ክብደትና ድግግሞሽ በገንዘብ ከ500 እስከ 6,000 ብር፣ እንዲሁም በተደራቢነት ከአንድ እስከ ሦስት ወራት የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ዕገዳን ያስቀምጣል፡፡ ይህ የአስተዳሩ መመርያ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴን ያላማከለ ነው ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሥጋ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ አበባው መኮንን፣ ይህ መመርያ ሊበላሹ የሚችሉ እንደ ሥጋና አበባ ጫኝ ተሽከርካሪዎችን ሊመለከት አይገባውም ነበር ብለዋል፡፡

ምርቱ እንደተጫነ ወደ አየር መንገድ መግባት ያለበት ስለሆነ እንዲህ ያለው መስተጓጎል ለምርት መበላሸት፣ የበረራ ሰዓትን ጠብቆ ለማስጫን ጭምር ችግር የሚፈጥር በመሆኑ፣ ጉዳዩ ሊጤን እንደሚገባ በማመልከት ተሽከርካሪዎቹ በልዩ ፈቃድ እንዲገቡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ልዩ ፈቃዱም እየተሰጠ ያለው በክፍያ በመሆኑ፣ በኤክስፖርት ሥራ ላይ አዲስ አሠራር ያስከተለ ስለመሆኑም ሪፖርተር ያነጋገራቸው ላኪዎች ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያለው አሠራር ያልተለመደ ከመሆኑም በላይ ሊያስከትል የሚችለውን ሥጋት በማስረዳት መኪኖቹ በክፍያ እንዲለቀቁ ቢደረግም፣ በቀጣይ እንዴት ሊሠራ ነው? የሚለው ጥያቄ አስነስቷል፡፡ እነዚህን ምርቶች በየጊዜ እንዲህ ባለው ፈቃድና ክፍያ እንዲስተናገዱ ማድረግ አግባብ ባለመሆኑ የኢትዮጵያ ሥጋ አምራቾችና ላኪዎች ከኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ጋር በመሆን የጉዳዩን አሳሳቢነት በመግለጽ ደብዳቤዎች ለተለያዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች አስገብተዋል፡፡

አቶ አበባው እንደገለጹት መመርያው በሥጋ፣ በአበባ፣ በአትክልትና የፍራፍሬ ምርቶች ላይ ተፈጻሚ መሆን እንደሌለበት ነው፡፡ ድርጊቱ ተወዳዳሪነትን የሚቀንስ እንደሚሆን ሊጤንም ይገባል ይላሉ፡፡  እነዚህን የወጪ ንግድ ምርቶች የሚያጓጉዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ አይደለም፡፡ ኤምሬትስ፣ ሉፍታንዛና እንደ ሳዑዲ ኤር ያሉ አየር መንገዶችንም ላኪዎች የሚጠቀሙ በመሆናቸው፣ በመመርያው ምክንያት ተሽከርካሪዎችን በተፈላጊው ጊዜ ለማንቀሳቀስ አይችልም ብለዋል፡፡

በመሆኑም የከተማው አስተዳደሩ መመርያውን በክፍያ ጭምር እንዲተገበር ያደረገበት አግባብና ተሽከርካሪዎቹ እንዲንቀሳቀሱ ማሟላት አለባቸው ብሎ የጠቀሳቸው መሥፈርቶችን ለመተግበር አስቸጋሪ ነው ተብሏል፡፡ አንድ ውጭ አገር ያለ ደንበኛ ዛሬ ከተላከለት ምርት በተጨማሪ በማግሥቱም ሌላ ምርት ሊያዝ ስለሚችል፣ እንዲህ ያለውን አስቸኳይ ትዕዛዝ ለመፈጸም እንደገና ልዩ ፈቃድ ለማግኘት በውጣ ውረዱ ምክንያት ጊዜ ላይኖር ስለሚችል አሠራሩን ፈታኝ እንደሚያደርገውም ተጠቁሟል፡፡

ከአየር መንገዶቹም ጋር የዓመት ወይም የወራት ስምምነት በማድረግ ስለሚሠራ አስቸጋሪ ነው ተብሏል፡፡ ሥጋ፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የሚጫንባቸው ተሽከርካሪዎች ባለማቀዝቀዣዎች በመሆናቸውና ኤክስፖርት ሊደረጉ የሚችሉ ምርቶችን ብቻ የሚያጓጉዙ ስለሆነ፣ ለሌላ ሥራ የሚውሉ ባለመሆናቸው ለእንቅስቃሴያቸው በየዕለቱ ገንዘብ እየከፈሉ ማስፈቀዱም ተገቢ አይደለም የሚል ሙግት ቀርቧል፡፡

‹‹ይህ መመርያ ከመውጣቱ በፊት በደንብ አልተጤነም፤›› ያሉት አንድ  ኤክስፖርተር ደግሞ፣ በደንብ ቢጤን ኖሮ የኤክስፖርት ዘርፉን እንዴት ነው ልናስተናግደው የምንችለው ብሎ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ይመከር ነበር ብለዋል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለውን ቀላል ጉዳይ በመሥራት አማራጮች ተወስደው የተሻለ ነገር ሊሠራ ይችል እንደነበር ነው፡፡ የወጪ ንግዱ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ይመጣል ተብሎ እንዳልጠበቁ የሚገልጹት ላኪዎች፣ መመርያው መውጣቱ ሲታወቅ ኤክስፖርትን ሊመለከት አይችልም የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ ኤክስፖርት እናበረታታለን ተብሎ ድጋፍ እተደረገ፣ በሌላ በኩል ኤክስፖርቱን በቢሮክራሲ የሚያጠላልፍ እንዲህ ዓይነት አሠራር መተግበር አልነበረም በማለት በመመርያውና በአተገባበሩ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል፡፡ 

በትራፊክ ማኔጅመንት መመርያው በልዩ ፈቃድ በክፍያ መንቀሳቀስ ይቻላል መባሉ በራሱ ግራ የሚያጋባ ስለመሆኑ የሚገልጹት ላኪዎች፣ ለፈቃዱ የሚፈጸመው ክፍያ ምክንያቱ ግልጽ አይደለም ይላሉ፡፡ መንግሥት እንዲህ ያለውን ክፍያ መሰብሰብ ዓላማው ሊሆን አይገባም፣ መንቀሳቀስ የሚያስከፍል ከሆነ ሁሉም ላይ መተግበር ነው፣ ስለዚህ አሁን እየሆነ ያለው ነገር ኤክስፖቱን የማያበረታታና የተምታታ ነው ይላሉ፡፡

ለራሱ ሕመም ላይ ያለን የወጪ ንግድ የበለጠ እንዲታመም፣ በተጨማሪ ወጪና በቢሮክራሲ እንዲዳከም ማድረግ ነው ያሉት የዘርፉ ተዋናዮች፣ እንዲህ ያለው የአፈቃቀድ ሥርዓት ብዙ ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ልዩ ፈቃዱን ለማግኘት በሚሞላው ፎርም ላይ የሾፌሩን ማንነት ሊብሬ፣ የተሽከርካሪ ሰሌዳና የመሳሰሉትን የሚያካትት በመሆኑ ብዙ ውጣ ውረድ አለበት ይላሉ፡፡ ልዩ ፈቃድ አሰጣጡም ቢሆን ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖ እንዳልታየም አስረድተዋል፡፡ ልዩ ፈቃዱን ለማግኘት በሚሞላው ፎርም ላይ የሾፌሩ ስም ይጠቀሳል፡፡  በአጋጣሚ አሽከርካሪው ቢታመም በድጋሚ ፈቃድ መጠየቅ ግድ ሊሆን ነው ብለው፣ አሠራሩ ያለውን ክፍተት ተናግረዋል፡፡ በብልሽት ምክንያት ልዩ ፈቃዱ የተገኘበትን ተሽከርካሪ መቀየር ቢያስፈልግ እንደገና ፈቃድ መጠየቅ ሊኖርበት ይችላልና አሠራሩ የሚያሳስብ ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለው መመርያ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡  

አንዳንድ ኩባንያዎች ለውጭ የሚያቀርቡት ሥራ በሁለትና በሦስት ተሽከርካሪዎች ሊሆን ስለሚችል፣ በየዕለቱ እነዚህን ተሽከርካሪዎች ለማንቀሳቀስ በልዩ ፈቃዱ እንዲከፍሉ የሚገደዱበት ገንዘብ ለተጨማሪ ወጪ ይዳርገናል ብለዋል፡፡  

የሥጋ ላኪዎች ማኅበር ይህ አካሄድ የወጪ ንግድ እንዳይበረታታ የሚያደርግ በመሆኑ፣ አሁንም ሊታሰብበት እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ ባለፉት ሁለትና ሦስት ቀናት ከከተማው አስተዳደር፣ ከትራንስፖርት ቢሮና ኤጀንሲዎች ጋር የተደረገው ውይይት መልስ የማያገኝ ከሆነ፣ ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቤት ለማለት መዘጋጀታቸውን አቶ አበባው ገልጸዋል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ደግሞ እስካሁን የነበረው ውይይት ተስፋ ሰጪ ነው ይላሉ፡፡

እንደ ወጪ ንግድ ምርት ማጓጓዣዎች ሁሉ ሌሎች የተለያዩ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ የጭነት ተሽከርካሪዎች፣ የአስተዳደሩ መመርያ ጎድቶናል መላ ሊበጅለት ይገባል በማለት ያማርራሉ፡፡ የሲኖትራክ ባለቤት የሆኑት አቶ ዳንኤል አባተ እንደገለጹት፣ መመርያው አስቸጋሪ ነው፡፡ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች እንደሚጠቁሙት፣ አስተዳደሩ ያወጣው አዲስ መመርያ በአጠቃላይ ሥራቸውን ማስተጓጎሉንና የገቢ ምንጫቸውን መግታቱን ነው፡፡ ከእንቅስቃሴ እንዲታቀቡ የተቀመጠው የሰዓት ገደብ የረዘመ በመሆኑ፣ ምንም ዓይነት ሥራ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት የማያስችል ነው ይላሉ፡፡ እንዲንቀሳቀሱ በተመደበላቸው ሰዓት እንሥራ ቢሉ እንኳን፣ አብዛኞቹ የኮንስትራክሽን ዕቃዎችን የሚያቀርቡ ድርጅቶች በምሽት ስለማያገበያዩ ችግሩን አብሶታል ሲሉም ይናገራሉ፡፡

ስለዚህ ችግሩ በከባድ ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ንግድ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ጭምር ላይ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ መመርያው ከወጣ ወዲህ በኢኮኖሚው ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነም እየተነገረ ነው፡፡ ለኮንስትራክሽን ግንባታ መጓተት ምክንያት ስለመሆኑ ከአንዳንድ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች እየተሰማ ሲሆን፣ ለግንባታዎች ማካሄጃ በቶሎ የሚፈለጉ ምርቶችን ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ መፈጠሩም እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህም በኋላ በቀን የግንባታ ግብዓቶችን ለማምጣት ካልተቻለ፣ የግንባታ ሥራዎችን በወቅቱ ለማጠናቀቅ ፈተና ይሆናል የሚሉም አሉ፡፡

ስለዚህ መመርያው ሥራ ላይ በመዋሉ በከተማ ውስጥ ይታይ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ያስተነፈሰ ቢሆንም፣ መንግሥት ሊከተል የሚችለውን ቢያንስ የተራዘመው የእንቅስቃሴ ዕገዳ ሰዓትን ማሻሻል ተገቢ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹የምንለውጠው ነገር የለም›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩት ላኪዎች ግን የኤክስፖርት ወጪን መጨመርና ቢሮክራሲን ማበራከትና እንደ አገር ጉዳት ስላለው መመርያው መታየት ይኖርበታል፡፡ መመርያው የወጪ ንግድ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለው አቤቱታ ካቀረቡት ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው የአበባ፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ዘርፍ ባጠናቀቀው በጀት ዓመት 307 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቷል፡፡ ከሥጋ ወጪ ንግድ ደግሞ ከ104 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል፡፡  

አስተዳደሩ በወጣው መመርያ መሠረት ቀላል የጭነት ተሽከርካሪዎች ከጠዋቱ 12፡30 እስከ 4፡00 ሰዓት፣ እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከቀኑ 10፡00 እስከ ምሽቱ 2፡00 ሰዓት፣ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከማለዳው ከ12፡30 እስከ ምሽቱ 2፡00 ሰዓት ወደ ከተማ መግባትም ሆነ በከተማ ውስጥ መንቀሳቀስ፣ እንዲሁም ጭነት የመጫንና የማውረድ ተግባር ማከናወን የተከለከለ መሆኑን የሚያሳውቅ ነው፡፡

ባለብረትም ሆነ ባለጎማ የኮንስትክሽን ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ወደ ከተማ ውስጥ መግባትም ሆነ መንቀሳቀስ፣ እንዲሁም ጭነት መጫንና ማራገፍ የሚችሉት ከምሽቱ 2፡00 እስከ ማለዳ 12፡30 ሰዓት ብቻ ይሆናል ይላል፡፡ የፈሳሽ ቆሻሻ የማንሳት አገልግሎት የሚሰጡ በከተማ ውስጥ መንቀሳቀስ የሚችሉት ከጠዋቱ 4፡00 እስከ ቀኑ 10፡00 ሰዓት ብቻ እንደሆነ በመመርያው ሠፍሯል፡፡ የደረቅ ቆሻሻ የማንሳትና ውበትና መናፈሻ ቦታዎችን ውኃ የማጠጣት አገልግሎት የሚሰጡ ከጠዋቱ 12፡30 እስከ ምሽቱ 2፡00 ሰዓት፣ በከተማው ውስጥ መንቀሳቀስም ሆነ ውኃ የማጠጣት ተግባር ማከናወን የተከለከለ መሆኑንም ይደነግጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች